ዜና

ዩኒቨርሲቲው ከአሸባሪዎች ጋር በማበር አገር ለማፍረስ የሚያሴሩ ምሁራንን አስጠነቀቀ

Views: 74
ህዳር 17/2014  የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ጊዜያት የተመረቁና በመላው ዓለም የሚገኙ፤ አገር ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ አሸባሪዎችን የሚደግፉ ምሁራን ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አስጠነቀቀ።
የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ወቅታዊውን አገራዊ ጉዳይና የህልውና ዘመቻውን አስመልክቶ የአቋም መግለጫ አውጥቷል።
ባወጣው ባለ ዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ “ጥቂት ግለሰቦች የዩኒቨርሲቲውንና የአገር ውለታ ክደው ከአገር አፍራሽ ሽብርተኞች ጋር ሲተባበሩና በአገር ላይ ክህደት በመፈፀም በምስጢር ሲያሴሩ ተደርሶባቸዋል” ሲል አመልክቷል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ከዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ጊዜያት ተመርቀው በመላው ዓለም የሚገኙና የሽብር ቡድኑን የሚደግፉ ምሁራን ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል ብለዋል።
ከድርጊታቸው በማይቆጠቡት ላይ የዩኒቨርሲቲው ሕግ እስከሚፈቅደው ድረስ በመሄድ ሕጋዊ እርምጃ የሚወስድ መሆኑንም አስታወቀዋል።
በሌላ በኩል የዩኒቨርሲቲው የቀድሞም ይሁን የአሁን ምሩቃን “የጀመራችሁትን አገር የማዳን ትግል አጠናክራችሁ መቀጠል አለባችሁ” ብለዋል ፕሮፌሰር ጣሰው።
የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ የአቋም መግለጫ በተጨማሪም አሸባሪውን የህወሓት ቡድን በግልጽ የሚደግፉት አሜሪካና አንዳንድ የአውሮፓ አገራት ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አመልክቷል።
ዩኒቨርሲቲው ምዕራባዊያን በኢትዮጵያ ላይ የያዙትን የተዛባ ግምገማና አላስፈላጊ የውስጥ ጣልቃገብነት በፅኑ ያወግዛል ሲልም አትቷል።
ዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ በእጅ አዙር ቅኝ ግዛት፣በአድሏዊ ማዕቀብና በሽብርተኝነት ላይ ጠንካራ ተቃውሞውን እንዲያሰማና ከእኛ ጋር በጋራ እንዲቆም ጥሪ እናቀርባለንም ብሏል።
የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አባላት የህልውና ዘመቻውን ከግብ ለማድረስ የመንግስትን ጥሪ ተቀብለን አስፈላጊ ከሆነ ግንባር ድረስ ለመዝመት ዝግጁ ነን ማለታቸውም በአቋም መግለጫው ተጠቅሷል።
Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com