“ሽልማቱ መከላከያ ለቀጠናው ሰላም ላበረከተው አስተዋፅኦ እውቅና የሰጠ ነው”

Views: 50

ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ፣ ከጂቡቲ ህዝብና መንግስት የተበረከተላቸው የሀገሪቱ የመጨረሻ ደረጃ ከፍተኛ ኒሻን የሀገር መከላከያ ሰራዊት ለቀጠናው እያበረከተ ላለው ሰላም እውቅና የሰጠ መሆኑን ገለፁ። ሰራዊቱ በአካባቢው አገራት አድናቆት እንዲቸረው ማድረጉንም አመለከቱ።

በጁቡቲ የሀገሪቱ ከፍተኛ የሜዳልያ ኒሻን የተበረከተላቸው የመከላከያ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀኔራል ብርሀኑ ጁላ አዲስ አበባ ሲገቡ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸውል።

ጀኔራል ብርሃኑ ማምሻውን ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮኘላን ማረፊያ ሲደርሱ የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር ቀነዓ ያደታን ጨምሮ ከፍተኛ የመከላከያ መኮንኖች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ፣ ሽልማቱ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ለቀጠናው ሰላም እያበረከተ ላለው አስተዋጽኦ እውቅና የሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።

መንግስት በጁንታው ላይ የሕግ ማስከበር እርምጃ በወሰደበት ወቅት በርካታ የጎረቤት ሀገራት ቀጠናው ይረበሻል የሚል ስጋት አድሮባቸው እንደነበርም ነው ያስታወሱት።

ነገር ግን ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን የሕግ ማስከበር እርምጃውን በአጭር ጊዜ በድል ማጠናቀቁ በቀጠናው ሀገራት አድናቆት እንዲቸረው አድርጓል ብለዋል።

ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ በትላንትናው ዕለት በጂቡቲ ፕሬዚዳንት ሙሉ ፍቃድ የሀገሪቱ የመጨረሻ ከፍተኛ ኒሻን ከጂቡቲ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀነራል ዘከሪያ ሼህ ኢብራሂም የተበረከተላቸው መሆኑ ይታወቃል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com