ዜና

ምርጫው ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን የተላበሰ ፉክክርና ትብብር ላይ ሊያተኩር ይገባል  ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

Views: 110

ምርጫው ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን የተላበሰ ፉክክርና ትብብር ላይ ሊያተኩር ይገባል ሲሉ ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተናገሩ። በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በግል የሚወዳደሩት ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ ፓርላማ የመግባት ዕድሉን ቢያገኙ ድምጽ አልባ ባሕላዊ እሴቶች ጎልተው እንዲወጡ ለማድረግ እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ በየትኛውም አካሄድ ለአገሪቷ የሚበጃት “ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ብቻ ነው” ብለዋል።

ተፎካካሪ ፓርቲዎች ምርጫውን ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ ፉክክራቸው በመከባበር ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት።

እያንዳንዱ ተፎካካሪ ፓርቲ ስለ ሌላ ፓርቲ ሲናገር በአክብሮትና ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን በመላበስ ሊሆን አንደሚገባም ተናግረዋል።

በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል ያሉት መሰረታዊ ልዩነቶች ጥቂት ናቸው ያሉት ዲያቆን ዳንኤል፣ ፓርቲዎቹ በጋራና በትብብር የሚሰሩበትን ሁኔታ መፍጠራቸው ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂ አያደርጋቸውም ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጉት የምረጡኝ ቅስቀሳ ዘመቻ በተለየ አቀራረብና ስነ-ምግባር መሆን እንዳለብትም አመልክተዋል።

ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግል ተወዳዳሪ ናቸው።

እንደ እርሳቸው ገለጻ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል መገፋፋት ሲኖር የሃሳብ ልዕልናን የሚያስከብር ገለልተኛ አካል ያስፈልጋል።

ለዚህ ደግሞ እንደ እርሳቸው አይነት የግል ተወዳዳሪዎች ፓርላማ መግባት ወሳኝ ሚና ይጫወታል ባይ ናቸው።

በተለይ ለበርካታ ችግሮች መፍትሄ ያላቸው የኢትዮጵያዊያን ባሕላዊ እሴቶች ትኩረት እንዲያገኙ የግል ተወዳዳሪዎች ሚና የጎላ ይሆናል ብለዋል።

በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ ባሕላዊ እሴቶች ጎልተው እንዲወጡ ማድረግ ለሚስተዋለው ወቅታዊ ችግር ሁነኛ መፍትሄ መሆኑንም አውስተዋል።

ለድምጽ አልባ ባሕላዊ እሴቶች ድምጽ የሚሆን ገለልተኛ አካል ያስፈልጋል ያሉት ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል በግል ተወዳድረው ፓርላማ መግባት ከቻሉ በነዚህ ኢትዮጵያዊ ባሕላዊ እሴቶች ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ምርጫው ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻውን ከመወጣት ባለፈ ባህሉንና እሴቱን ለሚሸረሽሩ ጉዳዮች ጆሮ ባለመስጠት እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com