ዜና

ጅማ ዞን ውስጥ በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ ‹20 ሰዎች መገደላቸው› ተነገረ

Views: 47

በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ውስጥ በሚገኙ ሁለት ቀበሌዎች ታጣቂዎች ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ በፈጸሙት ጥቃት በርካታ ሰዎችን መግደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ።

ጥቃቱ ዓርብ ሚያዝያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም ሊሙ ኮሳ ወረዳ፣ ቀጮ ክርክራ እና ጋሌ በተባሉ ቀበሌዎች ውስጥ የተፈጸመ ሲሆን፣ ቢያንስ 20 ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን ኢሰመኮ ለቢቢሲ ገልጿል።

በተመሳሳይ እንዲሁ ሐሙስ ሚያዝያ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ፣ ዳኖ ቀበሌ ውስጥ በታጠቁ ኃይሎች በተፈጸመ ጥቃት አንድ ሰው መገደሉን ኮሚሽኑ ጨምሮ አመልክቷል።

የኮሚሽኑ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት አቶ ኢማድ ቱኔ እንደተናገሩት በጅማ ዞን ሊሙ ኮሳ ወረዳ ውስጥ የፀጥታ ኃይሎች የደረሱት ታጣቂዎቹ ጥቃት ፈጽመው በስፍራው በርካታ ንፁሃን ሰዎች ከተገደሉ በኋላ ነው።

ቢሆንም ግን ከዚያ ክስተት በኋላ በነዋሪዎች ላይ ተጨማሪ ጥቃት እንዳይደርስ ለመከላከል መቻላቸውን ጠቅሰው ባለፉት ቀናት የፀጥታ ኃይሎች በተለይም በጅማ ዞን ተሰማርተው ጥቃቱ በቁጥጥር ስር መዋሉን አመልክተዋል።

ኮሚሽኑ ጥቃቶቹን ተከትሎ ወደ አካባቢዎቹ ባለሞያዎችን ለማሰማራትና የደረሰውን ጉዳት በትክክል ማጣራት አለመቻሉን አቶ ኢማድ ቱኔ ተናግረዋል።ኮሚሽኑ ከአካባቢው ባሰባሰበው መረጃ በጅማ ዞን የተፈጸመው ጥቃት የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ መሆኑን የሚያመለክት መረጃ እንዳገኘ አቶ ኢማድ ገልጸዋል።

ቢቢሲ ጥቃት ከተፈጸመበት አካባቢ ነዋሪዎች፣ ከዞኑ እንዲሁም ከወረዳው አስተዳዳሪዎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም

በተመሳሳይ ኮሚሽኑ ጥቃት እንደተፈጸመበት የተገለጸው የአማሮ ልዩ ወረዳ የሰላም እና ደኅንነት ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ኤሊያስ ይልማ ጉዳትና ዝርፊያ መፈጸሙን አረጋግጠዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ በጥቃቱ ከብት ጥበቃ ላይ የነበረ አንድ ግለሰብ መገደሉን እንዲሁም ከ70 በላይ ከብቶች በታጣቂዎቹ ተነድተው መወሰዳቸውን ለቢቢሲ አስረድተዋል። ይህን ጥቃት የፈፀሙትም ከአጎራባች ቀበሌ የተነሱ ሽፍቶች መሆናቸውን ገልፀዋል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com