ዜና

ታላቁ የሥዕል ሊቅ አለ፡ ፈለገሰላም ኀሩይ፤ በግብርናው መስክ ያልተነገረለት ውለታው …

Views: 231

(የጀርመን ጎመን)

መነሻ፡-    

አለ፡ ፈለገሰላም ኀሩይ፤ ኢትዮጵያዊ ታላቅ የሥዕል ሊቅ እና  መምህር ነበር፡፡ በዚህ ሙያው እውቅናው የጎላ ነው፡፡ በአዲስ አበባ የሚገኘው አለ፡ፈለገሰላም የሥነ ጥበብ እና ዲዛይን ት/ቤት በስሙ ተሰይሟል፡፡

ቀደም ባለው ዘመን፣ የትምህርት ቤቱ መሥራች እና ዳይሬክተር መሆኑን እና  በሥነ ጥበብ መስክ ለኢትዮጵያ ያበረከተውን ውለታ ብዙ ሰው ያውቀዋል፡፡ የሙያው ልጆቹ፣ ተማሪዎቹ፣ የሥነ ሥዕል አዋቂዎች፣ የሥነ ሥዕል አድናቂዎች ብዙ ብለውለታል፣ ጽፈውለታል፡ዶክመንተሪ ሠርተውለታል፡፡ ከበሬታው የበዛ ነው! አዲስ አበባ  አለ፡ፈለገሰላም የሥነ ጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ቤት ለዘመናት ብዙ የዘርፉን ባለሙያ ሲያሰልለጥን ቆይቷል፡፡ ዛሬም እያስተማረ ይገኛል፡፡

ከአሥር አመታት በፊት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተዘጋጀውን ዶክመንተሪ በሚከተለው ዩቲዩብ ላይ ማየት ይቻላል፡፡

https://www.youtube.com/watch?v=7LK3V88Bayg

https://www.youtube.com/watch?v=mF_WDrrS43k

የሠዓሊው አለ፡ ፈለገሰላም ኀሩይ ስም አጠራር ስያሜ ለመታሠቢያ ከተዘጋጀው ወረቀት ላይ እንዲህ ይነበባል፡፡

ታላቁ የሥዕል ሊቅ እና መምህር ሠዓሊ አለ ፈለገሰላም (1915 – 2ዐዐ8)

ሠዓሊ እና መምህር አለ ፈለገሰላም ከአባታቸው አቶ ፈለገሰላም ኀሩይእና ከእናታቸው ከ ወ/ሮ አፀደ ደስታ ሐምሌ 24 ቀን 1915 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ በጉግስ ጨዋታ ምክንያት አባታቸውን አቶ ፈለገሰላም ህሩይን በሞት ያጡት ገና በአርባ ቀን ሕፃን ሳሉ ነበር፡፡ ሆኖም ቁርጥ፡ አባታቸውን ይመስሉ ስለነበር፤ አያታቸው ሠዓሊ አለቃ ኀሩይ ልጄ ፈለገሰላም አልሞተም፤ በማለት አለ ብለው ስም አወጡላቸው፡፡   (ሲነበብ ይጠብቃል፡፡)

Photo is courtesy to Lissan Magazine  The Modernization of Ethiopian Art Ale Felege Selam – Ethiopian artist and founder of Addis Ababa School of Fine Arts

 

ሀ/ ውለታው ምን ነበር?

ሠዓሊው አለ፣ ፈለገሰላም በአደባባይ ውሎው ሠርቻለሁ ብሎ ያልነገረው፣ በሥነ ሥዕል ሥራዎቹም ያልገለፀው፣ ወዳጆቹም ያልተናገሩለት፣ ትልቅ ውለታው አለ፡፡ ቤተሰቡ እና ዘመዶቹ ባዘጋጁት ወረቅት ላይ ከሙያው ውጪ የተለየ ክህሎት አለው ብለው የገለፁት ስፖርት፣ ንብ ማነብ፣ ዓሣ ማጥመድ እና የመዝናኛ ልምድ ሲሆን፣ ይህን ትልቁን የአገር ስጦታ አልጠቀሱም ነበር፡፡

ስጦታው ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ የቆየ ነው፡፡ ይኸውም አለ፡ ፈለገሠላም ኀሩይ በማህበራዊ ሕይወቱ ውስጥ ብዙ የአዳማ ናዝሬት ከተማ ጎረቤቶቹን ሲያስተምር የኖረው አንድ ተክል ነበር፡፡ ይህን ተክል የጀርመን ጎመን ብሎ ሰይሞታል፡፡ እስከ ዛሬም በከተማው ውስጥ በሚያውቁት፣ በሚያለሙት እና በሚመገቡት ሰዎች ዘንድ የጀርመን ጎመን ተብሎ ይጠራል፡፡

በ2ዐ1ዐ ዓ.ም ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ከመጡት ባለሙያዎች ጋር ስንጎበኝ ተክሉ የቀድሞው የሠዓሊው አለ፣ ፈለገሰላም መኖሪያ ቤት ውስጥ ግዙፍ ሆነው ይታያሉ፡፡ ጥቂት ጎረቤቶቹ እንደ ነገሩን፣  እራሱ አቶ አለ፣ ሠርቶ ይመገብ እንደነበር፣ ከአዋሽ አሣ አጥምዶ ሲመለስ፣ ከቻያ ቅጠል ጋር በአንድ ላይ እያበሰለ ያጣጥም እንደነበርም ነግረውናል፡፡

ለ/ ለማገናዘቢያ

ሌሎች አገራት አንድ አዲስ ተክል ወደ አገራቸው ሲወስዱ ወይም በአጋጣሚ ሲያገኙት ምን ያደርጋሉ? እንዴት ያለሙታል? እንዴት ያስፋፉታል?  የተባለ እንደሆን፤ ነገሩ የዋዛ አይደለም፡፡ ከአንድ አመት በፊት ከአዝዕርት እና ከጤፍ ተመራማሪው እና ጤፍን ለመጀመሪያ ጊዜ ካዳቀሉት ከዶ/ር ታረቀ በረሔ ጋር ስለ ጤፍ ቃለመጠይቅ ስናደርግ፣ እንዲህ ብለው ነበር፤

“አውስትራሊያ ለመጀመሪያ ጊዜ አገኘሁ ያለችው 4 ፍሬ ጤፍ ነበር፡፡ ያንን እያባዙ በ 4 አመት ውስጥ ጤፍን ለገበያ ማቅረብ ቻሉ፡፡”

ይህንን ስሰማ 4 ኩንታል ማለት ፈልገው ነው ብዬ አሰብኩ፡፡ ነገር ግን በትክክል 4 ፍሬ ጤፍ ነበር፡፡ ይህንን በእነዚህ ሊንክ ላይ ስለጤፍ ጉዳይ በሚል ርዕስ ማድመጥ ይቻላል፡፡ https://www.youtube.com/watch?v=4EV0Yev5EGE

https://www.youtube.com/watch?v=KAs4SGaBINw&t=258s

https://www.youtube.com/watch?v=gi18IoXejIU&t=1390s

በሌላው አገር እነሆ፤ የአውስትራሊያ ሳይንቲስቶች ጤፍን እንዴት ቆጠሩት፣ እንዴትስ 4 ፍሬ ለዩ፤ ከዚያም እንዴት በ 4 አመት ውስጥ ለገበያ አደረሱት!?

በእኛ አገር በቀላሉ ተቆራርጦ የሚተከል እንጨት ለማባዛት ወይም የምርምር በር ላይ ሳይደርስ ግማሽ ክፍለ ዘመን ሲሻገር፤ በምን ይገለፃል፤

“ልብ ያለው ልባሙ ሄደ ገሰገሰ፣

ወይኔ በስንፍናው ቀረ እያለቀሰ፡፡”

የሚሉት ምሳሌያዊ ንግግር ማጠቃለያ ይሁነኝ፡፡

ሐ/ የጀርመን ጎመን ጥቅሙ ምንድነው?

እነሆ ይህ ተክል ቻያ CHAYA (Cnidoscolus chayamansa -ኒዶስኮሉስ ቻያማንሳ)  ወይም ቻያ መንሳ፣ ትሪ እስፒናች፣ ይባላል፡፡  ነቅ መነሻ አገሩ  ሜክሲኮ ነው፡፡ በአገሩ የተወደደ ምግብ ነው፡፡ በብዙ አገራትም ተወስዶ ሰፊ ጥቅም እየሰጠ ይገኛል፡፡

ቻያ ተክል

የጎሉ ጥቅሞቹ በአጭር ሲገለፁ እንዲህ ነው፤

በቆላ ምድር ይለማል፣

ቻያ የበረሐ ጥላ ይሆናል፣

ድርቅን፣ በረሐማነትን ይቋቋማል፡፡

ለምግብ፣ ለመጠጥ፣ ለመድኃኒት፣

ለኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ ይሆናል፡፡

አተካከሉ፡    የቻያ እንጨት ቁርጥራጩ  በተተከለ ከ 3 ወር ጀምሮ ለምግብ፣ ወይም ለመጠጥ ይውላል፡፡ አመቱን ሙሉ ይበላል፡፡ ከዚያም ተቆርጦ ይተከላል፡፡ ይቀጥላል ….. የበረሐን ምድር አረንጓዴ ያለብሳል … የምግብ ዋስትናን ይደግፋል … ተክሉ ባለ ብዙ ጠቀሜታ ነው፡፡ አመቱን ሙሉ በፈለጉበት ወራት ቢተክሉት ይለማል፡፡ ቁርጥራጩን ለመጓጓዝ ሁለት ሳምንት ቢቆይ ይለማል፡፡

የት ይለማል፡-  በቆላማ እና ሞቃት ወይናደጋ አካባቢ ሁሉ፣  በቆላ ምድር በጓሮ፣ በተጎዳ መሬት፣ በእርሻ ማሳ ዙሪያ፣ በአጥር ዙሪያ፣ በደን ውስጥ፣ በሰፋፊ በረሐ ምድር፣ በቆላማ መንደሮች፣ በአርብቶ አደሮች አዲስ በሚመሠረቱ መንደሮች ውስጥ፣ በትምህርት ቤቶች ጊቢ ውስጥ፣ ወዘተ ማልማት ይቻላል፡፡

ስብጥር ትክሎሽ፡-  ከሌላ አዝዕርት ወይም ዛፍ ጋር  በስብጥር መትከል ይቻላል፡፡

ማን ያለማዋል፡- ይህን ተክል በቀላሉ እናቶች፣ ሴት ልጆች፣ አረጋውያን በትንሽ ቦታ ላይ አልምተው ብዙ ጥቅም ሊያገኙበት ይችላሉ፡፡  በሰፋፊ እርሻም ሊለማ ይችላል፡፡ በብዛት ቢለማ ለብዙዎች ጥቅም ይሰጣል፡፡

ሰደድ እሳት መመከት ይችላል፣ እርጥበትን የመያዝ ችሎታ ስላለው፤ ደን ውስጥ በመስመር አልፎ አልፎ ቢተከል የሰደድ እሳት አደጋ ድንገት ቢከሰት ከቻያ በሚገርም ሁኔታ እሣቱ ይመክታል፡፡  እሣቱም ሊጠፋ ይችላል፡፡

መ/ ሠዓሊው ስሙን ለምን የጀርመን ጎመን አለው?

ሠዓሊው አለ፡ ፈለገሠላም ኀሩይ፤  ይህንን የተክል ቁርጥራጭ እንደምን አድርጎ ከሜክሲኮ ወይም ከሌላ አገር አመጡት? ወይም እንደምን እና በማን አስመጡት? እዚህ ከደረሰ በኋላ ይህን ስያሜ ለምን የጀርመን ጎመን ብሎ ሰየመው?

ይህንን ወደፊት ትውልዱ ጥናትና ምርምር ያድርግበት፡፡

ሠ/ እስከ አሁን ምን ጥረት አደረግኩኝ?

ተክሉን ለመጀመሪያ ጊዜ ከ5 አመታት በፊት (በ2ዐዐ8 ዓ.ም በጋ ወራት) ከጎረቤቶቼ ጊቢ አየሁት፡፡

ከተመራማሪ ጓደኞቼ ጋር የፃፍነው፣ የደከምነው፣ ያመለከትንበት ድርጅቶች፣ ታዋቂ የአገራችን ሚንስትር መሥሪያ ቤቶች፣ ዓለምአቀፍ ተቋማት ትኩረት ነፈጉት፡፡ እኛ የፃፍነው በአግባቡ ደረጃውን የጠበቀ በኢንግሊዘኛ ነበር፡፡   ሆኖም…  (?)

እንዲሁ በግል ጥረት ለማስፋፋት አዳማ እና በዙሪያዋ በየሰው ቤት እንዲተከል አደረግኩኝ፡፡ አዲስ አበባ ቃሊቲ አካባቢ ጥቂት ቦታ እንዲተከል ሞከርኩኝ፡፡ ለመትከል፣ ወይም ርቀት ቦታ ይዘው ለሚያደርሱ ፍቃደኛ ሰዎች ብዙ ቦታ ልኬአለሁ ወይም እራሴ አድርሻለሁ፡፡ ከነዚህም ጥቂቱ ያቤሎ፣ ከፋ፣ ሸካ፣ መቀሌ፣ ባሕርዳር፣ ሚኤሶ፣ ዝዋይ ዱግዳ ወዘተ፡፡ ብዙዎቹም ተክሉ ይዞልናል ብለዋል፡፡

ከ2ዐዐ9 ዓ.ም ጀምሮ ለብዙ የምርምር ተቋማትና ኮሌጆች  ብዙ ውትወታ አድርጌ ነበር፡፡ ከብዙዎች አንዱ ተባባሪ ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ነበር፡፡ በ2ዐዐ9 ዓ.ም ነሐሴ ወር እና 2ዐ1ዐ ዓ.ም ህዳር ላይ አንድ ቡድን ከቤቴ መጥተው የሚተከለውን ይዘው ሄዱ፡፡ የወሰዱትን ግማሹን በሐሮማያ ጊቢ ውስጥ ተከሉት፣ አንድም ሳይፀድቅ እንዳለ ደረቀ፣ ግማሹን ድሬዳዋ በሚገኘው ቶኒ ፋርም ጣቢያ ውስጥ ተከሉት፤ ሁሉም ያዘ፣ በ4 ወራት ውስጥ ያሳየው እድገት የሚደነቅ ነበር፡፡

አንድ የማስተርስ ተማሪ የመመረቂያ ወረቀቱን በቻያ ልማት ላይ ጽፎ ጥሩ ውጤት አስመዘገበ፡፡ ጥር 2ዐ11 ዓ.ም በድሬዳዋ ቶኒ ፋርም ውስጥ የመስክ ምልከታ እና የምግብ ቅምሻ ቀን አብረን አዘጋጅተን ነበር፡፡ በወቅቱም ለቆላ መሬት ልማት እና ለስነምግብ መልካም መሆኑን፣ ወደፊት ብዙ ጥናት እንደሚያደርጉበት ገለፁ፡፡ ከዝግጅቱም በኋላ ስለ ውሎው ቻያ አዲሱ እንግዳ በከተማ ውስጥ ብለው አሞጋግሰው ጽፈው ነበር፡፡ ይህንኑ በሚከተለው መረጃ መረብ ላይ አንብቡ፡፡

Chaya: The New Guest in Town    https://www.haramaya.edu.et/chaya-the-new-guest-in-town/

ረ/ ቻያ በጂንካ ከተማ

በሩቅ ደቡብ በምትገኘው ጂንካ ከተማ ቻያ በየሰው ጓሮ እና መንገድ ዳርቻ ተስፋፍቶ ይገኛል፡፡ ቻያን፣ ማን፣ መቼ እንዴት ወደዚያ እንዳደረሱት ለጊዜው አልታወቀም፡፡  የከተማ ውስጥ መንገድ ሲሠራ፣ የሚነሳ ከሆነ ቤተሰቦች “የልጆቼ ማሳደጊያ ነው” በማለት ካሳ ይቀበሉበታል ብለውኛል፡፡

በዚያ አካባቢ ለማስፋፋት ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት ነው፡፡ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ እና ሌሎችም የምርምር ተቋማት ትኩረት ቢያደርጉበት በጣም ጥሩ ነው፡፡

መዝጊያ፡-

በክፍል ሁለት ምግቡ ተሠርቶ ሲበላ እንዴት ይሆን፣ ሲጠጣስ፣ ጠቀሜታው፣ ምግብ አዘገጃጀቱስ፣ ወደ ዱባይ የሚልኩ አገራት እነማን ናቸው፣ የሚለውን ይዘን እንቀርባለን፡፡ እስከዚያው ያንብቡ፡፡ እናም ቸር ሠንብቱ!!!

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com