በማካድራው የዜጎች ጭፍጨፋ ወንጀል የተጠረጠሩ 2 ግለሰቦችና ተባባሪዎቻቸው ፍርድ ቤት ቀረቡ

Views: 48

በማካድራው የዜጎች ጭፍጨፋ ወንጀል የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦችና ተባባሪዎቻቸው ፍርድ ቤት ቀረቡ። በዚህ የምርመራ መዝገብ በማይካድራ ዜጎችን ሲያስጨፈጭፉ ነበሩ የተባሉ ሁለት ተጠርጣሪዎችና ሶስት ተባባሪዎቻቸው ዛሬ የፌዴራሉ መካከለኛ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ቀርበዋል።

ሁለቱ ተጠርጣሪዎች በማይካድራ ንጹሐን ዜጎች እንዲጨፈጨፉ ካስደረጉ በኋላ ሸሽተው አዲስ አበባ ገቡተው ከተሸሸጉበት የእንግዳ ማረፊያ ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት።

በዚህ ወንጀል ተጠርጥረው ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡት ተስፋይ ከበደ እና አባዲት አብርሃ ሲሆኑ፣ እነሱን በመሸሸግ ተባባሪ ናቸው የተባሉት ደግሞ ኪዳኔ ገብረሕይወት፣ ሙሉዓለም ዮሐንስ እና ፍሬሰንበት ለማ ናቸው።

መርማሪ ፖሊስ ዛሬ ለፍርድ ቤቱ እንዳቀረበው በተጠርጣሪዎቹ ላይ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ሲያሰባስብ የቆየ መሆኑን አስረድቷል።

በመሆኑም፣ እስካሁን በተካሔደው የምርመራ ስራ የተጠርጣሪዎችን ቤት በመፈተሽ ማስረጃዎችን ማሰባሰቡን አመልክቷል።

በአሁኑ ወቅት ማስረጃዎችን ለቴክኒክ ምርመራ ወደ ሚመለከተው አካል መላኩን ጠቁሞ ቀሪ ስራዎችን ለማከናወን ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል።

ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው መርማሪ ፖሊስ ማስረጃዎችን እስኪሰበስብ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርና በውጭ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ጠይቀዋል።

የግራ ቀኝ ክርክሩን ያደመጠው ፍርድ ቤቱ ግን የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ መርማሪ ፖሊስ ከጠየቀው 14 ቀን ውስጥ 11ዱን በመፍቀድ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com