ዜና

አንጣሬ (አንጣሪያ)፣ ትኩረት ያጣው ጉምቱ ምግብ

Views: 98

መነሻ፣

በአማሪኛ አንጣሬ (Antare) ወይም አንጣሪያ ይባላል፡፡ በኦሮሚፋ ማራሬ (marare) ይባላል፡፡  በእኛ አገር አረም እንደሆነ ይታወቃል፡፡

እነ ደምል ተከታይ ባዘጋጁት የጥናት ሪፖርት (መጽሐፍ) ላይ የሚከተለው መረጃ ይገኛል፡፡ ከ ባህር ወለል በላይ ከ ዜሮ እስከ 2,35ዐ ሜ.ባ.ወ.በ ይበቅላል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ባሌ፣ ጋሙጎፋ፣ ጎንደር፣ ሐረርጌ፣ ኢሉአባቦር፣ ከፋ፣ ሸዋ፣ ሲዳሞ እና ወሎ ይገኛል፡፡ በየቦታው በተለያየ ቋንቋ ብዙ መጠሪያዎች አሉት፡፡ ከነዚህም በትግሪኛ- መለሔና፣ በአኙዋ-አዲላጌ፣ በአሪ-ሙቃዛ፣ በጋሞ- ቹርቃሌ፣ በከምባታ-አርባግራሶ፣ በኮንሶ-ማራይታ፣ ተብሎ ይጠራል፡፡  የተክሉ ሙሉ ክፍል ወይም ለጋ ቀንበጡ በጋሙጎፋ፣ በተለይም በሰገን ወንዝ ወይናደጋ እና በኮንሶ ደጋ ቦታዎች፣ ባኮ ጋዘር፣ ደቡብ ኦሞ፣ ሰሜን ኦሞ ቆላ፣ ጂንካ እና ጋምቤላ  ውስጥ ለምግብነት ይጠቀማሉ፡፡ አመቱን ሙሉ በተለያየ የአገሪቱ ክፍሎች፤ በተለያየ ወቅት ይበቅላል፣ ያብባል፣ ያፈራል ወዘተ፡፡ ይበቅላል በተባለባቸው ቦታዎች በወቅቱ ይገኛል፡፡  ቅጠል እና አገዳውን ጭምር በኬንያ፣ ታንዛንያ እና ኡጋንዳ ይመገቡታል፡፡ ማጣቀሻ አንድ

በሥነምግብ ይዘቱ ከፍተኛ የሆነ ቢሆንም  ወደ ጓሮ ልማት ያመጣው የለም፡፡ በሌሎች አገራት በተለይም አሜሪካ፣ ቻይና፣ አውሮፓ በጣም ጥሩ ጠቀሜታ በመሥጠት ይታወቃል፡፡ እንደተለመደው ከፍተኛ የሥነምግብ ዋጋ ያላቸው ተክሎች በእኛ አገር ዕውቅና አልተሰጣቸውም፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ አንጣሬ ነው፡፡

አንጣሪያ የሳይንስ መጠሪያው ፖርቱላሴ ኦለራሴ (Portulaca oleracea )   ሲሆን በእንግሊዘኛ ፐርስላኔ (Purslane) ይባላል፡፡ በብዙ የጥናት መረጃ ላይ ኦሜጋ 3 ፋቲ አሲድ መገኛ እና አንቲኦክሲደንት እንደሆነ ይነገርለታል፡፡  ቫይታሚን ኤ፣ ቢ፣ ሲ፣ ኢ አለው፡፡ ከማዕድናት ካልስየም፣ ማግኒዝየም፣ ፖታስየም እና ሌሎችም እንዳሉት ይነገራል፡፡ ከተክሎች ሁሉ በተለየ የኦሜጋ 3 ፋቲ አሲድ (rich in omega-3 fatty acids)  ይዘቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህም ለልብ ጤና ጠቀሜታ አለው፡፡ ከማንኛውም የልብ ህመም ለመከላከል ይረዳል፡፡ ብግነትን ይከላከላል፣ ለቆዳ ጤንነት ጥሩ ነው፡፡ ለዓይነት 2 የስኳር ታማሚዎች ምቹ ምግብ ነው፡፡ ማጣቀሻ አንድ

አንጣሪያ ዝናው የጎላው በአሜሪካ፣ አውሮፓ፣ በጃፓን፣ በደቡብ ኮሪያ እና በመሳሰሉት ነው፡፡ በእኛ ዘንድ  እንደ አረም ተቆጥሮ ዱርበቀል ሆኖ መቅረቱ ያስቆጫል፡፡

በዚህ በክረምት ወቅት አዲስ አበባ እና አዳማ ከተማው በሙሉ አንጣሪያ ነው፡፡ በየመስኩ ይገኛል፡፡ ሌላው ቀርቶ በኮብል ድንጋይ በተሠሩ መንገዶች ላይ ይበቅላል፡፡ ከላይ የመኪና ጎማ እየተንከባለለበት፣ እግረኛ እየተራመደበት ይበቅላል፡፡ እንዴት አደጋ ተቋቋሚ ተክል መሰላችሁ??

ሀ/  የአንጣሪያ አበቃቀል

በኢትዮጵያ አረም፣ ዱር በቀል ነው፡፡ እንደቦታው ወቅታዊ ነው፡፡ እንደአረም ሆኖ በቀላሉ ይባዛል፡፡ ሙቀት ይወዳል፣ የፀሐይ ብርሃን ይፈልጋል፡፡ አሸዋማ አፈር ይመርጣል፡፡ መሬት ላይ ሰፋ ብሎ ያድጋል፣ ከተመቸው እስከ 3ዐ ሣ.ሜ ከፍ ብሎ ይረዝማል፡፡ በሚበቅልበት ጊዜ በጥቂት ጊዜ ፍሬ ያፈራል፣ ፍሬው ሲራገፍ መልሶ ይበቅላል፡፡ ይህ የአረምነት ፀባዩ ነው፡፡ በእኛ አገር በአብዛኛው የእርሻ ባለሙያዎች አስቸጋሪ ወይም ወራሪ አረም እንደሆነ ይታመናል እንጂ ጠቃሚ ምግብ ተብሎ ምክር አልተነገረለትም፡፡

ብቃዩን ነቅሎ ወይም ግንጣዩን በጓሮ መትከል ይቻላል፡፡ ዘሩንም በመዝራት ይባዛል፡፡ እጅግ በዝቶ ወደ ወራሪ አረም ደረጃ እንዳይደርስ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በበጋ ወራት ውሃ ካላገኘ ይደርቃል፡፡ ውሃ ማጠጣት ነው፡፡

እንደአረም በዝቶ መሬት እንዳይወር በየጊዜው ማረም እና ማስወገድ ነው፡፡ ካስቸገረ ግን ማንኛውንም የአረም መከላከያ ዘዴ መጠቀም ነው፡፡

ለ/ ለምግብ ጠቀሜታው

ለጋ ቅጠሉን ከነዘንጉ መቁረጥ፣ ደህና አድርጎ ማጠብ፤ በሚፈልጉት መጠን መክተፍ፤ በቀላሉ ምግብ ማሰናዳት ነው፡፡

በዋናነት

በጥሬው ይበላል፣

በውሃ ይቀቀላል፣

በእንፋሎት ይበስላል፣

በዘይት ይጠበሳል፣

በአገራችን ባህል እንደ መጠባበስ፣ እንደ ወጥ፣ ሰላጣ፣ ሾርባ፣  ጎመን ዓይነት ለብቻው ወይም ከሌሎች ተክሎች ጋር ወይም ከእንቁላል ጋር፣ ከሥጋ ጋር ማብሰል ይቻላል፡፡ በእንጀራ ወይም በዳቦ ይበላል፡፡

ለምሳሌ፣

  • ከላይ በምስሉ ላይ እንዳለው በርከት አድርጎ መልቀም፡፡ ይህንን በዘይት ለመጥበስ ቢፈለግ፣ ከቀይ ሽንኩርት፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ጨው፣ ወዘተ ጋር በ3 ደቂቃ ይበስላል፡፡
  • በሾርባ ላይ ለማከል ቢፈለግ የተሠራው ሾርባ በስሎ ሲያበቃ መጨመር ነው፡፡
  • ጥሬውን ሠላጣ ለመሥራት፣ ለሠላጣ የተለመዱ አሠራሮችን መከተል ነው፡፡

ሐ/  የአንጣሪያ ልማት እና እንክብካቤ

ከዱር፣ ከማሳ ዳርቻ ወይም ከተገኘበት ነቅሎ ወደ ጓሮ አምጥቶ መትከል ይቻላል፡፡ በተተከለ ከሁለት ሳምንት በኋላ ከላዩ እየቀነጠቡ  ምግብ ማዘጋጀት ነው፡፡ ዘር ከማፍራቱ በፊት በየጊዜው መቀንጠብ እና መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ በተተከለበት ቦታ ዘር ካፈራ ለምግብ የሚሆን የሚለቀምለት አይኖረውም፡፡  ዘር እንዲያፈራ ከተፈለ አለመቀንጠብ ነው፡፡ ሲያፈራ ዘሩ ደቃቃ እና ጥቁር ነው፡፡ ሥራዬ ብሎ የያዘው ሰው ያንን መልሶ በሌላ ቦታ ወስዶ በሰፊው መዝራት ይችላል፡፡

መ/ አንጣሪያ ላኪ እና ተቀባይ አገራት ማጣቀሻ ሁለት

በዓለም ደረጃ ከፍ ባለ ዋጋ እንደሚሸጥ እና እንደሚገዛ ማጣቀሻ ሁለት ላይ ከታች በሊንኩ  ያለውን አንብቡ እና “አጃኢብ ነው” በሉ፡፡

መ.1  ወደ ውጪ ላኪ አገራት

በአገራቸው በከፍተኛ መጠን አምርተው ወይም ከሌላ ገዝተው ወደ ውጪ ላኪ አገራት በደረጃ ሲቀመጡ 1ኛ/ ቻይና፣ 2ኛ/ቤልጀም፣ 3ኛ/ስፔን፣ 4ኛ/ሜክሲኮ፣ 5ኛ/ ፖላንድ ወዘተ ናቸው፡፡

መ.2 ወደ አገር ውስጥ ተቀባይ አገራት

1ኛ/አሜሪካ፣ 2ኛ/ጃፓን፣ 3ኛ/ጀርመን፣ 4ኛ/ፈረንሳይ፣ 5ኛ/ቤልጀም፣ 6ኛ/ደቡብ ኮሪያ ወዘተ ናቸው፡፡

የገረመኝ ቤልጀም ወደ ውጪ ላኪነት 2ኛ ስትሆን በተቀባይነት ደግሞ 5ኛ ናት፡፡ በብዙ ያገኘችበት ጥቅም ቢኖረው ነው፡፡ የገዙቱ ለምግብነትም፣ ለመድኃኒት አምራች ፋብሪካም ይጠቀሙት ይሆናል፡፡ አንድን ነገር ዋጋ ቢኖረው ነው ዋጋ አውጥተው የሚገዙት፡፡

አንጣሪያ በደረጃ የተገለፀ ባይሆንም ለአረብ አገራትም እንደሚቀርብ እና በሱፐር ማርኬት እንደሚሸጥ  ያዩ አረብ አገር የኖሩ ሴቶች ነግረውኝ ነበር፡፡

ሠ/ ዋጋው ስንት ይገመታል

በዓለም ገበያ የአንድ ኪሎ ዋጋ ከ3 እስከ 6 ዶላር በአማካይ ይሆናል፡፡ ከ አንድ መቶ አምሳ እስከ ሶስት መቶ ብር እንደማለት ነው፡፡ በአዲስ አበባ በጣም ውድ ቅጠል እስፒናች ነው፡፡ ዋጋው ከ 4ዐ እስከ 7ዐ ብር በኪሎ ይሆናል፡፡ እናም አንጣሪያን በኪሎ ከ3ዐ እስከ 5ዐ ብር ቢገኝ ሰዉ ተደስቶ ይገዛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በተወደደ አትክልት ቆስጣ እንኳን ዋጋው ስንት ነው? ብላችሁ ጠይቁ፡፡

ረ/ ሌላው ጠቀሜታ

በዓለም ላይ ለመድኃኒት ኢንዱስትሪ፣ ለውበት መጠበቂያ፣ ወዘተ ተፈላጊ ነው አንጣሪያ፡፡

ሰ/የቤታችን ሙከራ

እንደተለመደው ይጠቅማል የተባሉትን ተክሎች መሠብሰቤ አይቀርም፡፡ በቅርብ ሁለት ዓመታት ከሌሎች አትክልት ጋር ጎን ለጎን ስንተክል እና ስንመገብ ነበር፡፡ ከምንም አትክልት ጋር በተለይም ከቻያ ጋር ሠርተን ጥሩ ነው፡፡ ማጣቀሻ ሶስት   ስለ ቻያ ማለትም የጀርመን ጎመን ማጣቀሻ ሶስት ላይ በሊንኩ ላይ አንብቡ፡፡

ከአኩሪ አተር ቶፉ ጋር ሲሠራም ተስማሚ ነው፡፡  ከላይ በምስሉ ላይ ያለው ከመስክ ላይ ተለቅሞ ከተተከለ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለ3ኛ ጊዜ የተለቀመ ነው፡፡ አሁንም ገና ይለቀምለት እና እንመገባለን፡፡ በክረምት ወይም በቂ ውሃ ሲያገኝ ቶሎ ቶሎ ያድጋል፡፡

ማጠቃለያ፣

አንጣሬ እስከ ዛሬ በአካባቢያችሁ እያለ  “ዱር በቀል እና ተፈላጊ አይደለም” በማለት ትኩረት ያልሰጣችሁ ወገኖች እነሆ ባለዋጋ እና ተፈላጊ መሆኑን ተገንዘቡ፡፡ እናም በመስክ የሚገኘውን ባለበት መንከባከብ እና ወደጓሮ አምጥቶ ማልማት አስፈላጊነቱን ተረዱ፡፡

እንደ አዲስ የምትሰሙት ደግሞ አንጣሪያን በቤተሰብ ደረጃ በቀላሉ በጓሮ መትከል ትችላላችሁ፡፡ አመቱን ሙሉ ቦታ በማቀያየር ብታለሙት እንደእኛ ቤት ተጠቃሚ ትሆናላችሁ፡፡  በከተሞች የቦታ ጥበት ቢኖር እንኳን በላስቲክ ዕቃ ላይ መትከል ይቻላል፡፡ ለቤተሰብ አባላት ሁሉ ጥሩ ምግብ ይሠራበታል፡፡

በሰፊው ለማልማት እና ለገበያ ለማቅረብ ሥራው እንደሌላው አዝመራ ከባድ አይደለም፡፡ እስቲ ሰፊ እርሻ ያላችሁ ሰዎች ይህንን አጥኑ፣ አስጠኑ፡፡ ለምን ቢባል?

  • ለአገር ውስጥ ገበያ በተወደደ ጎመን እና አበባ ጎመን አንጣሬን ብዙ ሰው ይፈልገዋል፡
  • ለውጪ ገበያ ከኬሚካል ነፃ ሆኖ “ኦርጋኒክ” ተብሎ ዋጋ ይገኝበታል፡፡

አንጣሬ አንድ ቀን የአዲስ አበባ ሱፐርማርኬት የደረሰ ለት ዜና ሆኖ ይነገርለት ይሆናል፡፡

ማጣቀሻ

አንድ፣ Demel Teketay, Feyera Senbeta, Mark Maclachlan, Million Bekele , Pia Barklund and

Demel Teketay. 2010 (eds). Edible Wild Plants in Ethiopia,  Addis  Ababa University

Press, Eclipse PLC,  Addis Ababa, Ethiopia.

ሁለት፣  https://www.tridge.com/intelligences/purslane

ሶስት፣  https://ethio-online.com/archives/15207

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com