ለጉበት ስብ ክምችት መላው ምን ይሆን?

Views: 246

መነሻ ጉዳይ፡-

ለጉበት ስብ ክምችት በሽታ (Fatty Liver disease) ተብሎ በዩ.ኤስ.ምግብ እና መድኃኒት አስተዳደር (U.S. Food and Drug Administration) የተረጋገጠ መድኃኒት የለም፡፡ “ለማንኛውም እስከ 1ዐ ከመቶ የክብደትን መጠን መቀነስ መልካም ነው፤ ሌላው ቀርቶ ከ 3 እስከ 5 ከመቶ እንኳን ክብደት መቀነስ ይረዳል፡፡ ደግሞም በሕክምና ዶክተር የሄፐታይተስ ኤ የደም ምርመራ ማድረግ  እና ሄፐታይተስ ቢ ክትባት ማግኘት ቫይረስ ጉበትን እንዳይጎዳ ለመከላከል ይረዳል” የሚለው ሔልዝ ላይን ዶት ኮም ነው፡፡ ማጣቀሻ 1

ስሙ እንደሚገልፀው ይህ በሽታ የሚከሰተው በጉበት ውስጥ ብዙ ስብ (ቅባታም ነገር) ተከማችቷል ማለት ነው፡፡ በጤነኛ ሰው አካል ውስጥ ጉበት በዋናነት የሚሠራው መርዛማ ነገሮችን ማስወገድ እና  ለምግብ ፕሮቲን ስልቀጣ የሚውል ሐሞት ማምረት ነው፡፡ በጉበት ውስጥ የስብ ክምችቱ የጉበትን የተለመደ ሥራ ያስተጓጉላል፡፡ ይህን መስተጓጎል ተከትሎ ብዙ የጤና ቀውስ ሊመጣ ይችላል፡፡

አስተውሉ፡-  ብዙ የጉበት በሽታ ዓይነት አሉ፡፡ ይህ የጉበት ስብ ክምችት በሽታ እና ሌላው የጉበት በሽታ የተለያዩ ናቸው፡፡ የጉበት ስብ ክምችት በሽታን በቀላሉ በአልትራሳውንድ ምርመራ መለየት ይቻላል፡፡

ሀ) ስንት ዓይነት የጉበት ስብ ክምችት በሽታ አለ?

በዋናነት ሁለት ዓይነት የጉበት ስብ ክምችት በሽታ አለ፡፡

 • በአልኮል መጠጥ የሚከሰት (alcohol-induced) ብዙ አልኮል መጠጥ በመጠጣት የተነሳ የሚከሰተው የጉበት ስብ ክምችት በሽታ ባለ አልኮል የጉበት ስብ ክምችት  በሽታ  (alcoholic fatty liver disease  – AFLD).  ይባላል፡፡
 • በአልኮል አልባ የሚከሰት (non alcoholic fatty liver) በአልኮል መጠጥ ሳይሆን በሌሎች ችግሮች የተነሳ የሚከሰተው የጉበት ስብ ክምችት በሽታ አልኮል አልባ የጉበት ስብ ክምችት በሽታ (non-alcoholic fatty liver disease  – NAFLD). ) ይባላል፡፡  አልኮል አልባ የጉበት ስብ ክምችት ብዙ ጊዜ የሚከሰትባቸው ልክ አለፍ ውፍረት ያላቸው ወይም በጣም የተቀናበሩ ምግቦችን በሚያዘወትሩት ላይ ነው፡፡

በዚህ ጽሑፍ ላይ ለታማሚው ይህን የጉበት ስብ ክምችት በሽታ ለማስወገድ የሚረዱ ምግብ እና መጠጥ እንዲሁም አስፈላጊ ያልሆኑ የምግብ ዓይነት ተለይተው ተገልፀዋል፡፡ በተፈጥሮ ዘዴ በሽታውን ማስወገድ እና ዳግመኛ እንዳያገረሽ የሚረዳውን ዘዴ መከተል ብልሃት ነው፡፡

ለ) ለሁለቱም ዓይነት የጉበት ስብ ክምችት የተሻሉ ምግቦችና መጠጦች

 1. ቡና መጠጣት፡- ቡናን በልክ መጠጣት
 2. አረንጓዴ አትክልቶች ፡-መመገብ፡፡ በተለይም ብሮኮሊ፣ እስፒናች፤ አበሻ ጎመን፣ የሰናፍጭ ቅጠል፣ እና የመሳሰሉት በአግባብ አብስሎ፣ በወይራ ዘይት ሠርቶ መመገብ፡፡
 3. ቶፉ፡-  ይህ ማለት የአኩሪ አተር ወተት ሲዘጋጅ ወተቱ ተጨምቆ የሚቀረው ነው፡፡ ይህን ቶፉ እንደገና በማብሰል፣ በመጠባበስ፣ ከሌሎች አትክልት ጋር በማዘጋጀት መመገብ፡፡
 4. ኦሜጋ 3 ፋቲ አሲድ ይዘት ያለውን አሳ መመገብ፡፡  እንደ ሳልሞን፣ ሳርዲን፣ ቱና ያሉትን ማለት ነው፡፡
 5. ኦትስ የተባለ የሰብል ዓይነት፡- ይህ ከአገራችን አጃ የተለየ ነው፡፡ በጣሳ የሚሸጡ አሉ፡፡ በአገር ውስጥም በደጋ አካባቢ ይመረታል፡፡
 6. ዋልነት መመገብ፡- ነጩ የዋልነት ፍሬው በትልልቅ ሱፐርማርኬት ውስጥ ይገኛል፡፡
 7. አቮካዶ መመገብ፡፡    ቢቻል ከበሰለ እንጉዳይ ጋር የተዘጋጀ ይመረጣል፡፡
 8. ስቡ የወጣለት ወተት መጠጣት፡፡

ትልልቁ ሱፍ Sunflower  ፍሬውን መመገብ፡-  ይህም ከአገራችን ሱፍ የተለየ ነው፡፡ ሲበቅል አናቱ እንደሰፌድ የተዘረጋ ነው፡፡ ይህን የደረሰውን ፍሬውን ማመስ፣ ከወፍራም ቅርፊቱ መፈልፈል እና መመገብ ነው፡፡ ወይም በማሽን መፍጨት እና በውሃ በጥብጦ፣ ቀቅሎ አጥልሎ መጠጣት ነው፡፡ ከፍተኛ ቫይታሚን ኢ ያለው ስለሆነ ጉበትን ከጉዳት ይታደጋል፡፡

ትልልቁ ሱፍ አብቦ እያፈራ ሳለ

 1. የወይራ ዘይት መጠቀም፡-  ለማንኛውም ምግብ ለማሰናዳት የወይራ ዘይት ብቻ መጠቀም ይገባል፡፡ ይህም ሆኖ ምግብ በማብሰል ሂደት ሙቀት እንዳይጎዳው ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
 2.  ነጭ ሽንኩርት አዘውትሮ መመገብ፡፡
 3.  አረንጓዴ ሻይ መጠጣት፡፡
 4.  የግሬፕ (grapefruits ) ፍራፍሬ መመገብ፤

ግሬፕ ፍራፍሬ

 1.  ወይን  ፍራፍሬ መመገብ፣
 2. የቁልቋል በለስ ፍራፍሬ መመገብ፣ ቁልቋል በለስ የሚበላ እና የሚጠጣ በሚል ርዕስ በዚህ ሊንክ https://ethio-online.com/archives/4036  ላይ አንብቡ፡፡
 3.  የቀይ ሥር ጁስ መጠጣት፣ ስለ አዘገጃጀቱ ቀይ ሥር ለጤና በሚል ርዕስ በዚህ ሊንክ https://ethio-online.com/archives/5146 ላይ አንብቡ፡፡
 4.   ቻዮቴ ከወዴት አለሽ? በሉ፡፡ ስታገኙ ተመገቡ፤ ልማቱም ላይ ትጋት አድርጉ፡፡ ስለ ቻዮቴ ልማት እና ጠቀሜታ በዚህ ሊንክ https://ethio-online.com/archives/14436   ላይ በይበልጥ አንብቡ፡፡

ሐ) ታማሚው መጠቀም የሌለበት ምግብ ወይም መጠጥ

 1. ማንኛውም አልኮል መጠጥ፤
 2. ቀይ ሻይ በምንም መጠን ቢሆን፤
 3. ስኳር የተጨመረበት ማንኛውም ምግብ ወይም መጠጥ፤
 4. የተቀሩትን ዘይት ሁሉ፣ (ከወይራ ዘይት በቀር ማለት ነው)
 5. በዘይት የተጠበሱ ምግቦች
 6. ጨው፣ በጨው የተሠሩ ምግቦች፤
 7. ነጭ ፍርኖ ዱቄት፣ ሩዝ፣ ፓስታ፣ መኮረኒ እና ከእነዚህ የተዘጋጁ ማንኛውም ምግብ፣
 8. ሥጋ እና በሥጋ የተሠሩ ምግቦች፣
 9. በፋብሪካ የተቀናበሩ ምግቦች፤
 10. በርበሬ፤ በርበሬአችን እና የአፍላቶክሲን ችግር በሚል ርዕስ በዚህ ሊንክ https://ethio-online.com/archives/2483  ላይ አንብቡ፡፡
 11. በአሉሚኒየም ብረት ድስት የተዘጋጁ ምግቦች፡፡ የጉዳቱን መጠን በዚህ ሊንክ https://ethio-online.com/archives/14241  ላይ አንብቡ፡፡

መ)  በሽታውን ለማስረዳት የተገኘ ምስል

ከላይ በግራ ጤነኛ ጉበት                                              በቀኝ የስብ ክምችት የጎዳው ጉበት

ምስሉ የተገኘው ከ https://www.healthline.com/health/fatty-liver   መረጃ መረብ ነው፡፡

ሠ)  ተጨማሪ ምክሮች፡-

ከላይ ከተነገሩት ምክሮች በተጨማሪ

 • ክብደት ለመቀነስም ስለሚረዳ ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ፣
 • የኮልስትሮል መጠን መቀነስ፣ ቅባታማ ምግቦችን፣ ስኳር እና መሠል ምግቦችን በመቀነስ የኮልስትሮል መጠን መቆጣጠር ያስፈልጋል፤
 • የስኳር በሽታን (Diabetes) መቆጣጠር፣ አልፎ አልፎ የስኳር በሽታ እና የጉበት ስብ ክምችት አብረው ይከሰታሉ፡፡ ስነ ምግብ እና እንቅስቃሴ ሁለቱንም ለመቆጣጠር ያግዛሉ፡፡

ረ) የጉበት የስብ ክምችት በሽታ ደረጃዎች ምስል

በውል ተለይተው የሚታወቁ የጉበት በሽታ ደረጃዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ቀጥሎ ካሉት ምስሎች ውስጥ የመጀመሪያው ገና የስብ ክምችት ላይ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ሳለ በትጋት ያሉትን አማራጮች በሙሉ መጠቀም ነው፡፡ ጉበቱን ለማዳን ያለው ተስፋ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ ምስል በዐይን ቀጥታ በማየት ሣይሆን በምርመራ መሳሪያ ሲታይ ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ላይ ሳለ ህመሙ እራሱ ለባለቤቱ አይታወቅ ይሆናል፡፡ በሽታውን አውቆት ቢሆን እንኳን የዘወትር ተግባሩን ይከውን ይሆናል፡፡  ለዚህ ነው አዋቂዎች በየትኛውም ደረጃ የሚገኝ የጉበት በሽታ ጉዳይ ከፍተኛ ስጋት የሚያሳድርባቸው፡፡

Courtesy to       https://hunterdongastro.com/non-alcoholic-fatty-liver-disease-nafld/

የጉበቱ የስብ ክምችት በሽታ እንደታወቀ  በወቅቱ እራስን ካላስታመሙ ወደ ሌላው ደረጃ ይሻገራል፡፡ እናም  የመጨረሻው ደረጃ ሲሮሲስ ይባላል፡፡ በዚህ ደረጃ የደረሰውን ለማዳን እጅግ ከባድ ነው፡፡  ከታች በምስሉ እንደሚታየው እና እንደሚያስረዳው ሲሮሲስ የደረሰውን ወደ ቀደመው የጤናማ ጉበት ደረጃ መመለስ አይቻልም፡፡

ለምስሉ ምስጋናው ለሜዲካል ኒውስ ቱዴይ ይሆን

ማጠቃለያ፡-

ከላይ የተነገረው ሁሉ ጠቃሚ ምክር ነው፡፡ ሁሉንም አትክልት እና ፍራፍሬ በአንድ ጊዜ ለማግኘት አይቻልም፡፡ እንደተገኘ መጠቀም ነው፡፡ ነገር ግን ታማሚው መጠቀም የሌለበት ምግብ ወይም መጠጥ የሚለውን ጉዳይ በቸልታ አትመልከቱ፡፡ ጉበት አደጋ ቻይ የሰው አካል ነው፡፡ በብዙ ጉዳት ተይዞ እንኳን ታማሚው ይበላል፣ ይጠጣል፣ ይሠራል፡፡ አንዳች የመጨረሻ ደረጃ ከደረሰ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡  አስታማሚዎችም የጉበትን ጉዳይ እንደቀላል አትመልከቱ፡፡

ማጣቀሻ

በይበልጥ ከእነዚህ ሊንክ ላይ አንብቡ

ማጣቀሻ 1    https://www.healthline.com/health/fatty-liver

ማጣቀሻ 2   https://www.healthline.com/nutrition/11-foods-for-your-liver#TOC_TITLE_HDR_12

ማጣቀሻ 3  ኮሸሽላ ለጉበት ጤና https://ethio-online.com/archives/6194

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com