ዜና

የኢትዮጵያ የውጭ ጫናውን አሸንፎ መውጣት ለአፍሪካም ማሸነፍ ነው

Views: 77
ህዳር 16 ቀን 2014 ኢትዮጵያ አሁን የተከፈተባትን የውጭ ጫና አሸንፎ መውጣት ለአፍሪካም ጭምር ማሸነፍ እንደሆነ መገንዘብ እንደሚያስፈልግ የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት ዶክተር ምህረት ደበበ ገለጹ፡፡
በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያውያን ትልቅ እና ታሪካዊ ጊዜ ላይ ነን ፤ አፍሪካውያን ከጎናችን እንደሚቆሙ እያሳዩን ነው ፤ ስለሆነም ጦርነቱን ከማሸነፍ ውጪ ሌላ ምርጫ የለንም ብለዋል፡፡
በታሪካችን ኢትዮጵያ ብቻዋን ነፃነቷን አስከብራ ሌሎችንም ወደ ነፃነት ስትመራ ይሄ ሁለተኛው የነፃነት ጥሪ መሆኑን ጠቁመው  ይሄንን ጦርነት በማሸነፍ የአሁኑ ትውልድ ታሪክ መጻፍ እንዳለበትም ነው የገለጹት፡፡
ምዕራባውያን የአፍሪካን አገራት እንደ አገር ማየት እና ማክበር አይፈልጉም ያሉት ፕሬዚዳንቱ  ኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ውስጥ ያልገባች በአጭር ጊዜ ውስጥም ቢሆን በጣልያን ወረራ አባቶቻችን እጅ ሳይሰጡ የኢትዮጵያን ነፃነት እንዳስጠበቁ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያን ትልቅ እናደርጋታለን ብለው ዜጎቿ ሲነሱ ምዕራባውያን ደግሞ እንዳንሆን በአሁኑ ወቅት ተነስተውብናል ብለዋል፡፡
ይህንን እንዳይሳካ ለማድረግ እንደ ሁነኛ መሣሪያ ሆኖ ያገኙት በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት እንደሆነ ጠቅሰው የአሸባሪውን ህወሓት ኃይል ለዚህ መጠቀሚያ ስለማድረጋቸውም ነው ያነሱት፡፡
በግብጽና በሱዳን በኩልም በዓባይ ዙሪያ ያለው ፍላጎት ቀላል እንዳልሆነ ማንሳታቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡
ስለሆነም በጦር መሣሪያ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሰው የአገሩ አምባሳደር መሆን ይጠበቅበታልም ነው ያሉት፡፡
አሸናፊነት ከድል በኋላ የሚመጣ አይደለም የሚሉት ዶክተር ምህረት  ሰው ሳይዋጋ በፊት የአሸናፊነት ሥነ ልቦና ሊላበስ ይገባልም ብለዋል፡፡
ጦርነቱን ቀላልና በአገር ውስጥ የተለያየ እይታ ያላቸው የአንድ አገር ሰዎች እየተዋጉ እንዳሉ አድርጎ ማሰብ አያስፈልግም፡፡
ይልቁንም የምዕራባውያን ትልቅ እጅ ያረፈበት እጅግ ውስብስብ ጦርነት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
አገር ከገባችበት እንድትወጣ ጦርነቱን አቅልሎ አለማየትና የኔ ነው ብሎ በመነሳት ሁሉም የሚችለውን ርብርብ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል።
ለዚህ ቆራጥ በመሆን እኛ ባንጠቀም ቀጣዩ ትውልድ ይጠቀማል ብሎ መነሳት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡
በተሳሳተ አቅጣጫ ያሉ ኢትዮጵያውያንም መንቃት እንዳለባቸው ያነሱት ዶክተር ምህረት ÷ ምን እያደረጉ እንዳሉና መጨረሻ ላይ ማግኘት የሚፈልጉት ነገር ምን እንደሆነ በማወቅ አገራቸውን ከማፍረስ እንዲመለሱ ዶክተር ምህረት መክረዋል፡፡
Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com