ዜና

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ከጠ/ሚ ዐቢይ ጋር በስልክ ተወያዩ

Views: 43

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በስልክ ውይይት ማድረጋቸውንና በኢትዮጵያ “እየተባባሰ ስለመጣው የሰብአዊና የሰብአዊ መብት ቀውስ”ያላቸውን ስጋት በአጽንኦት መናገራቸውን በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ አስታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ በኩል እስካሁን ውይይቱን በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ የለም፡፡ብሊንከን በትግራይ ያለው የረሃብ ተጋላጭነት እንዲሁም በሌሎች አካባቢዊች ያለው አለመረጋጋት አሜሪካን እንደሚያሳስባት ገልጸዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያና ኤርትራ በተስማሙት መሰረት የኤርትራ ጦር በአስቸኳይ እንዲወጣና፣ይህም ማረጋገጥ በሚቻል መልኩ መሆን እንዳለበት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መናገራቸውን ኢምባሲው አስታውቋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቅርቡ የኤርትራ ሰራዊት በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ መግባቱን በይፋ ባሳወቁበት መግለጫቸው፤ የኤርትራ ሰራዊት ከኢትዮጵያ እንዲወጣ ከኤርትራ ጋር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታውቀው ነበር፡፡

‹‹የኤርትራና የአማራ ኃይሎች›› በትግራይ እየተባባሰ ባለው የሰብአዊ መብት ቀውስ ላይ አስዋጽኦ እንዳላቸው ገልጸዋል፤ ሁሉም አካላት ግጭቱን በአቸኳይ እንዲያቆሙ በውይይቱ ወቅት አንስተዋል ብሏል ኢምባሲው፡፡

ኢትዮጵያ፣ የኤርትራ ወታደሮቿ በትግራይ መግባታቸውን ብትገልጽም፤ በሰብአዊ መብት ጥሰት ላይ ተሳትፈዋል የሚልው የአሜሪካና የተመድን ክስ አስተቀበለችም፡፡ የአማራ ክልላዊ መንግስትም፣ አሁን የያዘው ቦታ የክልሉ አካል እንደሆነና በሕገወጥ መንገድ ከክልሉ መወሰዱን ገልፆ፣ በሰብአዊ መብት ጥሰት ተሳትፏል የሚለው ክስን እንደማይቀበል ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

ብሊንከን በትግራይ ክልል የተካሄደውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ለመመዝገብ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽን በጋራ መስራታቸውን በበጎነት ተቀብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ጥቅምት 24 ቀን 2013 የፌደራል መንግስት፣ ህወሓት በትግራይ ክልል በሚገኘው ሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ማድረሱን ካሳወቀ በኋለ፣ ሁለቱ አካላት ወደ ውጊያ መግባታቸው ይታወሳል፡፡ ጥቃቱን ተከትሎ የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል “የሕግ ማስከበት ዘመቻ” ማካሄድ መጀመሩን ተከትሎ በተፈጠረ ውጊያ የሰብአዊ መብት ጥሰት አጋጥሟል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com