ብረት-ድስት፣ ዘይት እና በርበሬ ወጥን እንዴት አፋለሱት?

Views: 209

መነሻ፡-

በተለምዶ ብረት-ድስት በትክክለኛ መጠሪያ ሥሙ ደግሞ ‹‹አሉሚኒየም-ድስት›› ተብሎ የሚጠራው የቤት ቁስ የዛሬ አትኩሮታችን ማጠንጠኛ ነው፡፡ በማዕድ ቤታችን የወጥ-ሥራ በሚከወንበት ወቅት፣ አልሙኒየም-ድስት፣ የዘይትና የቀይ ሽንኩርት ቁሌት አንድም ሦስትም ሆነው የወጥ-ቀውስ እና የጤና-ቀውስ ማስከተላቸው በብዙኃኑ ተገልጋይ ዘንድ ገና አልተነቃባቸውም፡፡

በሀገራችን ወጥ ዋና የእንጀራ ማባያ ነው፡፡ ወጥ ለመሥራት ከሚያስፈልጉ ጥሬ ዕቃዎች ዘይት፣ ቀይ ሽንኩርት፣ በርበሬ፣ ጨው፣ እና ሌሎችም ናቸው፡፡ ይህ ለሁሉም ሰው ግልጽ ነው፡፡ ግልጽ ያልሆኑ ነገረ ጉዳዮች ግን የአገራችን ወጥ በአሉሚኒየም ብረት ድስት ውስጥ፤ ቀይ ሽንኩርት፣ ዘይት እና በርበሬ ስንት ቃጠሎ እየደረሰባቸው እንደሚሠሩ እና እኒህም ምን ዓይነት የጤና ቀውስ እንደሚያስከትሉ አለመረዳታችን ነው፡፡ በእኛ ዘንድ የወጥ ቅመማ እና የወጥ አበሳሰል ቀውስ ስንት የጤና ቀውስ እንደሚያስከትል ገና ብዙ አልተረዳንም፡፡ ንፁህ ውሃ ለጤና፣ ንፁህ ምግብ ለጤና እንደምንለው ሁሉ፤  ጤነኛ የወጥ አሠራር ለጤና ማለት አለብን፡፡

የችግሩ ምንጭ፡-

ሀ/ ወጥ ለመሥራት ሲጀመር ቀይ ሽንኩርት፣ ዘይት እና  በርበሬ በአሉሚኒየም ብረት ድስት ለረዥም ሰዓት ሲቁላላ ቆይቶ ለምግብነት መቅረቡ ነው፡፡

ለ/ አሉሚኒየም ቀላል ብረት ነው፡፡ በብዙ ዘርፍ ባለጠቀሜታ ነው፡፡ ነገር የመጣው ከአሉሚኒየም የተሠሩ ዕቃዎች ለምግብ ማብሰያ፣ ማስቀመጫ እና መጠቅለያ ሥራ ላይ በመዋላቸው ነው፡፡

አሉሚኒየም በሌሎች አገራት ለምግብ ማብሰያ፣ ማስቀመጫ እና መጠቅለያ ሥራ ላይ እንዳይውል በህግ ተከልክሏል፡፡ በእኛ አገር ግን በስፋት የጓዳ ሥራ ላይ መዋሉ ብዙ ስጋት ያስከትላል፡፡

የችግሩን መነሻ አንድ በአንድ እንመልከት፤

 1. የዘይት የጤና ቀውስ

ዘይት ከተሠራበት ጥሬ የእርሻ ምርት ዓይነት የተነሳ ጥራቱ ከፍተኛ ልዩነት አለው፡፡ ቀጥሎም ዘይቱ በፋብሪካ ደረጃ የተሠራበት የአመራረት ዘዴው ብዙ ልዩነት አለው፡፡ ዘይቱ በከፍተኛ ሙቀት ተጨምቆ ቢሆን፣ ወይም በቀዝቃዛው ተጨምቆ ቢሆን ልዩነት አለው፡፡ ሙቀት ያልጎዳው ተመራጭ ነው፡፡  ዘይቱ ተመርቶ የታሸገበት ዕቃ፣ አያያዙ፣ ሁሉ ብዙ የጥራት ችግርን ያስከትላል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ እቤት ከደረሰ በኋላ ለረዥም ጊዜ በከፍተኛ ሙቀት ሲቁላላ ቆይቶ ለምግብነት ሲቀርብ ዳፋው ብዙ ነው፡፡ ለግንዛቤ ይረዳችሁ ዘንድ “ዘይት ለምን እንዴት፡ በሚል ርዕስ በዚህ https://ethio-online.com/archives/5914    ሊንክ ላይ አንብቡ፡፡

 1. የአሉሚኒየም የጤና ቀውስ (ማጣቀሻ አንድ)

አሉሚኒየም በቅድሚያ የሚያገኘው  አየርን፣ ውሃን እና አፈርን በመሆናቸው የተነሳ  በዋናነት ወደ ሰውነት የሚሰርገው በሥርዓተ ምግብ መስመር ነው፡፡ እንዲሁም በሳንባ እና በቆዳ ነው፡፡ በመቀጠል በሰውነት ቲሹ ውስጥ ይጠራቀማሉ፡፡

ብዙ ጊዜ የቧንቧ ውሃ የሚጣራው በአንድ ወይም በሁለቱም ማለትም፤ አሉሚኒየም ሰልፌት እና አሉሚኒየም ፍሎራይድ ሲሆን እኒህ ሁለቱ ኬሚካሎች እርስበርሳቸው በደም ውስጥ ይዋሃዳሉ፡፡ በተጨማሪም አሉሚኒየም ፍሎራይድ አንዴ ከተከሰተ በቀላሉ በሽንት እንኳ አይወገድም፡፡ በተፈጥሮ በተለያየ መጠን በሁሉም ምግብና መጠጥ ውስጥም ይገኛል፡፡

የሚገርመው በእኛ አገር አሉሚኒየም በዚህ ዘመን  ለምግብ ማብሰያ በከፍተኛ ሁኔታ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ አሉሚኒየም ብረት ድስቶች በገበያው ላይ፣ በየጓዳችን ሞልተዋል፡፡

የአሉሚኒየም ማብሰያ ድስት ለብዙ ጊዜ መጠቀም ብዙ አሉሚኒየም ውሁድ ወደ ምግብ እንዲገባ ያደርጋል፡፡ ያም ወደ ሰውነት ገብቶ ይሰርጋል፡፡ አሉሚኒየም በቀላሉ የሚሟሟው አሲድነት ፈጣሪ በሆኑት ምግቦች በእነ ቡና፣ አይብ፣ ስጋ፣ ሻይ፣ ጥቅል ጎመን፣ ዝኩኒ፣ ቲማቲም፣ ተርኒፕ፣ እስፒናች፣ ራዲሽ እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡

አሲዳማ ዝናብ አሉሚኒየምን ከአፈር ውስጥ አጥቦ ወደ መጠጥ ውሃ እንዲገባ ያደርጋል፡፡

         2.1 ከአንጎል ጋር ያለው ችግር  (ማጣቀሻ አንድ)

አሉሚኒየም የበዛ መጠን ወይም ሌላው ቀርቶ በትንሸ መጠን እንኳን ወደ ሰውነት ውስጥ ገብቶ በሰው አንጎል (brain) እና በነርቭ ቲሹ  ውስጥ ይጠራቀማል፡፡ የበዛው ጥርቅም መርዛማ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ማለት በአንጎል ውስጥ የአሉሚኒየም ጥርቅም የአእምሮን ሥራ ያስተጓጉላል፡፡ አሉሚኒየም በደም ውስጥ  ወደ እዚህ ወሳኝ አካል አንጎል ከመድረሱ በፊት የግድ መከላከያ በሆነ የማጣሪያ ክፍል ውስጥ ማለፍ አለበት፡፡ ምንም እንኳን ይህ ማዕድነ አሉሚኒየም በዚህ ተከላካይ ውስጥ ማለፍ ባይችልም ጥቂት የአሉሚኒየም ውሁድ ለምሳሌ አሉሚኒየም ፍሎራይድ (aluminium florid) ሊያልፍ ይችላል፡፡

        2.2 የአሉሚኒየም ጥርቅም የሚያስከትለው የበሽታ ምልክቶች  (ማጣቀሻ አንድ)

የአሉሚሊየም መርዝነት የሚያስከትለው ብዙ የበሽታ ምልክቶች ከአልዛይመር በሽታ እና ከአጥንት መሳሳት በሽታ ምልክቶች ጋር ይመሳሰላሉ፡፡

የአሉሚኒየም መርዝነት ጤናን በማቃወስ፣

 • ኮሊክ የተባለ የአንጀት ውስጥ በሽታ፣
 • ሪኬት
 • የጨጓአንጀት ጤና ማጣት
 • ደካማ የካልስየም ስርፀት
 • የበዛ ተቆጪ መሆን
 • ደም ማነስ
 • ራስ ምታት
 • ለደካማ የጉበት እና የኩላሊት ተግባር
 • ዝንጉ መሆን
 • ያልተስተካከለ ንግግር
 • የአስተውሎት ማነስ
 • የአጥንት መሳሳት እና ደካማ መሆን
 • የጡንቻ ማሳከክ ወዘተ ያስከትላል፡፡

አሉሚኒየም ከሰውነት የሚወገደው በኩላሊት አልፎ ነው፡፡ እናም የአሉሚኒየም መርዛማነት መጠን የኩላሊት ተግባርን ሊያዳክም ይችላል፡፡

2.3 የጤና ቀውሱ በአገራችን

ከላይ የተጠቀሱት የአሉሚኒየም ችግሮች በሌሎች አገራት የተደረገ ጥናት ውጤት ናቸው፡፡ በእኛ አገር ምን የጤና ቀውስ አስከትሎ ቢሆን የተጠና ነገር አልሰማሁም፡፡ ብዙ ሰዎች መፍትሔ ባልተገኘላቸው ሕመም ሲሰቃዩ እናያለን፡፡ ሆኖም ከአሉሚኒየም የጓዳ መገልገያ ጦስ የተነሳ ቢሆን ወይም በሌላ ለማወቅ ከአቅማችን በላይ ነው፡፡ እናም ለጉዳዩ የጠለቀ ዕውቀት  ባይኖረንም፣

ሀ፤ ከአሉሚኒየም ዕቃ በጓዳችን መጠራቀም የተነሳ፣

ለ፤ ዘይት እና ሽንኩርትን፣ በርበሬን ጨምሮ ከመጠን በላይ ከማቁላላት ልማድ የተነሳ፤ እና

ሐ፤ የሸክላ ድስቶች ከጓዳ ካለመኖራቸው የተነሳ፣

እነዚህ “በሌላ አገራት የተወሱ የጤና ቀውሶች በእኛም ላይ ተከስተው ይሆናል”  ብሎ መጠራጠር ተገቢ ይሆናል፡፡

ብዙ አጠራጣሪ ክስተቶች ይታያሉ፣ ለምሳሌ

 • አንዳንድ ሰዎች በምርመራም በቀላሉ የማይገኝ የሆድ ውስጥ የጤና እክል ያጋጥማቸዋል፤
 • “የጨጓራ በሽታ ነው”  እየተባለ የተለያየ መድኃኒት ሲወስዱ ቆይተው የጨጓራ ሕመሙ እራሱ የመጣው ያልተገባ መድኃኒት በመውሰድ ሆኖ ይገኛል፤
 • አልኮል ጠጪ ያልሆኑ፣ ሲጋራ የማያጨሱ፣ ጫት የማይቅሙ ሰዎች፤ ዓይነቱ በውል ባልተለየ የሆድ ውስጥ ሕመም ሲሰቃዩ ይስተዋላል፤
 • በኑሮአቸው ውስጥ የምግብ መጓደል ችግር ሳይከሰት፤ ነገር ግን ከሲታ፣ አጥንታቸው የሳሳ ሰዎችን ማየት እየተለመደ መጥቷል፤
 • አልዛይመር መሰል በሽታ እየተበራከተ መጥቷል፣
 • ሌላም ብዙ ውስብስብ ችግር በቤተሰብ ውስጥ ይታያል፡፡

ለማረጋገጥ የችግሩ መነሻ ከአሉሚኒየም ድስቶች የተነሳ ሊሆን ይችላል? ወይም በሌላ ምክንያት ሊሆን ይችላል?  ቢባል ጥናት ይፈልጋል፡፡

2.4 መፍትሔው፡-

 • ከላይ እንደተጠቀሰው አሉሚሊየም ወደ ሰውነት የሚገባው በተለያየ መንገድ ቢሆንም፤ እኛን ግን በእጅጉ ለዚህ ችግር የሚዳርጉን የአሉሚኒየም የብረት ድስቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አከራካሪ እና አደናጋሪ ያልሆነው አንዱ ሁነኛው እና ቀላሉ መከላከያ  ዘዴ፤ የሸክላ ድስቶች ናቸው፡፡ የሸክላ ድስት ወይም የሸክላ መቀቀያ ዕቃ ለሁሉም ምግብ ማብሰያ ተመራጭ ናቸው፡፡ የቀደመው የዕደጥበብ ውጤት፤ ዘመን ተሻጋሪ እና ዘመን አይሽሬው የወጥ መሥሪያ ለእኛ የሸክላ ድስቶች ናቸው፡፡  በቀላሉ ከገበያ ላይ መግዛት ይቻላል፡፡ በሚፈልጉት መጠን በትዕዛዝ ማሠራት ይቻላል፤ በውጪ ምንዛሪ አይገዙም፣ አገራዊ ናቸው፡፡ ከታሰበበት  ሰፊ አማራጭ አለ፡፡
 • የሸክላ ዕደጥበብ ሙያተኞች ብርሃናማ ገበያ እየመጣ መሆኑን ልብ በሉ፡፡ ሥራችሁን እጅግ አሻሽሉ፣ በዓይነት በመጠን ለይታችሁ ገበያውን በሽ በሽ አድርጉት፣
 • ሌሎችም እንደ አረብ ብረት ያሉት የተሻሉ ድስቶች ናቸው፣ ነገር ግን ከሸክላ ድስት በላይ ተመራጭ አይደሉም፡፡
 • የአሉሚኒየም ድስት አምራቾች ጉዳዩን አጥኑት፤ አስጠኑት፤ አሉሚኒየምን ለሌላ አማራጭ የምርት ውጤት ተጠቀሙ፡፡
 • የሸክላ ድስቶችን ወደ ጓዳ ስታስገቡ፤ ቀደም የተሰበሰቡ የአሉሚኒየም ድስቶችን ሌላ ሙያ ፈልጉላቸው፡፡
 • እስከዛሬ በሆነው የአበሳሰል ስርዓት ለተከሰተው የውስጥ አካል ችግር ከዚህ በኋላ በምንም መንገድ በአሉሚኒየም ድስት የተሠራ ምግብ አለመመገብ እና በሸክለ የበሰለ ምግብ እና ብዙ አሠር ያለው ምግብ መመገብ፡፡
 1. ቀይ ሽንኩርት ሌላው የወጥ ጥሬ ዕቃ

3.1 የቀይ ሽንኩርት የጤና ጥቅሞች ማጣቀሻ ሁለት

 • የካሎሪ ይዘቱ ዝቅተኛ ሲሆን በቫይታሚን ሲ እና ቫይታሚን ቢ የዳበረ ነው፣
 • በፖታስየም ማዕድን የዳበረ ነው፡፡
 • ቀይ ሽንኩርት ኮልስትሮልን በመቀነስ ለልብ ጤና ይጠቅማል፡፡
 • የደም ግፊትን ይቀንሳል፣ የደም መርጋትን ይቀንሳል፣
 • የጨጓራን፡ የሳንባን፡ ነቀርሳ ይፋለማል፣ ይከላከላል፡
 • የደም ስኳርን በመቆጣጠር ለስኳር በሽተኞች ጤና ይረዳል፣
 • ከሌሎች ምግቦች ጋር በመሆን ለአጥንት ጥንካሬ ያግዛል፣
 • የጤና ችግር የሚያስከትሉትን መጥፎ ባክቴሪያ ይፋለማል፣
 • የምግብ ስልቀጣን ያቀላጥፋል፡፡

3.2 ቀይ ሽንኩርት የአበሳሰል ዘዴ ማጣቀሻ ሶስት

ለጤና እንዲጠቅም  ሽንኩርቱን በሸክላ ድስት ጨምሮ፣ ትንሽ ጨው እና ውሃ አክሎ ዝግ ባለ ሙቀት ማፍላት ነው፡፡ አሥር (1ዐ) ደቂቃ ውስጥ ይበስላል፡፡

ከልክ በላይ ሲበስል እነዚህን የተነገሩለትን የጤና ጥቅሞች እና የንጥረ ምግብ ይዘት ሊያጣ ይችላል፡፡  ከዚህም በላይ የጤና ቀውስ ሊያስከትል ይችላል፡፡ ለምሳሌ ቀውሱ፣ በጨጓራ እና አንጀት ላይ ወይም በሥርዓተ ምግብ ሥልቀጣ ላይ  ሊከሰት ይችላል፡፡

 1. በርበሬ

በርበሬ በአፍላቶክሲን  እየተበከለ የጤና ቀውስ ማስከተሉ የታወቀ ነው፡፡ በአንዳንድ ጥናት ለይ  እንዲህ ይብራራል፤ “የበርበሬ ዛላው ወይም ዱቄቱ እንደሌሎቹ የእርሻ ምርት ለሻገታ ልክፍት (fungal infection) የተጋለጡ ናቸው፡፡ ቀጥለውም የሻገታ ልክፍቶቹ አንድ ዓይነት ወይም ብዙ ዓይነት ማይኮቶክሲንስ የተባሉ የሻገታ ምርዝ ብክለት (mycotoxin contamination)  ያስከትላሉ፡፡

የበርበሬ ዛላ ምርቱ በሚሰበሰብበት ጊዜ እና ከተሰበሰበ በኋላ፣ በሚደርቅበት ወቅት እና ምርቱ የሚጓጓዝበትን ጊዜ ጨምሮ፣ ብዙ ጊዜ የሚያጠቁት የተለያዩ የሻገታ ዝርያዎች አሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አስፐርጊሉስ እና ፐኒሲሉም የሚባሉት በካይ ዝርያዎች (Aspergillus and Penicillium species) በዋናነት ይገኛሉ፡፡ ማይኮቶክሲንስ ማለት የብዙ ዓይነት የሻገታ ልክፍቶች በአንድነት የሚጠሩበት ጥቅል ስም ሲሆን ሲሆን፣ ከእነሱም ውስጥ ቀደምት ጥናቶች የሚነግሩት በኢንዱስትሪ የተቀነባበረ በርበሬ በአፍላቶክሲን (aflatoxins (AFs), ይበከላል፡፡”

የእኛ አገር በርበሬ በአመራረት ሒደት እና በሰው ሰራሽ ችግር የተነሳ  ከሌሉች አገራት የበለጠ የተበከለ ነው፡፡

እንግዲህ ይህንኑ የተበከለ በርበሬ ለወጥ መጠቀማችን ሌላው የወጥ ችግር ነው፡፡ በርበሬአችን እና የአፍላቶክሲን ችግሮች በሚል ርዕስ በዚሁ ዓምድ https://ethio-online.com/archives/2483     በሚለው ሊንክ ላይ በይበልጥ አንብቡ፡፡

 1. ወሳኝ የጤና ጥያቄዎች

ከበርበሬ እና አሉሚኒየም ጋር በተገናኘ ብዙ ጥያቄዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡

ለጊዜው ግን፡-

1ኛ፣ በሌሎች አገራት አሉሚኒየም ብረት ከምግብ ጋር በተያያዘ “ሥራ ላይ እንዳይውል” ተብሎ ሲታገድ፣ በእኛ አገር በስፋት የጓዳ አገልግሎት ላይ እንዲውሉ መፈቀዱ ለምንድነው? ማጣቀሻ አራት፤

2ኛ፣ አሉሚኒየም ድስት ጋር በተያያዘ ያለ የጤና ቀውስ ላይ አገራዊ የሆነ ጥናት ተደርጎ እንደሆነ መረጃው ያለው ይንገረን፤

3ኛ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚመለከታቸሁ ጥያቄዎችን በማንሳት ውይይት ቢደርጉ፤ ጥናት እንዲደረግ ጥረት ቢያደርጉ እጅግ ጥሩ ነው፡፡

4ኛ/ በርበሬ ከምርት ጀምሮ በገበያ አልፎ ጓዳ እስኪደርስ በአፍላቶክሲን የተበከለ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ መንግስት በዚህ ጉዳይ መመሪያ፣ እና አስገዳጅ ደንብ ማውጣት ሲኖርበት ዝም ማለቱ ተገቢ አይደለም፡፡

ማጠቃለያ፡-

ንፁህ ውሃ ለጤና፣ ንፁህ ምግብ ለጤና፣ እንደምንለው ሁሉ ጤነኛ የወጥ አሠራር ለጤና ማለት አለብን፡፡

ችግሮቹ እና ኹነኛ መፍትሔ

                                                                                               

ማጣቀሻ

  አንድ፣https://www.google.com/search?q=side+effect+of+cooking+with+Aluminume+fiolet&ie=utf-8&oe=utf-8&client=firefox-b-ab

ሁለት    https://www.healthline.com/nutrition/onion-benefits#section7

ሶስት     https://www.quora.com › Why-do-cooks-sauté-onions-and-garlic-first

አራት፣   https://addisbiz.com/business-directory/manufacturing-industry/aluminium-cooking-pots

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com