ዜና

ቡና-ሻይ ከቡና ቅጠል

Views: 271

መነሻ

የቡና ተክል መገኛ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ቡና ፍሬው ተቆልቶ ተወቅጦ ተፈልቶ፤ በመላው ዓለም ተወዳጅ፣ አልኮል አልባ፣ አነቃቂ መጠጥ ነው፡፡ የቡናን ፍሬ በትንሽ ብረት ምጣድ ወይም ሸክላ ምጣድ ቆልቶ፣ በትንሽ ቡና ሙቀጫ ወቅጦ፣ በትንሽ ጀበና ማፍላት፣ በስኒ መጠጣት የኖረ፣ እስከ ዛሬም ያለ ልማዳችን ነው፡፡ እኛ የቡና መገኛ ተብዬዎቹ ዛሬም ቡናችን እንዲህ ይፈላል፣ እንዲህ ይጠጣል፡፡ አውሮፓዎች ቡናን የሚቆላ፣ የሚወቅጥ፣ የሚያፈላ ማሽን፤ ስንት እና ስንት ዓይነት ተራቀውበታል፡፡ እነዚህ እነሱ በረቂቅ ጥበብ ከሠሩት ውስጥ በእኛም አገር ተገዝተው ቀርበው ሥራ ላይ ይገኛሉ፡፡

የቡና ፍሬን መጠጥነት ሁሉም ያውቀዋል፡፡ ነገር ግን የቡና ቅጠል እንደሻይ ተፈልቶ ጠቀሜታው ከፍ ያለ ቢሆን ከፍ ያለ ጥናት አልተሠራም፤ የጎላ ወሬ አልተወሳም፡፡ የቡና ቅጠል ከቡና ፍሬ የበለጠ ጥቅም ቢኖረው ማን አወቀ?

ከቡና ቅጠል ቡና-ሻይ

ሻይ እና ቡና በሁሉም ቦታ ተወዳጅ ትኩስ መጠጥ ናቸው፡፡ ሻይ እና ቡና መገኛ ተክሉ የተለያዩ ሲሆኑ፤ ድንበር አላቸው፡፡ ሻይም ሻይ ነው፡፡ ቡናም ቡና ነው፡፡ ሻይ እንደ ቡና ሆኖ ሊፈላ አይችልም፡፡ ነገር ግን ቡና ድንበር አልፎ እንደ ሻይ ሆኖ ተፈልቶ ይጠጣል፡፡ የቡና ቅጠሉ ቡና-ሻይ ሆነ ማለት እንዲህ ነው፡፡

ሀ)  ቡና-ሻይ ቅጠል ለግብይት

በአገረ ጣሊያን ፓርማ የሚገኘው፤ የአውሮፓ ምግብ ደህንነት ባለስልጣን፤ The European Food Safety Authority (EFSA)  በ2ዐ15 እ.ኤ.አ፤  የቡና ቅጠል ሻይ በአውሮፓ ህብረት ገበያ ላይ፤ እንደ ባሕላዊ ምግብ ሆኖ እንዲቀርብ ደንብ ተቀርፆለት ፍቃድ ሰጠ የሚለን ዓለም አቀፍ ኮሚኒካፌ ዶት ኮም ነው፡፡  https://www.comunicaffe.com/efsa-gives-go-ahead-for-coffee-leaf-tea-as-traditional-food-from-third-country/

በዚሁ መረጃ መረብ ላይ፣ በ2ዐ12 እ.ኤ.አ የፈረንሳይ እና ኢንግሊዝ አገር ተመራማሪዎች፤ የቡና ቅጠል ከፍተኛ ጥርቅም ክሎሮጀኒክ አሲድ፣ (chlorogenic acid)፤ እና አንቲኦክሲደንት (an antioxidant) እንዳለው ማረጋገጣቸውን ነው፡፡  የአንቲኦክሲደንቱ ዓይነት የቡና ፍሬም ውስጥ የሚገኝ ነገር ግን የሻይ ቅጠል ውስጥ ካለው የተለየ መሆኑም ተነግሯል፡፡  በተለይም ኮፊ አራቢካ  ማለትም የኢትዮጵያ ቡና ቅጠል ከፍተኛ መጠን ማንጊፈሪን (mangiferin,)   የተባለ ፓይቶኬሚካል አለው፡፡ ማንጊፈሪን ቀደምት መገኛ የማንጐ ፍራፍሬ ነው፡፡

ለ) ቡና-ሻይ ቅጠል የጤና ጠቀሜታው

ፓይቶኬሚካል ለልብ ጤና ይጠቅማል፤ ብግነትን ያበርዳል፤ ልብን ከበሽታ ይከላከላል፤ ካንሰርን ይከላከላል፡፡ ብሎ የሚነግረን ይኸው ኮሚኒካፌ ዶት ኮም ነው፡፡ በይበልጥም አንብቡ፡፡

ሐ) እርጥብ የቡና ቅጠል ሲፈላ

እርጥብ የቡና ቅጠል ምስል

እራሱ እርጥቡ የቡና ቅጠል ሲፈላ ቀለሙ እንዲህ ነው፡፡

መ) ቁጢ የቡና ቅጠል

በሐረርጌ፣ በድሬዳዋ በእነዚህ ሁሉ አካባቢ የደረቀው የቡና ቅጠል፣ ቁጢ ተብሎ ተፈልቶ ይጠጣል፡፡ ቁጢ የሚለቀመው ከቡና ዛፍ ላይ ደርቆ፣ ወይቦ የረገፈው ደረቅ ቅጠል ነው፡፡ ይህ እንዲህ ወይቦ ወይም ዳለቻ ቢጫ መልክ ያለው የቡና ቅጠል፤ ልከ እንደ አረንጓዴው የቡና ቅጠል የተባለውን የጤና በረከት ይኖረው እንደሆን ሌላ ጥናት ያስፈልገዋል፡፡

ሠ) ጨሞ የቡና ቅጠል ሻይ፣

እርጥቡ የቡና ቅጠል ከተለያዩ ቅመማት ጋር ተደቆሶ የሚፈላ እርጥብ የቡና ቅጠል ሻይ ነው፡፡ ይህም የተቀመመው የቡና ቅጠል ሻይ ከፍተኛ የጤና ጠቀሜታ እንዳለው በደቡብ እና ምዕራም የኢትዮጵያ አካባቢዎች በሕዝብ እውቀት የተመሠከረ ጉዳይ ነው፡፡ ስለ አዘገጃጀቱ በዚሁ አምድ https://ethio-online.com/archives/5306     “ጨሞ ሀገራዊ ሻይ ለጉንፋን”  በሚል ርዕስ ላይ ያለውን አንብቡ፡፡

ማጠቃለያ

አገራችን ከፍተኛ የቡና እርሻ አላት፡፡ ከዚህ ሞልቶ ከተረፈው ላይ፤ የቡና ቅጠሉ በእርጥቡ ተለቅሞ በአግባቡ ተዘጋጅቶ ለአገር ውስጥ እና ለውጪ ገበያ እንዲቀርብ ሁሉም የድርሻውን ይወጣ፡፡ አውሮፓ ይቅረብልኝ ያለው የቡና ቅጠል እስከዛሬም የሚቀርበው ከሌሎች አገራት እንጂ ከእኛ አገር አይመስለኝም፡፡ በዚህ ላይ ተጨማሪ ምክረ ሐሳብ ያላችሁ ምክራችሁን ለግሱ፡፡ የቡና እና ሻይ ልማት ባለሥልጣን ይህ መልዕክት እንዲደርሰው ላኩለት፡፡    መልካም ንባብ፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com