የግብፁ ሱዌዝ ቦይ 400 ሜትር በሚረዝም የጭነት መርከብ ምክንያት ተዘጋ

Views: 51

የአደጋ ጊዜ መርከቦች ወደ ሥፍራው ተልከው 400 ሜትር ርዝማኔና 59 ሜትር ስፋት ያለውን መርከብ ለማገዝ ደፋ ቀና እያሉ ነው። ነገር ግን መርከቡ በሥፍራው ለቀናት ቆይቶ በመተላለፊያው ላይ የትራፊክ መጨናነቅ ሊፈጥር ይችላል የሚል ስጋት አለ። መርከቡ የትራፊክ መጨናነቅ የፈጠረው ባለፈው ማክሰኞ በሱዌዝ ቦይ በስተሰሜን በኩል ነው።

የሱዌዝ ቦይ በመባል የሚታወቀው የግብፅ መተላለፊያ ቦይ የሜድትራኒያን እና ቀይ ባህርን በማገናኘት በእስያና አውሮፓ መካከል አጭሩ የሚባለውን የውቅያኖስ መንገድ ይፈጥራል። ኤቨር ግሪን የተሰኘው ግዙፍ መርከብ ከቻይና ተነስቶ ወደ ኔዘርላንድስ እያቀና ነበር። የግብፅ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት መርከቡ ባጋጠመው ቴክኒካዊ ችግር ምክንያት ነው መሃል ላይ ቆሞ የቀረው። በፈረንጆቹ 2018 የተሠራው ይህ የፖናማ መርከብ ኤቨርግሪን ማሪን በተሰኘው የትራንስፖርት ኩባንያ ባለቤትነት ነው የሚንቀሳቀሰው።መርከቡ የበርካታ የጭነት መርከቦች መተላለፊያ መንገድ ላይ በመቆሙ ምክንያት የመርከቦች እንቅስቃሴ ለጊዜው ተገትቷል።መርከቡ መሃል መንገድ ላይ በመቆሙ ምክንያት ከወዲህም ሆነ ከወዲያ የሚመጡ መርከቦች ቆመው ችግሩ እስኪፈታ ከመጠበቅ ውጭ አማራጭ የላቸውም።

የግዙፉ መርከብ መንገድ መዝጋት በርካታ ዕቃዎች የጫኑ መርከቦችን በመግታቱ ምክንያት የምጣኔ ሃብት ቀውስ እንዳይመጣ ተንታኞች ይሰጋሉ። መርከቡ ከሥፋራው እንዲንቀሳቀስ ለመርዳት ምናልባት ከሥር ያለውን አሸዋ ቆፍሮ ማውጣት ስለሚጠይቅ ቀናት ሊወስድ ይችላል እየተባለ ነው። መርከቡ በምን ዓይነት ቴክኒካዊ ችግር ምክንያት መንቀሳቀስ እንዳልቻለ አልታወቀም። የሱዌዝ ቦይ 193 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ አለው።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com