ዜና

በሰሜን ሸዋ በደረሰ የእሳት አደጋ ንብረት ወደመ

Views: 63

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በሀገረ ማሪያም ከሰም ወረዳ ሾላ ገበያ የህዝብ መናኸሪያ ትናንት ሌሊት በደረሰ የእሳት አደጋ 4 ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸውን የወረዳው ፖሊስ ፅህፈት አስታወቀ።

የፅህፈት ቤቱ ኃላፊ ኮማንደር ደምሰው ዳኜ እንደገለጹት አደጋው ሌሊት 5:30 አካባቢ በአንድ ሚኒባስ ተሽከርካሪ ላይ የተፈጠረ እሳት ወደሌሎችም ተዛምቶ በንብረት ላይ ጉዳት አስከትሏል።

የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መሆኑነን የገለፁት ኮማደሩ፣ በሚኒባስ ተሽከርካሪው የሞተር ክፍል የኤሌክትሪክ መስመር መገናኘት ምክንያት ሳይሆን አይቀርም ብለዋል፡፡

በአደጋው የእሳቱ መነሻ ተሽከርካሪ ሙሉ ለሙሉ ሲወድም ከጎኑ የነበረ በተለምዶ ዶልፊን የሚባል ተሽከርካሪ በከፍተኛ ሁኔታ ተቃጥሏልም ነው ያሉት፡፡

ኃላፊው በሌላ አንድ የህዝብ ማመላለሻ አይሱዙና ሚኒባስ ተሽከርካሪ ላይ መጠነኛ ጉዳት መድረሱን ጠቅሰው፣ በፖሊስ አባላት እና በማህበረሰቡ ትብብር የጉዳት መጠኑን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል።

የወረዳው ፖሊስ ፅህፈት ቤትም የመናኸሪያውን የእለቱን ጥበቃ በቁጥጥር ስር በማዋል ተጨማሪ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com