አምባሳደር ብርሃኑ ከጅቡቲው የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ጋር መከሩ

Views: 48

በጂቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ ከጅቡቲው የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ዘካሪያ ሼክ ኢብራሂም ጋር ተገናኝተው በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እና አካባቢያዊ የፀጥታ ጉዳየች ዙሪያ መክረዋል።

በውይይታቸው በሀገሪቱ ፕሬዚዳንት የተፈቀደውን ከፍተኛ የወታደራዊ ኒሻን ለጄኔራል ብርሃኑ ጁላ መሸለማቸው የኢትዮጵያን መንግሥት፣ የመከላከያ ሠራዊቱን እና መላው ኢትዮጵያውያንን ያስደሰተ መሆኑን አምባሳደር ብርሃኑ አስረድተዋል።

ሽልማቱ ጅቡቲ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን ሥፍራ የሚያመላክት መሆኑን የገለጹት አምባሳደሩ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የተላከውን ከፍተኛ ምስጋናም ለጄኔራሉ አቅርበውላቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የጁንታው ቡድን በትግራይ ክልል የመከላከያ ሠራዊት ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ የመከላከያ ኃይል በአካባቢው ሕግ እና ሥርዓትን ለማስከበር ያደረገውን እንቅስቃሴ ተከትሎ የጅቡቲ መንግሥት እና ሕዝብ ለኢትዮጵያ ያላቸውን ድጋፍ ቀድመው ያረጋገጡ መሆኑን ያስታወሱት አምባሳደሩ፣ ጅቡቲ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ወዳጅ መሆኗን ማሳያ እንደሆነም አንስተዋል።

የጅቡቲ ጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ዘካሪያ በበኩላቸው የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት ታሪካዊ እና በሕዝብ ለሕዝብ የተሳሰረ መሆኑን አንስተው፣ በመከላከያ ኃይል ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ የተመራው ቡድን በጅቡቲ በነበረው ቆይታ በሁለቱ ሀገራት መካከል ባለው ግንኙነት እና በመከላከያ ኃይሎችም መካከል ተባብሮ መሥራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸውን ገልጸዋል።

“ኢትዮጵያ ስትራቴጂክ አጋራችን ናት” ያሉት ጄኔራል ዘካሪያ ግንኝነቱን ይበልጥ ለማጠናከር በጅቡቲ በኩል ያለውን ቁርጠኝነትም በድጋሚ አረጋግጠዋል።

ሁለቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከሁለትዮሽ ጉዳዮች በተጨማሪ በአካባቢያዊ የፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ የተወያዩ ሲሆን፣ በሀገራቱ ብሎም በቀጣናው ሰላም እንዲሰፍን ተብብረው መሥራት እንደሚገባቸውም በውይይታቸው ወቅት መግለጻቸውን በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com