ቻዮቴ፣ የጉበት ስብ ማስታገሻ ፍሬ-አትክልት

Views: 153

መግቢያ፡-

ቻዮቴ ድንች ለምኔ የሚያሰኝ ምርታማ ተክል ነው፡፡ ፍሬው እንደ ፍራፍሬ ሲሆን፣ ለአመጋገብ ግን እንደ አትክልት ነው፡፡ ስለዚህ፣ ፍሬ-አትክልት ቢባል ጥሩ ነው፡፡  ቻዮቴ በሳይንሳዊ ስሙ Sechium edule  ይባላል፡፡ ቀደምት መገኛው ሜክሲኮ ቢሆንም፣ በደቡብ ምዕራብ አሜሪካ በብዛት ይገኛል፡፡ ሐረጋማ፣ ተንጠልጣይ ተክል ነው፡፡ አበቃቀሉ እንደ ዱባ ሆኖ፤ ቻዮቴ ግን በአጥር ላይ፣ በዛፍ ላይ ወይም በቆጥ ላይ ተንጠላጥሎ ማደግ ይወዳል፡፡ እንደ ዱባ መሬት ለመሬት ለማደግ አይመቸውም፡፡ ቦታው ከተመቸው እና በአግባብ ከተያዘ ለብዙ ዓመታት ምናልባትም ከ 1ዐ እስከ 4ዐ ዓመታት  ምርት እየሰጠ መቆየት ይችላል፡፡ በአንድ አመት ውስጥ ብዙ ሐረግ ሆኖ ቆይቶ፣ ማፍራት ይጀምራል፡፡ ፍራፍሬው ብዙ ጊዜ የታወቀው ዓይነት ከላይ በምስሉ የሚታየው ዓይነት ትንንሽ ቅል (ወይም ፒር የመሰለ) ቅርፅ አሉት፡፡ ሌላው ዓይነት ደግሞ የታጠፉ የሰው እጅ ጣት የመሰሉ ናቸው፡፡

1. ለምርታማነት የሚፈልገው ኹኔታ

ደጋ እና ወይናደጋ አካባቢ ይመርጣል፡፡ ከፍተኛ ደጋ መሬት፣ በቀዝቃዛ አየር አያድግም፡፡   አፈሩ በተፈጥሮ ፍግ የዳበረ፣ ለስላሳ፣ ዘወትር ከፍተኛ ውሃ የሚያገኝ፣ በቂ የፀሐይ ብርሐን እና ሙቀት ይወዳል፡፡ የውሃ እጥረትን አይቋቋምም፡፡ ዝናብ ከሌለ በየቀኑ ውሃ ማጠጣት ያስፈልጋል፡፡  በቆላ አካባቢ ከሥሩ ለም አፈር እና  ዘወትር ውሃ የሚያገኝ ከሆነ በጥሩ ሁኔታ ያድጋል፡፡ በተመቸው ቦታ ላይ እስከ 12 ሜትር ወይም ከዚያ በላይ ሊያድግ ይችላል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲተከል ከ 8 ወራት በኋላ ያፈራል፡፡ አንዴ መሬት ከያዘ ግን በዓመት እስከ 3 ጊዜ ሊያፈራ ይችላል፡፡ በአንድ ዙር ምርት ከሰጠ በኋላ ሐረጉ ይቆረጣል፡፡

ቻዮቴ ቅጠሉ እንዲህ ነው፡፡

ከአንዱ ተክል ላይ በአንድ የምርት ጊዜ እንደ አያያዙ ኹኔታ ከ 2ዐ እስከ 1ዐዐ ፍሬ ሊያፈራ ይችላል፡፡ አንዱ ፍሬ ከ 2ዐዐ ግራም እስከ አንድ ኪሎ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ቻዮቴው የተንጠላጠለበት ዛፍ ወይም አጥር መሸከም የሚችል መሆን አለበት እንጂ፣ ሁለቱም ሊወድቁ ይችላሉ፡፡

የሚፈልገው ጥንቃቄ፡-

መሬቱ ካልተመቸው፣ ከፍተኛ ጥላ ከበዛበት ግን ከቶም ሊደርቅ ይችላል፡፡

2. የሚተከለው፡-

ለማባዛት የሚተከለው እራሱ ፍሬው ሲያጎነቁል ነው፡፡ ተሰብስቦ ሲቆይ በጎንቆል ይጀምራል፡፡

ከዚሁ ላይ በአንድ በኩል ወደላይ ሐረግ ሆኖ፣ በሌላ በኩል ሥር ሆኖ ያድጋል፡፡ ለመትከል የተመረጠውን ቦታ እስከ አንድ ሜትር መቆፈር እና በፍግ እና የዳበር አፈር መሙላት ነው፡፡ሥር ባወጣው በኩል አፈር እንዲይዝ አድርጎ ከላይ መትከል ነው፡፡

3. የምግብ ጠቀሜታው

  • ፍሬውን ልክ እንደ ድንች አብስሎ ወይም ለጋ ጥሬውን በሰላጣ ዓይነት ለምግብነት ማዋል ይቻላል፡፡
  • ለጋ ቅጠሉን እንደ ጎመን አብስሎ መመገብ ይቻላል፡፡
  • ጠንካራ ቅጠሉን አድርቆ ማቆየት እና የዕፀዋት ሻይ ማፍላት ይቻላል፡፡

እንደ ድንች ጤናን አያቃውስም፡፡ ለጤና የተመቸ ፍሬአትክልት ነው፡፡

4. የጤና ጠቀሜታው

4.1 ለእናቶች

ፎሌት(Folate) የተባለ ንጥረ ነገር ስለያዘ ለእርጉዝ እናቶች ወይም ማርገዝ ለሚፈልጉት ይረዳቸዋል፡፡  ይህ ፎሌት የተባለ ንጥረ ነገር ለጽንሱ የአንጎል እድገት እና የጀርባ አጥንት ይጠቅማል፡፡

4.2 የጉበት ጤና ያሻሽላል

የስብ ክምችት ያለበትን ጉበት ይረዳል፡፡ በጉበት ውስጥ የሚፈጠርን የስብ ክምችት (fatty liver disease) ለመከላከል ይረዳል፡፡ ፋቲ አሲድ ጥርቅም ይቀንሳል፣ ኮልስትሮልን ይቀንሳል፡፡ በጉበት ውስጥ ያለ የስብ ክምችት እራሱ በብዙ ምክንያት ከልክ በላይ ይከማቻል፡፡ ይህ የሰው ጤናን ያቃውሳል፣ ለአደጋም ያጋልጣል፡፡ እባካችሁ በዚህ ህመም የምትሰቃዩ ሰዎች ቻዮቴን ቀን በቀን አንድ ፍሬ ተመገቡ፣ ሌላ የጉበት ጠንቅ ቀይ ሻይ፣ ስኳር ወዘተ የተባሉትን ከምግባችሁ አስወግዱ፡፡

4.3 ለልብ ጤና ይለግሳል

ድሮ የሜክሲኮ ሰዎች በባሕላዊ ዘዴ የልብ ሕክምና ይሰጡበት ነበር፡፡ የኮልስትሮል መጠን ይቀንሳል፣ የውስጥ ብግነት ያበርዳል፡፡

4.4 የደም ስኳር ያስተካክላል፣

ካርቦሐይድሬቱ ዝቅተኛ ሆኖ አሠሩ የተሻለ ስለሆነ፣ ይህ ለጤናማ የደም ስኳር ይዘት ይረዳል፡፡ ትንሽ ሲመገቡት ያጠግባል፡፡ ለስኳር ታማሚ የተመረጠ ምግብ ነው፡፡

ማጠቃለያ፡-

ቻዮቴ አዲስ አበባ ውስጥ በተለያየ ቦታ ይገኛል፡፡ አንድ ፍሬ ብታገኙ ትከሉ፡፡ ወሎ ሠፈር ያለው አትክልት ተራ አልፎ አልፎ ይገኛል፡፡ ለመድኃኒትነት እጅግ በአስቸኳይ የሚፈልገው ሰው ከደቡብ ምዕራብ የአሜሪካ ግዛት ማስመጣት ወይም እዚያው ሄዶ መመገብ ይበጀዋል፡፡  በተለይ ለጉበት ስብ ክምችት በቀላሉ መድኃኒት ማግኘት ስለማይቻል፤ ቻዮቴ ፈውስ ሆኖ ሲገኝ እጅግ መልካም ዜና ነው፡፡ ለበቂ መረጃ ከታች ባለው ሊንክ ይበልጥ አንብቡ፡፡

ቻዮቴን ትከሉ፤ ጤናችሁን ተንከባከቡ፡፡

ማጣቀሻ፣

https://www.webmd.com/diet/health-benefits-chayote#1

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com