ዜና

የአውሮፓ ሕብረት የምርጫ ታዛቢዎችን ወደ ኢትዮጵያ ሊልክ ነው

Views: 42
– ሕብረቱ በታዛቢዎች ጉዳይ በሚቀጥሉት ሳምንታት የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጥ ተገልጿል!
– አቶ ደመቀ መኮንን ከአውሮፓ ሕብረት የአደጋ ጊዜ አስተዳደር ኮሚሽነር ጄንዝ ሌናር ጋር ተወያዩ!

የአውሮፓ ሕብረት በግንቦት ወር የሚካሔደውን የኢትዮጵያን ምርጫ ለመታዘብ የምርጫ ታዛቢ ልዑክ ሊልክ በመዘጋጀት ላይ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የሕብረቱ የውጭ ጉዳይ ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፕ ቦሬል ከአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር በቪዲዮ ኮንፈረንስ ከተወያዩ በኋላ በሰጡት አስተያየት ፣ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ “ይበልጥ ካልተባባሰ በስተቀር” የአውሮፓ ሕብረት የምርጫ ታዛቢዎች ይላካሉ ብለዋል፡፡ በሚቀጥሉት ሳምንታት የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጥም አክለው ገልጸዋል፡፡
በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከአውሮፓ ሕብረት የአደጋ ጊዜ አስተዳደር ኮሚሽነር ያኔዝ ሌናርቺችን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ እስካሁን መንግስት እያከናወናቸው ባሉ ጥረቶች እና በክልሉ ለተጎዱ ወገኖች የሰብዓዊ ድጋፍን ለማድረስ የተስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለማቃለል መከናወን ባለባቸው ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡
ኮሚሽነሩ ያኔዝ ሌናርቺች ፣ በክልሉ የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነት መሻሻሉን ያደነቁ ሲሆን የግጭቱ መቀጠል አንዳንድ የገጠር አካባቢዎች ለሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዳይሆኑ ማድረጉን ስለማንሳታቸውም ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው፡፡
አምባሳደር ሌናርቺች ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግስታት በክልሉ ውስጥ ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በጋራ ለማጣራት ያደረጉትን ስምምነት አድንቀዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው መንግስት ብዙ ችግሮችን በመቋቋምና ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ፣ በትግራይ የዜጎችን ህይወት ለማሻሻል እስካሁን ድረስ የሚያስመሰግኑ ተግባራትን መፈጸሙን እና መሻሻሎችም መኖራቸውን አብራርተዋል፡፡
ይሁንና የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፕ ቦሬል ፣ የምርጫ ታዛቢዎችን ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ ስለሚደረገው ዝግጅት አስተያየት በሰጡበት ወቅት ባደረጉት ንግግር በትግራይ ያለው “መሻሻል ውስን ነው” ሲሉ ገልፀዋል፡፡
Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com