በሰሜን ጎንደር ዞን በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት የተገነባ ትምህርት ቤት ተመረቀ

Views: 44

በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት 14 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ የተገነባ 2ተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዛሬ ተመረቀ።

በጽ/ቤቱ የተገነባውን የብርሃን ደባርቅ 2ተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መርቀው የከፈቱት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር ሲሆኑ በሥነ-ሥነዓቱ ላይ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ተገኝተዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ እንዳሉት የክልሉ መንግስት የትምህርት ቤቱን የውስጥ ቁሳቁስ በአጭር ጊዜ ውስጥ በማሟላት የመማር ማስተማር ስራ እንዲጀምር ይደረጋል።

የቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት በክልሉ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻልና ገፅታ ለመቀየር እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀው የክልሉ መንግስትም የጽሕፈት ቤቱን የማስፈጸም መልካም ተሞክሮ ወስዶ እንደሚተገብርም አስታውቀዋል።

የአካባቢው ማህበረሰብ ትምህርት ቤቱን እንደራሱ ንብረት በመጠበቅና በመንከባከብ ከትውልድ ትውልድ እንዲሸጋገር የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ መልዕክት ያስተላለፉት ደግሞ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ናቸው።

የተማረ ሰው ራሱን ቤተሰቡንና ሀገሩን የሚጠቅም በመሆኑ ወላጆች በተለይ ሴት ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት በመላክ የትምህርት ተቋዳሽ እንዲሆኑ ትኩረት እንዲሰጡም ጠይቀዋል።

የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ያየዓለም ፈንታሁን በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት እንዳሉት ትምህርት ቤቱ በሁለት ፈረቃ 1 ሺህ 800 ተማሪዎችን የማስተናገድ አቅም አለው።

ትምህርት ቤቱ 18 የመማሪያ ክፍሎች፣ ሶስት ቤተ ሙከራዎች፣ አንድ ቤተ መጻሕፍትና ሌሎችም መገልገያዎች ማካተቱን አስረድተዋል።

በትምህርት ቤቱ የምረቃ ሥነ- ሥርዓት የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞን ጨምሮ ሌሎች የክልሉና የዞን ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የደባርቅ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

ለትምህርት ቤቱ ግንባታ የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት የዕውቅና ምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን፣ ለቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውና ለአቶ አገኘሁ ተሻገር የባህል አልባሳት ስጦታ ተበርክቷል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com