ዜና

በበዓሉ ወቅት የቃጠሎ አደጋ እንዳይከሰት ማህበረሰቡ በተለይ ኤሌትሪክ አጠቃቀም ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ተጠየቀ

Views: 70

በበዓሉ ወቅት የቃጠሎ አደጋ እንዳይከሰት ማህበረሰቡ የኤሌትሪክ አጠቃቀምና ማብሰያዎች ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

በ2013 በጀት ዓመት 9 ወራት በእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች በአዲስ አበባ የ74 ሰዎች ሕይወት ማለፉም ተገልጿል።

የትንሳኤ በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የፊታችን እሁድ ይከበራል።
የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ገንኙነት ቡድን መሪ አቶ ጉልላት ጌታነህ በዓሉ ሲከበር ማህበረሰቡ ከእሳትና ድንገተኛ አደጋ አጋላጭ ነገሮች እንዲጠነቀቅ አሳስበዋል።

በተለይም በምግብ ማብሰል ወቅት የኤሌክትሪክ ኃይል ጫና ሊፈጥር የሚችል የሶኬት አጠቃቀም እሳት ሊፈጥር ስለሚችል መጠንቀቅ ያስፈልጋል ብለዋል።
የጋዝ ሲሊንደሮች ከመለኮሳቸው በፊትና በኋላ የሚያስፈልጉ ጥንቃቄዎችንም ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በ2013 በጀት ዓመት 9 ወራት በአዲስ አበባ ከደረሱ 249 የእሳት አደጋዎች መካከል 42ቱ በኤሌትሪክ ኮንታክት የተከሰተ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ጉልላት የኤሌትሪክ ኃይል አጠቃቀም ከፍተኛ ትኩረት ያስፈልገዋል ብለዋል።

በተጨማሪም ሕብረተሰቡ በበዓሉ ወቅት የሚጠቀምባቸውን ከሰል፣ ሻማና ሌሎች ተቀጣጣይ ነገሮችን በጥንቃቄ መሆን እንዳለበት መክረዋል።

የአዲስ አበባ አደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን የትንሳኤ በዓል በሚከበርበት ወቅት የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች እንዳይደርሱ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል።

ለበዓሉ 1 ሺህ 112 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች፣ 27 ከባድ ተሽከርካሪዎች፣ 19 አምቡላንሶችና ሌሎች አደጋን ለመከላከል ጥቅም ላይ የሚውሉ ተሽከርካሪዎች ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለማህበረሰቡ ጥንቃቄ የሚረዱ የግንዛቤ ስራዎችን በእምነት ተቋማት፣ በገበያ ማዕከላትና ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በሌላ በኩል በ2013 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት በመዲናዋ በደረሱ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች የ74 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ያስታወሱት አቶ ጉልላት የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ባደረጉት ርብርብ የ50 ሰዎች ሕይወት ማትረፍ መቻሉን አመልክተዋል።

በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 249 የእሳት አደጋ እንዲሁም 111 ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች መከሰታቸውን ገልጸዋል።

ከተከሰቱት አደጋዎች መካከል 313 በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲሆን 47ቱ ደግሞ በአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞኖች የተከሰቱ ናቸው ብለዋል።

በአጠቃላይ በደረሱ አደጋዎች ከ299 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ንብረት የወደመ ሲሆን፣ በአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በተደረገ ርብርብ ከ3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ላይ ንብረት ማዳን መቻሉን ተናግረዋል።

ከደረሱ የእሳት አደጋዎች የቤት፣ የንግድ ቤቶች፣ የመኪና፣ የቆሻሻ፣ የፖልና የሳር ክምር ቃጠሎ አብዛኛውን ድርሻ እንደሚይዙ የገለጹት አቶ ጉልላት ከድንገተኛ አደጋዎች የወንዝ፣ የጎርፍና የሕንጻ መደርመስ አደጋዎች ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ ብለዋል።

ከደረሱት 360 አደጋዎች 238ቱ መንስኤያቸው እንዳልታወቀም ገልጸዋል።
አደጋዎች ሲያጋጥሙ በነጻ የስልክ መስመር 939፤ በቀጥታ የስልክ መስመሮች 011 155 53 00 ወይም በ011 156 86 01 ደውሎ ማሳወቅ እንደሚችልም ጠቁመዋል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com