ዜና

ፈረንሳይ በቻድ የተቋቋመውን ወታደራዊ የሽግግር መንግስት እንደምትደግፍ አስታወቀች

Views: 51

የሟቹ የቻድ ፕሬዚዳንት እድሪስ ዴቢይ ልጅ ጄነራል ማሃማት እድሪስ ዴቢ የፕሬዚዳንትነት ስልጣንን መያዛቸው ይታወሳል፡፡ ፈረንሳይ የፕሬዚዳንትነት ስልጣንን ከአባት ወደ ልጅ ለማስተላለፍ ያደረገችው መፈንቅለ መንግስት ነው- ተቃዋሚ ኃይሎች፡፡

የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዛሬው እለት እንዳስታወቀው የቻድ ጦር ስልጣኑን መያዙ በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋትን ከመፍጠር አንጻር ተቀባይነት አለው።

የቻድ ፕሬዚዳንት እድሪስ ዴቢይ መገደላቸውን ተከትሎ ልጃቸው ጄነራል ማሃማት እድሪስ ዴቢ የፕሬዚዳንትነት እና የአገሪቱን ጦር መሪነት ስልጣንን መቆጣጠራቸው ይታወሳል።

በሀገሪቱ ሕገ መንግስት ግን ሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ከስልጣን በሚነሱበት ጊዜ የሀገሪቱ ብሄራዊ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት በመሆን ስልጣን እንደሚይዙ ያመላክታል።

ሆኖም ግን፣ የሀገሪቱ ብሄራዊ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ሃሩን ካባዲ በሰጡት መግለጫ ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ሀገሪቱን በመምራቱ መስማማታቸውን አስታውቀዋል።

የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዢያን ያቭሰ ሊ ዳረንም የቻድ ብሄራዊ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ሀሩን ካባዲ የሰጡት መግለጫ ጦሩ ሀገሪቱን እንዲመራ የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

በሀገሪቱ ሕግ መሰረት የፕሬዚዳንትነት ስልጣኑን መያዝ የነበረባቸው የብሄራዊ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ሃሩን ካባዲ ነበሩ ያሉት የፈረንሳይዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት ነው የቻድ ጦር በልዩ ሁኔታ ስልጣኑን የያዘው ብለዋል።

የቻድ ተቃዋሚ ኃይሎች የሀገሪቱ ጦር ስልጣኑን መያዙን የተቃወሙ ሲሆን፤ ተግባሩም ፈረንሳይ የፕሬዚዳንትነት ስልጣንን ከአባት ወደ ልጅ ለማስተላለፍ ያደረገችው መፈንቅለ መንግስተ ነው ሲሉም አስታውቀዋል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com