‹‹የመተከል ግጭት የህዳሴ ግድብን ለማስተጓጎል በመሆኑ ለመፍትሄው መስራት ይገባል››

Views: 47

በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ እና የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ጥምረት ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች ጋር በአሶሳ ከተማ ተወያይተዋል፡፡

የሀገር ሽማግሌዎች ተወካይ ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኢትዮጵያውን አሻራ ያረፈበት የህዳሴው ግድብ መገኛ በመሆኑ ክልሉ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ማብሰሪያ ነው፤ በአካባቢው ተደጋጋሚ ግጭት እንዲነሳ የሚደረግበት ምክንያትም ይኸው ነውም ብሏል፡፡

ፕሮጀክቱ ቢደናቀፍ የመጀመሪያ ተጎጂ የቅርብ ተጠቃሚ የሆነው የክልሉ ህዝብ እንደሆነም አስረድቷል፡፡

የሀገር ሽማግሌዎች በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሲዘዋወሩ በየቦታው የሚከሰቱ ግጭቱ ዘላቂ መፍትሔ እንዲኖረው አመራሮች በኃላፊነት እንዲሠሩ ጥያቄ እንደሚያቀርብም ጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና የሀገር ሽማግሌዎች ጥምረት ምክትል ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በበኩላቸው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በህዳሴው ግድብ ምክንያት የዓለምን ትኩረት ስቧል ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በክልሉ ትምህርት እና መሠረተ ልማት በሚገባ ያላገኙ ነዋሪዎችን ህይወት ይቀይራል ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን ኀብረተሰቡ በክልሉ ተደጋጋሚ ግጭት እንዲነሳ የሚደረገው የልማቱ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ለማድረግ እንደሆነ መረዳት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ሀገር ሽማግሌዎች እንደ ክልል ብቻ ሳይሆን እንደሀገር የገጠመውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት የሃይማኖት አባቶች፣ ቤተሰብ፣ ትምህርት ቤት እና መንግስት የሚጠበቅባቸውን መወጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡

የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር አዳሙ ጅባት እንዳሉት ክልሉ በሚጠበቅበት ደረጃ አለመልማት ለጸረ ሠላም ኃይሎች ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልፀው ሕገወጥ የጦር መሳሪያንም መቆጣጠር እንደሚያስፈልግ እንዲሁም ለወጣቱ ስራ እድል መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ጉባዔ የበላይ ጠባቂ ተቀዳሚ ሙፍቱ ሃጂ ዑመር የሰው ልጅ በሰውነቱ ሊከበር እንደሚገባው ገልፀዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት ስለመተከል ግጭት ግንዛቤ ማግኘታቸውን በመጥቀስም መንግስት እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ለችግሩ የመፍትሔ እርምጃ እንዲወስዱ እንሠራለንም ነው ያሉት፡፡

ሀገሪቱ በብዙ ፈተና ውስጥ ናት ያሉት በኢትዮጵያ የሃይማኖት ጉባዔ እና የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ጥምረት ሞት እና ስደት እንዲበቃ ሁሉም በአንድ ሃሳብ መስራት አለበት ሲሉ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com