‹‹በመተከል ዞን በንፁሃን ዜጎች ላይ ጥቃት እየፈፀመ ባለው የጥፋት ቡድን ላይ የተጠናከረ እርምጃ እየተወሰደ ነው››

Views: 39

በመተከል በንጹሃን ዜጎች ላይ ጥቃት እየፈፀመ ባለው የጥፋት ቡድን ላይ የተጠናከረ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን በዞኑ የተቋቋመው ግብረ ኃይል አስታወቀ።

ግብረ-ሃይሉ ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ዕቅዶችን አውጥቶ በመተግበር ላይ መሆኑንም ነው የገለጸው።

በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ የጥፋት ቡድኑ ላይ የሚወሰደው ሕጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

ባለፉት 15 ቀናት የመንግስት አመራሮችን ጨምሮ በርካታ የቡድኑ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አስታውሰዋል።

ይሁንና የጥፋት ቡድኑ በአንዳንድ አካባቢዎች የተስፋ መቁረጥ ጥቃት መፈጸሙን ገልጸው፤ በእነዚህ አካባቢዎች የፀጥታ ኃይሉ በአፋጣኝ በመድረስ በቡድኑ ላይ እርምጃ መውሰዱን ተናግረዋል።

የአካባቢውን ሠላም ለማስጠበቅ እየተወሰደ ካለው እርምጃ ጎን ለጎን የመንግስት መዋቅሮችን የማጥራትና በሕዝብ አመኔታ ያገኙ አዳዲስ አመራሮችን የመተካት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልፀዋል።

ከ177 በላይ አመራሮች ለሦስት ቀናት ስልጠና መውሰዳቸውንና ከእነዚህም መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት አዳዲስ አመራሮች መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ስልጠናው በዋናነት በዞኑ የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር በዘላቂነት በመፍታት ረገድ የአመራሩ ሚና ምን መሆን አለበት በሚለው ጉዳይ ትኩረት ያደረገ ነው ብለዋል።

በስልጠናው በአመራሩ የስነ ምግባር ጉድለትና ቸልተኝነት የተፈጠሩ ችግሮችን በተቀናጀ መልኩ መፍታት የሚያስችሉ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውንም አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል።

የሠላም ሚኒስትር ደኤታ ወይዘሮ ፍሬአለም ሽባባው በበኩላቸው በችግሩ ለተፈናቀሉ ዜጎች የዕለት ደራሽ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት በጥቃቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የጤናና የስነ-ልቦና ድጋፍ እንደሚደረግም ገልፀዋል።

በፀጥታ ችግርና የተሟላ መረጃ ባለመኖሩ ምክንያት የዕለት ደራሽ ድጋፍ ዘግይቶባቸው ለነበሩ ዜጎች አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል።

የፌዴራል መንግስት ከሚያደርገው ድጋፍ ጎን ለጎን በአቅራቢያው ያለው ማኅበረሰብ ለተጎጂዎች ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com