ዜና

የፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ ድልድል ይፋ ሆነ

Views: 83

በስድስተኛው አጠቃላይ አገራዊ ምርጫ ለሚፎካከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመገናኛ ብዙሃን የምርጫ ቅስቀሳ የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ ድልድል ይፋ ሆነ።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ጋር በመተባበር ”በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀምና ድልድል መመሪያ” እንዲሁም ”የመገናኛ ብዙሃንና የጋዜጠኞች የምርጫ አዘጋገብ የስነ-ምግባርና የአሰራር መመሪያ” ዙሪያ ውይይት አድርጓል።

በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሚፎካከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመገናኛ ብዙሃን የምርጫ ቅስቀሳ የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ ድልድል በብሮድካስት ባለስልጣን በኩል ይፋ ተደርጓል።

በዚህም 700 የሬዲዮ ሰዓት፣ 400 የቴሌቪዥን ሰዓት እና 600 የጋዜጣ አምድ ድልድል መደረጉ ተገልጿል።

በድልድሉ መሰረት 25 በመቶ ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እኩል የሚከፋፈል ሲሆን 40 በመቶ ባቀረቡት የእጩዎች ብዛት መሰረት ይሆናል።

እንዲሁም 20 በመቶ ለሴት እጩዎች፣ 10 በመቶ ለአካል ጉዳተኞችና 5 በመቶ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም በነበረው ምርጫ በምክር ቤት በነበራቸው የመቀመጫ ብዛት መሆኑ ተጠቁሟል።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተደለደለላቸውን የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ ከዚህ ወር መጨረሻ ጀምሮ እስከ ግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ.ም የሚጠቀሙበት እንደሆነም ተገልጿል።

በእያንዳንዱ ሚዲያ የተመደበ ሰዓት የመንግስት ሬዲዮ ከሰኞ እስከ አርብ ቀንና ማታ 30፣ 30 ደቂቃ በሳምንት 300 ደቂቃ የሚጠቀሙበት እንደሆነ ተገልጿል።

የመንግስት ወይም የህዝብ ቴሌቪዥን የሚባሉት ኢቲቪ፣ ኦቢኤን፣ አማራ ቲቪ፣ ደቡብና አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከሰኞ እስከ አርብ ቀንና ማታ ለ30 ደቂቃ በሳምንት 300 ደቂቃ አገልግሎቱን ይሰጣሉ ተብሏል።

ሌሎች የክልል ሚዲያዎች ከሰኞ እስከ አርብ ዘወትር ማታ ማታ 30 ደቂቃ በሳምንት 150 ደቂቃ፤ የንግድ ቴሌቪዠን በሳምንት 2 ቀን ዘወትር ማታ ማታ ለ30 ደቂቃ በሳምንት 60 ደቂቃ እንደሆነም ተጠቁሟል።

የመገናኛ በዙሃን ባለስልጣን የንግድ ሚዲያ ክትትል ዳይሬክተር አቶ ደሬሳ ተረፈ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ለዘንድሮ ምርጫ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመገናኛ ብዙሃን የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ ድልድሉን ከቦርዱ ጋር በመሆን እንዳወጡት ገልጸዋል።

የአየር ሰአትና አምድ ድልድሉ የተደረገው በ60 ሚዲያዎች ላይ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ጋዜጣን በተመለከተ አዲስ ዘመን ላይ በሳምንት ሶስት ቀን ስድስት ኮለምን የሚመደብ ሲሆን ሳምንታዊና ወርሃዊ በሆኑት ላይ በሚወጡበት ቀን ላይ ስድስት ኮለምን የሚመደብ እንደሆነ ተገልጿል።

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com