ዜና

በሀሰተኛ ሰነድ ወደ ኢትዮጵያ የገባ አራት ኮንቴይነር ገጀራ ተያዘ

Views: 48

ሀሰተኛ ሰነድን ተጠቅሞ ወደ ሀገር ውስጥ የገባ የነበረ ብዛቱ 186 ሺህ 240 የእጅ ገጀራ መያዙን መንግስት የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ በፌስቡክ ገጹ እንዳሰፈረው መረጃ ከሆነ ገጀራዎቹ ዳዊት የማነ በተባለ ተጠርጣሪ አስመጪ ስም ነው ከ15 ቀን በፊት በአራት ባለ 20 ጫማ ኮንቴይነሮች ከቻይና ተጭነው ሞጆ ጉምሩክ ጣቢያ የደረሱት።

ሞጆ ጉምሩክ ከደረሰ በኋላ እቃው በዲክላራሲዮን ቁጥር 4-1919/21 ተመዝግቦ ወደ ሀገር ዉስጥ እንዲገባ ከፌዴራል ፖሊስ የተፈቀደለት በማስመሰል እና ሐሰተኛ ሰነድ አዘጋጅቶ ለገቢ ዕቃ አወጣጥ የሰነድ መርማሪው አቅርቦ ሰነዱ ተመርምሮ ከ7 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ ቀረጥና ታክስ ተከፍሎበት እንደነበረም ታውቋል።

ሆኖም ግን እቃው ከተለቀቀ በኃላ በጉምሩክ ኮሚሽን እና በሞጆ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኢንተለጀንስ በኩል ክትትል ተደርጎ የቀረበው ሰነድ ሲጣራ ሐሰተኛ እና እቃዉም ወደ ሀገር ዉስጥ እንዲገባ ከፌዴራል ፖሊስ ፈቃድ ያልተሰጠው መሆኑ መረጋገጡን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ጉዳዩ ከ15 ቀን በፊት የተፈጸመ ቢሆንም አስመጪው “ያቀረብኩት ሰነድ ህጋዊ ነው” በማለት ቅሬታ ስላቀረበ ከፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጋር በጋራ ሲጣራ ቆይቶ በተደረገው ማጣራት ሰነዱ ሐሰተኛ እና ከፌደራል ፖሊስ ፍቃድ ያልተሰጠው መሆኑ መረጋገጡንም ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።

በተጨማሪም የእጅ ገጀራው በጉምሩክ ኮምሽን ሰራተኛ ተገቢውን የጉምሩክ ስነ-ስርዓት በመፈጸም እንዲስተናገድ የሚገልጽ ሐሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት ለማውጣት የተሞከረ ሲሆን ይህም ሐሰተኛ ሆኖ ተገኝቷል።

ይህን መነሻ በማድረግም በፌዴራል ፖሊስ ለሞጆ የወንጀል ምርመራ ማስተባባሪያ ጽህፈት ቤት መረጃውን በመስጠት በተደረገው ክትትል የእቃው ባለቤት እና ትራንዚተሩ ተይዘው ጉዳዩ በምርመራ ላይ እንደሚገኝም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ገጀራ በኢትዮጵያ ክልከላ ከተደረገባቸው እቃዎች አንዱ ሲሆን፣ ከፌደራል ፖሊስ ሕጋዊ ፈቃድ ሳያገኙ ማስገባት አይቻልም።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com