የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የውጭ ጉዳይ እና ውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሶስትዮሽ ስብሰባ ተካሄደ

Views: 45

የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የውጭ ጉዳይና የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዛሬው ዕለት በበይነ መረብ ስብሰባ አካሂደዋል። ስብሰባው በደቡብ አፍሪካ የዓለም አቀፍ ግንኙነትና ትብብር ሚኒስትር እና የአፍሪካ ሕብረት አስፈጻሚ ምክር ቤት ሊቀመንበር ሰብሳቢነት ተካሂዷል።

ሚነስትሮቹ የህዳሴ ግድብ ድርድር በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ያደረጉ ሲሆን፤ ስብሰባው ባሳለፍነው ሳምንት እንዲካሄድ ስምምነት ተደርሶበት የነበረው ቢሆንም ሱዳን ባለመገኘቷ ምክንያት ሳይካሄድ ከቀረ በኋላ የተካሄደ ነው ተብሏል።

የአፍሪካ ሕብረት አስፈጻሚ ምክር ቤት ሊቀመንበር ድርድሩን ለማስቀጠል እንዲረዳ በሚል ሀገራቱ ለሶስት ቀናት ከአፍሪካ ሕብረት ባለሙያዎች ጋር የሁለትዮሽ ስብሰባ እንዲያካሂዱ፤በማስከተል የሶስትዮሽ ስብሰባ እንዲካሄድ እና ውጤቱ ለሊቀመንበሯ እንዲገለጽ ሀሳብ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያና ግብጽ ይህን ተቀብለው ለመቀጠል የተስማሙ ሲሆን፣ ሱዳን ሀሳቡን ባለመቀበሏ ስብሰባው በዚሁ መጠናቀቁም ተገልጿል።

ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ስብሰባ ሱዳን የሶስትዮሽ ስብሰባ እንዳይካሄድና ስብሰባዎች ከአፍሪካ ህብረት ባለሙያዎች ጋር ብቻ እንዲደረጉ አቋም መያዟ ይታወሳል።

ሆኖም፣ በዛሬው ስብሰባ ሀገራቱ ከአፍሪካ ሕብረት ባለሙያዎች ጋር የሁለትዮሽ ስብሰባ ያድርጉ የሚለው ሃሳብ ሲቀርብ፣ ሱዳን የባለሙያዎቹ የተጨማሪ ሃላፊነት በጋራ ካልተዘጋጀ በቀር መካሄድ አይችልም የሚል አቋም መያዟም ተጠቅሷል።

ኢትዮጵያ የሱዳንን ጥያቄ ለመመለስ እንዲቻል በግድቡ ደህንነት፣በመረጃ ልውውጥ እንዲሁም በሌሎች ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ መፍትሔ ለመስጠት ዝግጁነቷን ገልጻ፤ በተጨማሪ አሁኑኑ ውጤታማ እና እንካ ለእንካ መርህ ላይ የተመሰረተ የመረጃ ልውውጥ ለመመስረት ፍቃደኛ መሆኗን አሳውቃለች።

በቀጣይነት የአፍሪካ ህብረት የአስፈጻሚ ምክርቤት ሊቀመንበር ለአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የስብሰባውን ውጤት የሚያቀርቡ ሲሆን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ምክርቤት የሚሰጠው አቅጣጫ እንደሚጠበቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ ያመለክታል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com