ዜና

የሶማሊያ ፓርላማ የፕሬዝደንቱን ስልጣን ለማራዘም ያሳለፈው ውሳኔ እንዳሳሰበው የአፍሪቃ የሰላምና የፀጥታ ም/ቤት አስታወቀ

Views: 42

የሶማሊያ ፓርላማ ያሳለፈው ውሳኔ፣ ምርጫ እንዲደረግ የተደረሰውን ስምምነት የሚጥስ መሆኑን ም/ቤቱ አስታውቋል፤ የሶማሊያ ፖለቲከኞች ውጥረትን ከሚያባብሱ ተግባራት በመቆጠብ ለውይይት እንዲቀመጡም ም/ቤቱ አሳስቧል፡፡

የሶማሊያ የፖለቲካ መሪዎች በሀገሪቱ ውጥረትን ከሚያባብሱ ተግባራት በመቆጠብ በአስቸኳይ ወደ ውይይት እንዲመለሱ የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ።

የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት በሶማሊያ ባለው ወቅታዊ የፖለቲካ እና ፀጥታ ሁኔታ ዙሪያ በትናትናው እለት ውይይት ማደረጉን አስታውቋል።

ምክር ቤቱ ከውውይይቱ በኋላ ባወጣው መግለጫ፣ የሶማሊያ ፓርላማ ከ10 ቀናት በፊት ባደረገው ስብስባ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎችን ባገለለ መልኩ የሀገሪቱን ፕሬዝደንት እና የፓርላማውን የስልጣን ቆይታ ጊዜ ለማራዘም ያሳለፈው ውሳኔ እንዳሳሰበው አስታውቋል።

የሶማሊያ ፓርላማ ያሳለፈው ውሳኔም በአውሮፓውያኑ መስከረም 2020 የሀገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች ምርጫ እንዲደረግ የደረሱትን ስምምነት የሚጥስ መሆኑንም አስታውቋል።

ውሳኔውም በሶማሊያ ከፍተኛ መስዋእትነት በመክፈል የተገኘችውን አንጻራዊ ሰላምና ፀጥታን አደጋ ላይየሚጥል መሆኑን እና የሀገሪቱን አንድነትና መረጋጋት እንዲሁም አዲስ የተጀመረውን ዴሞክራሲያዊ እና ሕገ-መንግስታዊ ሂደቶች የሚጎዳ ነው ሲል አህጉራዊው የሰላምና ፀጥታ ም/ቤት ስጋቱን አስቀምጧል።

በተጨማሪም አሁን ያለው የፖለቲካ ሁኔታ የሶማሊያ ፌዴሬሽን እና የሀገሪቱን የፀጥታ አካላት አንድነትን ሊጎዳ ይችላል ያለው ምክር ቤቱ፣ አልሸባብን ለማዳከም የሚሰራውን ስራም ሊያስተጓጉል እንደሚችል አሳስቧል።

የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት ስብሰባውን ተከትሎ ባወጣው መግለጫም የሶማሊያ የፖለቲካ ኃይሎች በመስከረም 2020 ስምምነት እና በባይዳዋ የቴክኒክ ኮሚቴ ምክሮች ላይ በመመርኮዝ ለሀገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት በአፋጣኝ ወደ ውይይት እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቧል።

ሁሉም የሶማሊያ የፖለቲካ ኃይሎች ሀገራቸውን፣ የአፍሪካ ቀንድ እና አህጉሪቱን ወደ ቀውስ ሊያስገቡ ከሚችሉ ውጥረትን የሚያባብሱ ተግባራት እንዲቆጠቡም ነው ያሳሰበው።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ከሶማሊያ ባለስልጣናት እና ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎቻ ጋር በቅርበት የሚሰራ ልዩ መልእከተኛ በአስቸኳይ ወደ ስፍራው እንዲልኩ የጠየቀው ምክር ቤቱ፤ አሚሶም፣ ኢጋድ እና ሌሎች ቀጠናዊ አካላትም የድርሻቸውን ኢንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com