ዜና

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሩሲያ ጉባዔን ለማስተናገድ ያላትን ፍላጎት ገለፀች

Views: 46

ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2022 የሚካሄደውን ሁለተኛውን የአፍሪካ ሩሲያ ጉባዔ ለማስተናገድ ያላትን ፍላጎት ገልፃለች። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በአምባሳደር ደረጃ የአፍሪካ ሩሲያ የትብብር ፎረም ጸሐፊ ኦሌግ ኦዜሮቭ ጋር ተወያይተዋል።

በዚህ ወቅት በፈረንጆቹ 2022 በአፍሪካ የሚካሄደውን የአፍሪካ ሩሲያ ጉባዔ ዝግጅት አስመልክቶ ውይይት አድርገዋል።

አቶ ደመቀ ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር ለረጅም ጊዜ የዘለቀውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ያላትን ፍላጎት ለጸሐፊው ገልፀውላቸዋል።

ሩሲያ ይህን መድረክ ለመፍጠር የወሰደችውን ተነሳሽነት ያደነቁት አቶ ደመቀ፣ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የአፍሪካ ሩሲያ ጉባዔ በአዲስ አበባ ለማዘጋጀት ያላትን ፍላጎት ገለፀዋል።

ኦሌግ ኦዜሮቭ በበኩላቸው ስለ ጽሕፈት ቤታቸው ስራ እና ኃላፊነት ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የአፍሪካ እና ሩሲያ ኩባንያዎች በጋራ እንዲሰሩ የሚያስችል የኢኮኖሚ ትብብር ማህበር መቋቋሙንም በገለጻቸው አንስተዋል።

የጉባዔው ዝግጅት አካል የሆነ ውይይት በመጪው ክረምት ከአፍሪካ ሕብረትና ከአፍሪካ አገራት ጋር እንደሚከናወንም ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈ በደህንነት፣ በቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ ግብርና፣ ኃይል፣ በኒውክሌር፣ በጤና እና በስነ ምድር ምርምር ያላቸውን ትብብር በተመለከተ መክረዋል።

ጸሐፊው ኦሌግ ኦዜሮቭ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ በሞስኮ ጉብኝት እንዲያደርጉ ግብዣ ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com