ዜና

በጎንደር ተቃውሞ ሠልፍ በማንነታቸው ለተገደሉ ሰማዕታት የሻማ ማብራት ሥነስርዓት ሊከናወን ነው

Views: 113

ለሀገር ሠላም በፀሎት እና ስግደት ላይ የሰነበተችው ጎንደር ከተማ፣ በአማራ ክልል ከተሞች የተቀሰቀሰውን የተቃውሞ ሠልፍ ትላንት የተቀላቀለች ሲሆን፤ በዛሬው እለት ተቃውሞው ቀጥሎ ውሏል፡፡ ቅዳሜ ሚያዚያ 16 ቀን 2013 ዓ.ም ደግሞ መላው ጎንደርን ያካተተ የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚካሄድ መርሃ-ግብር መያዙን በአካባቢው የሚገኘው የዜና ወኪላችን አሳውቆናል፡፡

በሰልፉ ላይ፣ ‹‹የተካድነው በኦህዴድ እንጂ፣ በኦሮሞ ህዝብ አይደለም፤ ብልፅግና ለምርጫ ሳይሆን ለፍርድ በዓለም አደባባይ መቅረብ አለበት፤ የአማራ ህዝብ በአደርባዮች እና በስግብግቦች አይመራም፤ አቢይ አዲስ አበባ ላይ የምታከማቸውን ልዩ ኃይል የማናቅ አይምሰልህ፤ አማራ ተደራጅ፤ ይህ ሰልፍ የመጨረሻችን ነው፤ ከእንግዲህ ወዲያ ሰልፍ ሳይሆን ሰይፍ ይዘን እንነሳለን›› የሚሉ መፈክሮች ተስተጋብተዋል፡፡

የተቃውሞ ሰልፉ ታዳሚዎች፣ ልሙጡን የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ያነገቡ ሲሆን፣ በኦሮሚያና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ማንነትን መሠረት ባደረገ መልኩ ለተገደሉ የአማራ ተወላጆች ሀዘናቸውን ለመግለጽ ጥቁር ጨርቅ ይዘውና ጥቁር ልብስ ለብሰው የተሰለፉም ነበሩ፡፡

በዛሬው ምሽትም፣ በአደባባይ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን በግፍ ለተገደሉት ሰዎች የሻማ ማብራት ሥነ ስርዓት እንደሚከናወን የተገለጸ ሲሆን፣ ቅዳሜ ሚያዚያ 16 ቀን 2013 ዓ.ም መላው የጎንደር ህዝብ እና የአዘዞ ህዝብ በሙሉ መስቀል አደባባይ ለመገናኘት ቃል ተገባብተዋል፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር ትላንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ በክልሉ ልዩ ልዩ ከተሞች የተካሄዱ ሰልፎች አግባብ እንዳላቸው ገልጸው፣ በተወሰነ ቦታ ላይ ግን ተገቢ ያልሆኑ መፈክሮች ተስተውለዋል፤ ይህም ሰልፉን ከጀርባ ሆነው ለፈለጉት ዓላማ ሊያውሎት የሚፈልጉ ኃይሎች ድርጊት ነው፤ ሆኖም በጎንደር የተስተጋባው ድምጽ በትክክል የአማራን ህዝብ ጥያቄ የሚገልጽ አግባብነት ያለው ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com