ዜና

የህዳሴ ግድብ ውሃ የሚተኛበት ስፍራ ሁለተኛው ዙር የደን ምንጣሮ ሊካሄድ ነው

Views: 107

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴው ግድብ ውሃ የሚተኛበት ስፍራ ሁለተኛ ዙር የደን ምንጣሮ ሊካሄድ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቴክኒክ እና ሙያ ስራ እድል ፈጠራ ኤጀንሲ ገለጸ፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ በሽር አብዱራሂም ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ሁለተኛውን ዙር የህዳሴውን ግድብ ውሃ ሙሌት ለማከናወን ውሃ የሚተኛበት ቦታ 4 ሺህ 854 ሄክታር ደን ይሸፍናል።
የውሃው መጠንም ከመጀመሪያው ዙር በአራት እጥፍ ከፍ እንደሚል ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ኤጀንሲው የደን ምንጣሮውን ለማከናወን በተገባደደው ሳምንት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ጋር ስምምነት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

በስምምነቱ መሰረት ወጪው ከ81 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡
ምንጣሮውን ለማከናወን ከክልሉ ሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ ከአምስት ሺህ በላይ ስራ አጥ ወጣቶች ካቀፉ 500 ኢንተርፕራይዞች ጋር ኤጀንሲው ውል እየገባ መሆኑንና ይህም በሳምንት እንደሚጠናቀቅ አመልክተዋል፡፡

ለስራው ወጪ ከሚሆነው ሀንዘብ ውስጥ 20 በመቶ ቅድመ ክፍያ በቅርቡ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል እንደሚለቀቅ የሚጠበቅ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የደን ምንጣሮ ስራውን በአንድ ወር ጊዜ ለማጠናቀቅ መታቀዱን አቶ በሽር ገልጸዋል፡፡

ውሃው በሚተኛበት ከግድቡ ግራ እና ቀኝ የሚገኙ ሸርቆሌ፣ ጉባ፣ ወምበራ እና ሰዳል ወረዳዎች የምንጣሮውን ስራ 40 በመቶ እንዲያከናውኑ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ቀሪው 60 በመቶ የምንጣሮ ስራ ደግሞ ለሌሎች የክልሉ ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች መከፋሉን አብራርተዋል፡፡

እያንዳንዱ ኢንተርፕራይዝ ዝቅተኛ 10 ሄክታር ከፍተኛው ደግሞ 20 ሄክታር ደን ተረክበው ምንጣሮ እንደሚያከናውኑ ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

የደን ምንጣሮው በ”ጂፒኤስ ቴክኖሎጂ” በመታገዝ እንደሚከናወን ጠቁመዋል፡፡
የመተከል ጸጥታ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ መሻሻል እያሳየ እንደመጣ የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ የምንጣሮ ስራው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚመራው የዞኑ ኮማንድ ፖስት ጋር በቅርበት እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ወረዳዎች በተቀመጠላቸው ጊዜ ስራውን በጥንቃቄ እንዲያከናውኑ ስምምነት ከተገባ ጊዜ ጀምሮ በቁርጠኝት ክትትል ማድረግ እንደጀመረ ተናግረዋል፡፡

የህዳሴ ግድብ ከደህነት ለመውጣት ወሳኝ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ በሽር የኢትዮጵያ ህዝብ ይህን በጥልቀት በመረዳት በራሱ ወጪ የግድቡን ግንባታ እንደሚጨርስ እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የክልሉ ህዝብም የግድቡ ሠላም የመጠበቅ የቅርብ ሃላፊነት እንዳለበት አመልክተው የግድቡን አካባቢ ደህንነት እንዲጠናከር ድጋፉን እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የደን ምንጣሮ ሰውን ለማከናወን ከኤጀንሲው ጋር ውል ከገቡት ኢንተርፕራይዞች መካከል ሲቱ እና ጓደኞቹ ኢንተርፕራይዝ ማህበር አባል ወጣት ሲቱ አደራ በሰጠችው አስተያየት ከ12 የማህበሩ አባላት መካከል አብዛኞቹ ሴቶች መሆናቸውን ትናገራለች፡፡

‹‹የደን ምንጣሮ ለማከናወን እድል በማግኘታችን በእጅጉ ደስተኞች ነን፤ ከገንዘቡ በላይ ለህዳሴው ግድብ አሻራችንን ማስቀመጣችን ትልቅ ነገር ነው›› ብላለች፡፡
የግድቡ አካባቢ ከፍተኛ የአየር ሙቀት እና ሌሎችም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩትም ሁሉም የማህበሩ አባላት የደን ምንጣሮ ስራውን ለመጀመር በጉጉት እየተጠባቡ መሆኑን ገልጻለች፡፡

ኢንተርፕራይጁ በመጀመሪያ ዙር የግድቡ ውሃ ሙሌት አስቀድሞ በስፍራው የሚገኝ ከአንድ ሺህ ሄክታር በላይ ደን ምንጣሮ ስራ ማከናወኑን በወቅቱ ተገልጿል፡፡

የሀገሪቱ መንግሥት ህዝቡን ከድህነት ለማውጣት ከሚያከናውናቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ አንዱ ነው።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com