ዜና

በግጭቱ ተዘግቶ የነበረው የአዲስ አበባ-ደሴ መንገድ በመከላከያ አጃቢነት ተከፈተ

Views: 119

በግጭቱ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል!

  • ከሸዋሮቢት እስከ ከሚሴ ድረስ ባሉ አከባቢዎች የመንግስት ተቋማና ባንኮች ዝግ መሆናቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል!

በምስራቅ አማራ አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት ምክንያት ላለፉት ስምንት ቀናት ተዘግቶ የነበረው የአዲስ አበባ-ደሴ መንገድ ዛሬ ጠዋት በመከላከያ ሰራዊት አጃቢነት ተከፍቷል፡፡

የካቲት 10 ቀን 2013 ዓ.ም በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እና ልዩ ቦታው አጣዬ ከተማ እና ዙሪያ ባሉ የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን አካባቢዎች የተጀመረው ግጭት የበርካቶችን ህይወት ሲቀጥፍ እስካሁን ግምቱ ያልታወቀ ንብረት መውደሙን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎች ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት በአጣዬ፣ ጀውሃ፣ካራቆሪ፣ ማጀቴ፣ ከሚሴ እና ሸዋሮቢት ግጭቱ የቆመ ቢሆንም፤ አሁንም ነዋሪዎቹ ግጭቱ መልሶ ሊከሰት ይችላል፤ በአካባቢው በቂ የጸጥታ ኃይል የለም ሲሉ ስጋታቸውን ተናግረዋል።

በትናንትናው ዕለትም በኤፍራታና ግድም ወረዳ አላላ እና አሽኳይ ሸረፋ ቀበሌዎች ከአጎራባች የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን ስር ካለው ጅሌ ወረዳ ቀበሌዎች በመጡ ታጣቂዎች መጠቃታቸውን እና ሰዎች መገደላቸውን ንብረታቸውም እንደወደመባቸው ተናግረዋል።

በአካባቢው በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ የሚያስኬደው ዋናው መንገድ ከሸዋሮቢት እስከ ከሚሴ ከተማ ድረስ በመዘጋቱ የጸጥታ ስራውንም ሲያደናቅፍ እንደነበር ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

ይሁንና ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ በሀገር መከላከያ ሰራዊት አጃቢነት ሚኒባሶች የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ስማቸው እንዳይጠቀስ ከፈለጉ የአካባቢው ነዋሪዎች ሰምተናል።

ነዋሪዎቹ እንዳሉት ግጭቱ በተከሰተባቸው ከሸዋሮቢት እስከ ከሚሴ ከተማ ድረስ ባሉ አከባቢዎች የመንግስት ተቋማት፣ ባንኮች እና ሌሎች የንግድ ድርጅቶች ዝግ ናቸው።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com