ዜና

የቀድሞው የብራዚል የኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት 30 ዓመት ተፈረደባቸው

Views: 58

ሪዮ ዲጄኔይሮ የ2016ቱን የኦሎምፒክ ውድድር እንድታስተናግድ የድጋፍ ድምጾችን በገንዘብ ገዝተዋል በሚል የተከሰሱት የቀድሞው የብራዚል የኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ካርሎስ አርተር ኑዝማን 30 ዓመት ከ11 ወር ተፈረደባቸው፡፡

የብራዚል ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ሆነው ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል ያገለገሉት ኑዝማን ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ጨምሮ ሌሎች ከሙስና የተያያዙ ወንጀሎችን ፈጽመዋል ተብሏል፡፡

የ2016ቱ የሪዮ ኦሎምፒክ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ የነበሩት አዛውንቱ ኑዝማን ግብርን ይሰውሩ እንደነበር ፍርዱን የሰጠው ፍርድ ቤት ዳኛ ተናግረዋል፡፡

ዳኛው ማርሴሎ ብሬታስ ኑዝማንንን ጨምሮ የአዘጋጅ ኮሚቴው አባል የነበሩት የወቅቱ የሪዮ ዲጄኔይሮ ከንቲባ እንዲሁም አንድ ሌላ ነጋዴ ላይ የእስር ትዕዛዝን አስተላልፈዋል፡፡

በእስር ላይ የሚገኙት ከንቲባው ከአሁን ቀደም ስድስት የድጋፍ ድምጾችን ለማግኘት 2 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መክፈላቸውን ተናግረዋል፡፡

30 ዓመት ከ11 ወር የተፈረደባቸው የ79 ዓመቱ አዛውንት ኑዝማን ግን በውሳኔው ላይ አቤት ሊሉ እንደሚችሉና ላይታሰሩ እንደሚችሉም የአሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ ያመለክታል፡፡

ብራዚል ሺካጎን፣ ቶኪዮን እና ማድሪድን አሸንፋ የኦሎምፒክ ውድድሩን ማስተናገዷ ይታወሳል፡፡ሆኖም በዴንማርክ ኮፐንሃገን በነበረው የአዘጋጆች ምርጫ የኦሎምፒክ ኮሚቴ አባላት ብራዚልን ለመምረጥ ጉቦ ተቀብለዋል በሚል በተለያዩ ዓለም አቀፍ ብዙሃን መገናኛዎች ሲዘገብ እንደነበር ይታወሳል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com