ዜና

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዲጂታል የተጓዥ ይለፍ መተግበሪያ ስራ ላይ ሊያውል ነው

Views: 105

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዓለም ዓቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር (አይኤቲኤ) ጋር በመተባበር ዲጂታል የተጓዥ ይለፍ የሞባይል መተግበሪያ በሙከራ ደረጃ ስራ ላይ ሊያውል መሆኑን ትራቭል ዴይሊ ኒውስ ዘገበ።

የሞባይል መተግበሪያው የአየር መንገዱ ተጓዥ ደንበኞች ስለ ኮቪድ-19 ምርመራና ክትባትን የተመለከተ ውጤታማ ስራ ለመስራት የሚያስችለው እንደሆነ ተገልጿል።

አየር መንገዱ ርቀትን በትክክል የጠበቀ የመረጃ አቅርቦትን ለመተግበር የሚያግዘው እንደሚሆንም ዘገባው አመልክቷል።

መተግበሪያው ማንኛውም ደንበኛ ወደ አገር ውስጥ ለመግባት የኮቪድ-19 ፕሮቶኮል መመሪያን በሚያሟላ መልኩ አገልሎት የሚሰጥ መሆኑን የጋዜጣው ዘገባ አመላክቷል፡፡

መተግበሪያው የጉዞ ዲጂታል የይለፍ ወረቀት፣ የምርመራ እና የክትባት ወረቀትየተመለኩቱ መረጃዎችን ለማቅረብ የሚረዳ መሆኑን ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም እንደገለጹት፤ አየር መንገዱ አጠቃላይ አሰራሩን ወደዲጂታል ለመቀየር እየሰራ ይገኛል።

አሰራሩን ሙሉ ለሙሉ ወደ ዲጅታል ሲቀይር የደንበኞች የኮቪዲ-19 ተጋላጭነትን ለማስቀረት እንደሚያስችል አስረድተዋል፡፡

“የዲጂታል ቴክኖሎጂ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያመጣቸውን ችግሮች ለመፍታት እጅግ ወሳኝ ነው” ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ይህንን የሞባይል መተግበሪያ ለተጓዦች ጥሩ እድል መሆኑን ገልጸዋል።

“ደንበኞቻችን ውጤታማ፣ ከንክኪ ነጻ የሆነና ምቹ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል” ብለዋል።

የአይኤቲኤ ዋና ዳይሬክተር አሌክሳንደር ደ ጁናይክ በበኩላቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ መተግበሪያውን ስራ ላይ በማዋል የኮቪድ-19 ምርመራ ውጤትንና የክትባት ወረቀትን በመቆጣጠር ረገድ የሚሰራውን ስራ በመደገፍ መሰረት ያስቀመጠ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com