ዜና

ትልልቁ ሱፍ እና የምግብ ዘይት ፍለጋ

Views: 227

መነሻ

የምግብ ዘይት ውድ ምግብ ሆነብን፡፡ በአገር ውስጥ የሚመረተው እና ከውጪ የሚመጣው ዘይት አላዳርስ አለ፤ የዘይት ዋጋ ናረ፤ የዘይቱ ሥረ መሠረት እና በቤታችን ሽንኩርትን የምናቁላላበት ደካማ አሠራር ለጤና ቀውስ እያጋለጠን መጣ፡፡  ከብዙ የበሽታ መነሻ ምክንያት ውስጥ እስከ ዛሬ “በዘይት የተነሳ በሽታ” ተብሎ ተለይቶ የወጣ እና የተነገረን ባይኖርም፤ በምንመገበው ዘይት ምክንያት ውስብስብ የጤና ቀውስ መኖሩን ልቦናችን ያውቀዋል፡፡

መቸም ቢሆን የምግብ ዘይት ያስፈልገናል፡፡ ብዙ የዘይት መገኛ ምርት መፈለግ አለብን፡፡ ከእነዚህ ብዙ አማራጭ አንዱ ትልልቁ ሱፍ ይሆናል፡፡

በስም አጠራር ትልልቁ ሱፍ በእንግሊዘኛ ሰንፍላወር (sunflower) ይባላል፡፡ አበባው ከላይ በምስሉ እንደሚታየው፡፡ የእኛ  የሆነው የአበሻ ሱፍ በእንግሊዘኛ ሳፍላወር (Safflower)  ይባላል፡፡ ሁለቱም ለዘይት ምርት ይውላሉ፡፡ ነገር ግን በምርት መጠን እና የዝናብ እጥረትን በመቋቋም ትልልቁ ሱፍ ይበልጣል፡፡

የአበሻ ሱፍ አበቃቀል

አመርረቱ ቀላል ነው

ትልልቁ ሱፍ (አንዳንዴም የፈረንጅ ሱፍ ይሉታል) በብዙ የኢትዮጵያ መሬት በቀላሉ ሊበቅል ይችላል፡፡ ነገር ግን በእርሻ ባለሙያዎች ትኩረት አልተሠጠውም፡፡ ከተለመደው ትንንሹ ሱፍ (የኢትዮጵያ ሱፍ) በበለጠ ምርታማ ነው፡፡

ትልልቁ ሱፍ አንዳንዴም ለአበባው ውበት ተብሎ የሚተከል የሚመስላቸው አሉ፡፡ በአንድ ወቅት በአንድ አካባቢ በብዛት ይመረታል፡፡ “ለከብት ነው”  በማለት ከገበያ ይሰበስቡታል፡፡ ያን የገዙትን ዘይት መጭመቂያ ቤት ወስደው ሙያ ይሠሩበት እና ዘይቱን ይሸጡታል፡፡ ካለማወቅ የተነሳ አምራቾቹም ትልልቁን ሱፍ  “ገበያ አለው፣ ለከብት ይገዙታል” በማለት በማሳ ዳርቻ ይዘሩታል፡፡

ትልልቁ ሱፍ እራሱ ዓይነቱም ብዙ ነው፡፡ የአገዳው እርዝመት በአማካይ ከ አንድ ሜትር እስከ ሶስት ሜትር ይደርሳል፡፡ በአናቱ ላይ እንደ ሰፌድ ተዘርግቶ ያብባል፤ ከአበባው ሥር የሱፍ ዘር ያፈራል፡፡ የዝብ እጥረት ቢከሰት ሥሩ ከ ግማሽ ሜትር በላይ ወደ መሬት ውስጥ ስለሚዘረጋ ድርቅን ይቋቋማል፡፡

ትልልቁ ሱፍ የጤና በረከቱ

ለሁሉም ዘይት የሚደረገው ጥንቃቄ ተደርጎ ዘይቱ ከተጨመቀ፤ ለሁሉም ዘይት የሚደረገውን የአበሳሰል ሥርዓት ጠብቆ ከተሠራ፣  የጤና በረከቱ ብዙ ነው፡፡

በወጥ አሠራራችን ላይ የተመለከተውን ችግር በዚህ ላይ አንብቡ፡፡ ብረት ድስት፣ ዘይት እና በርበሬ ወጥን እንዴት አፋለሱት?  https://ethio-online.com/archives/14241

ለምሳሌ በሚከተለው ሊንክ ላይ በይበልጥ አንብቡ፡፡

https://www.webmd.com/diet/health-benefits-sunflower-seeds#1

ለልብ ጤና፤ የደም ግፊት ለመቆጣጠር፤ የበሽታ መከላከል አቅም ለማጎልበት ይረዳል ይላል፡፡

በከፍተኛ መጠን አምራቾቹ

በዓለም ደረጃ በከፍተኛ መጠን የሚያመርቱት በቅደም ተከተል እነ ዩክሬን፣ ሩሲያ፤ አርጀንቲና፤ ቻይና፣  ሮማንያ፤ ቱርክ፤ ወዘተ ናቸው፡፡ በአፍርካ አህጉር እነ ደቡብ አፍሪካ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ግብጽ፣ ሞሮኮ፣ ዛቢያ፣ ሞዛምቢክ፣ አንጐላ ናቸው፡፡

http://thinkagribusiness.com/2020/06/24/the-sunflower-oil-market-in-the-africa/

ከእነዚህ ሁሉ አምራቾች ኢትዮጵያ በከፍተኛ መጠን የምታስገባው የትልልቁ ሱፍ ዘይት ከቱርክ ነው፡፡ ቱርክ በሌላው ያለን የንግድ ሽርክና እንዳለ ሆኖ በዘይት ተቀባይነት ሳናኮራት አልቀረንም፡፡ ሱቁ ሁሉ የሱፍ አበባ ያለው ዘይት መያዣ እቃ ሞልቶታል፡፡ ዘይቱን እንዲህ ጥሞን ከተመገብነው እራሱ ሱፉን የማናመርተው ስለምን ይሆን?

ፉክክር ይደርብን

ሌላው ቀርቶ የአበሻ ሱፍ የምንለውን ዓይነት እንኳን በከፍተኛ መጠን የሚያመርቱት ሌሎች አገራት ናቸው፡፡  ካዛኪስታን አንደኛ የአበሻ ሱፍ አምራች ናት፡፡ የዓለምን 24 በመቶ እሷ ብቻ ትመርታለች፡፡

የሆነው ሆኖ ይህንን ትልልቁን ሱፍ በርትተን ብናመርተው በብዙ ተጠቃሚ እንሆናለን፡፡ አርሶ አደሩ፣ ባለኢንዱስትሪው፣ ተመራማሪው ይህንን ችላ ባይለው ጥሩ ነው፡፡  እስቲ “ሌሎች ቀደሙን እኮ!” እንበል፣ “ሌሎች ነገዱብን እኮ!”  እንበል፡፡  የምግብ ዘይት ፍለጋው ይቀጥል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com