የፀጥታው ም/ቤት አባላት በትግራይ ክልል የኢትዮጵያ መንግስት እያከናወነ ያለውን የሰብዓዊ ድጋፍ አደነቁ

Views: 42

የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ም/ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ አውጥቷል፤ የም/ቤቱ አባላት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፣ የፖለቲካ ነፃነት እና የግዛት አንድነት ያላቸውን ጠንካራ ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በክልሉ ላለው ቀውስ እልባት ለመስጠት የኢትዮጵያ መንግስት እያከናወነ ያለውን ተግባር አድንቋል፡፡

መግለጫው እንደሚለው፣ የፀጥታው ም/ቤት አባላት የኢትዮጵያ መንግስት ሰብዓዊ ዕርዳታን ለማቅረብ እና ሰብዓዊ ተደራሽነትን ከፍ ለማድረግ እያደረገ ላለው ጥረት እውቅና ሰጥተዋል፡፡

ይሁንና የም/ቤቱ አባላት የሰብዓዊ ችግሮች አሁንም መኖራቸውን እንደሚገነዘቡ እና በክልሉ ያለው ሰብዓዊ ሁኔታ እንደሚያሳስባቸውም ነው መግለጫው ያመለከተው፡፡

ከምግብ ዋስትና ጋር በተያያዘም የሚደረገው የሰብዓዊ ድጋፍ መጨመር እንዳለበት እና ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ ለሁሉም የተቸገሩ ወገኖች ተደራሽ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ አስቸኳይ እርዳታ መርሆዎች ጋር በሚጣጣም መልኩ ሰብዓዊነትን፣ ገለልተኛነትን እና ነፃነትን መሰረት በማድረግ የሚከናወኑ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦቶችእንዲቀጥሉ የፀጥታው ም/ቤት አባላት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በትግራይ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር ለቀጣይ የሰብአዊ አገልግሎቶች እንቅፋት መሆኑን በመግለጽ መደበኛ ሁኔታው እንዲመለስም አባላቱ መጠየቃቸው በመግለጫው ተካቷል፡፡

በትግራይ ክልል በሴቶች ላይ የፆታ ጥቃት እንደሚፈጸም የሚያመለክቱ ሪፖርቶችን ጨምሮ በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና በደሎች ላይ የተሰማቸውን ጥልቅ ስጋት በመግለፅ፣ ምርመራ ተደርጎ ጥፋተኞች ለህግ እንዲቀርቡም ነው የፀጥታው ም/ቤት አባላት የጠየቁት፡፡

የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና በደሎች ላይ የሚያካሂዱትን የጋራ ምርመራ በአድናቆት ተቀብለዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የአፍሪካ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ተሳትፎም የፀጥታው ም/ቤት አባላት በአድናቆት መቀበላቸው ተገልጿል፡፡ ዓለም አቀፍ ህግን ሙሉ በሙሉ ማክበር አስፈላጊ መሆኑንም አባላቱ አሳስበዋል፡፡

የም/ቤቱ አባላት ለአህጉራዊ እና ለክፍለ-አህጉራዊ ጥረቶች እና ድርጅቶች ማለትም ለአፍሪካ ሕብረት እና ለኢጋድ ያላቸውን ጠንካራ ድጋፍ የገለጹ ሲሆን፣ የድርጅቶቹ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስምረውበታል፡፡

የፀጥታው ም/ቤት አባላት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፣ የፖለቲካ ነፃነት፣ የግዛት አንድነት እና አንድነት ያላቸውን ጠንካራ ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com