ሥንቅ- የተሰናዳ ምግብ

Views: 300

መነሻ፡-

ሁል ጊዜ እና በሁሉ ቦታ፤ እንጀራ በወጥ፣ ዳባ በሻይ፣ ገንፎ በቅቤ፣ ቆጮ በክትፎ ለማግኘት ወይም አዘጋጅቶ ለማቅረብ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ ለዚሁ ተብሎ እንደ አግባቡ ቀድሞ የተዘጋጀውን የስንቅ ምግብ መጠቀም ግድ ነው፡፡ ስለ ሥንቅ ትርጉም ብዙ ማብራራት የሚቻል ቢሆንም፣ በቀላሉ ለጥቂት ቀናት ተብሎ  የሚያዝ የበሰለ ምግብ ስንቅ ይባላል፡፡ ከፍ ብሎ ሲነገር ደግሞ ለወራት ሊቆይ የሚችል የተሰናዳ ምግብ ሁሉ ስንቅ ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ትኩረት የሚደረገው በአስቸጋሪ ቦታ ወይም በአስቸጋሪ ቀናት ለምግብነት የሚውል ስንቅ ስለማዘጋጀት እና ጠቀሜታው ነው፡፡  

ስለ ስንቅ ዝግጅት ገለፃ፡-

የሚዘጋጀው ስንቅ በንጥረ ምግብ ይዞታው ወይም ምጥነ-ህላዊ   (nutrient rich ) የተሻለ መሆን አለበት፡፡ ከዚያም ባመቸ ጊዜ ሲመገቡት የጣመ እና ተስማሚ፣ በትንሹ ሲመገቡት የሚበቃ፣ ለብዙ ጊዜ ሳይበላሽ የሚቆይ መሆን አለበት፡፡ ለምግብነት ሲያውሉት በቀላሉ ከታሸገበት ተከፍቶ ወይም ከታሰረበት ተፈቶ፤ በደረቁ የሚበላ፣ በውሃ ተርሶ የሚበላ ወይም በውሃ ተበጥብጦ የሚጠጣ ሊሆን ይችላል፡፡

ለምሳሌ በአገራችን በተለምዶ ለረዥም ጊዜ የሚቆዩ የሥንቅ ዓይነት፤

 • የእንጀራ ድርቆሽ፣ እስከ 6 ወራት ይቆያል
 • የእንጀራ ሊጥ እና ሥጋ ወጥ በአንድነት ተጋግሮ ድርቆሽ እንጀራው፣ እስከ 3 ወራት ይቆያል፡፡ ይህን በፈላ ውሃ ጨምሮ መመገብ ብቻ ነው፡፡
 • የሥጋ ድርቆሽ ማለትም ቋንጣ፣ እስከ 6 ወራት ይቆያል፣ ስለ አሠራሩ በዚህ ሊንክ ላይ https://ethio-online.com/archives/6884   ቀይ ሥጋን አድርቆ የማቆየት ዘዴ የሚለውን አንብቡ፡፡
 • የበሶ ዱቄት እንደ ቦታው ከ 3 እስከ 6 ወራት ይቆያል፡፡
 • ጭኮ ማለት በሶ በቅቤ ብቻ ተሰርቶ፣ እንደ አያያዝ ከ 6 እስከ 12 ወራት ይቆያል፡፡
 • የቆጮ (እንሰት) ድፎ ዳቦ፣ እስከ 6 ወራት ይቆያል፡፡

እና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ለዚህ እና መሰል የሥንቅ ዝግጅት በዋናነት የእህል ስብሎችን በአግባብ አብስሎ፣ አመጣጥኖ መቀየጥ እና ቅመም ጨምሮ  ማስፈጨት እና  ጨው፣ ቅቤ ወይም ዘይት ጋር ማሰናዳት እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡

ለምሳሌ፡-

ከብርዕ አዝመሮች እንደ  ገብስ፣ ጤፍ፣ ዳጉሣ፣ አጃ፣ ስንዴ እና የመሳሰሉት፣

ከአገዳ እህል  እንደ ማሽላ፣ በቆሎ ያሉትን

ከአዝርት  እንደ  ባቄላ፣ ሽንብራ፣ አኩሪ አተር እና መሰሎቹን፣

ከሥራሥር     እንደ እንሰት፣ ጎደሬ፣ እና ሌሎች ያሉትን

       በማብሰል፣ በማመጣጠን እና በመቀመም ግሩም ስንቅ ማዘጋጀት ይቻላል፡፡

ሀ) ሥንቅ ለማዘጋጀት ምን ቅድመ ሁኔታ ይኑረው?

 • ጥራት ያለው፣
 • ንጥረ ምግቡ የተሻሻለ፣
 • ረዥም ጊዜ ሳይበላሽ፣ ጣዕሙን ሳይቀይር የሚቆይ፣
 • በጥሩ ሁኔታ የታሸገ፣
 • ለአጠቃቀም ምቹ እና ቀላል የሆነ፣
 • ጣዕሙ ጥሩ የሆነ፣
 • ለጤና ተስማሚ የሆነ፣ እና
 • ሌሎችም ጠቃሚ መስፈርት ያሟላ ቢሆን ይመረጣል፡፡

ለ) ሥንቅ በምን ደረጃ (መጠን) ሊሠራ ይችላል?

 • በቤተሰብ ደረጃ በትንሽ መጠን፣
 • በባልትና ደረጃ በብዙ መጠን፣
 • በፋብሪካ ደረጃ በማቀናበር በከፍተኛ መጠን፣

ሐ) ሥንቅ ለእነማን ሊሆን ይችላል?

 • ለረዥም ጊዜ በገጠር ውስጥ በሥራ ላይ ለሚቆዩ፣
 • በስደተኛ ከምፕ ውስጥ ለሚገኙት፤
 • ለወታደር፣ ዘመቻ ላይ እና መሰል ኃላፊነት ላይ ለተሠማሩት፣
 • ረዥም የእግር ጉዞ ለሚያደርጉት፣
 • በተለያየ ካምፕ ውስጥ ለተለያየ ጉዳይ ለሚቆዩት፤

እና ለመሳሰሉት ይሆናል፡፡

መ. ከላይ ከተነሱት ውስጥ በሶን በተግባራዊ ምሳሌ እንመልከት፤

የተሻሻለ በሶ   (ማጣቀሻ አንድ)

በሶ በተለመደው አሠራር የሚዘጋጀው ከተቆላ ገብስ ነው፡፡ በሶ ለአጠቃቀም ቀላል ሲሆን፣ ለመብላት ወይም ለመጠጣት ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ ከተለመደው ከገብስ ብቻ ከማዘጋጀት ይልቅ የንጥረ ምግብ ይዘቱን ማሻሻል ይቻላል፡፡

ይህ ንጥረ ምግብ ይዞታው የተሻሻለ የበሶ ዱቄት የሚከተሉትን የእህል ዘር፣ የአባዝርት  እንዲሁም የቅመም ድብልቆች ሊያካትት ይችላል፡፡

እያንዳንዱን የማዘጋጀት ሂደት እና የሚደባለቀው መጠን

1ኛ/ ገብስ ማዘጋጀት (Barley )

ገብስ ይበጠራል፣ በሞቀ ውሃ ተነክሮ ተጠንፍፎ ያድራል፤ ጠዋት በመጠኑ በፀሐይ ሙቀት ላይ ይሰጣና እንደ ቆሎ ይቆላል፡፡ በእህል ወፍጮ ይሸከሸከል፡ ይበጠራል፡  ይህ የገብስ ቆሎ ከ 5ዐ እስከ 6ዐ ከመቶ ለበሶ ምጥን ይሆናል፡፡

ገብስ የላቀ ካርቦሃድሬት፤ ከፍተኛ ፎስፈረስ እና አሠር ሲኖረው፤ የካልስየም ይዞታው መጠነኛ ነው፡፡

2ኛ/ ጤፍ ወይም ዳጉሳን መርጦ ማዘጋጀት

ጤፍ ለማዘጋጀት (Tef )

በሁለት ዓይነት ጠቅጣቃ ወንፊት ይነፋል፣ በሰፌድ ይበጠራል፡ ከቆሻሻ የነፃ ሲሆን፣ በሸክላ ምጣድ ላይ ታምሶ ይበስላል፡፡ 1ዐ በመቶ ያህል ለበሶ ይመጠናል፡፡

ጤፍ ከፍተኛ  ካልስየም፣ ካርቦሃድሬት፣ ፎስፈረስ፣ የምግብ ኃይል እና ብረት ሲኖረው፤  መካከለኛ ፖታስየም አለው፡፡

ዳጉሣ ማዘጋጀት (Finger millet)

በደንብ ይበጠራል፣ ይታጠባል፣ ይደርቃል፣ ቆሻሻው ይለቀማል፡ በጥንቃቄ ተቆልቶ ይበስላል፡፡  ለበሶ 1ዐ  በመቶ ተመጥኖ ይቀየጣል፡፡

ዳጉሣ የላቀ መጠን ብረት፣ ካልስየም፣ ፎስፈረስ እና ካርቦሃይድሬ አለው፡፡

 ከፍተኛ ፖታስየም፣ ኘሮቲን፣ አሠር እና የምግብ ሐይል አለው፡፡

3ኛ/ ከጥራጥሬ ምርት አማራጭ፡-

 3.1 ሽምብራ ማዘጋጀት (chickpeas)

ሽምብራን በውሃ ነክሮ አጥቦ በፀሐይ ሙቀት ላይ ለ3ዐ ደቂቃ ማስጣት እና ለብ ባለ ሸክላ ምጣድ ማመስ እና አብስሎ ማዘጋጀት፡፡ ለበሶ ከሚዘጋጀው ጋር 2ዐ በመቶ ይመጠናል፡፡ ሽንብራ በከፍተኛ መጠን ፖታስየም፣ ብረት፣ ፎስፈረስ፣ ካልስየም፣ አሠር፣ ቅባት፣ ኘሮቲን እና የምግብ ኃይል አለው፡፡

3.2 አኩሪ አተር ወይም  ባቄላ  ማዘጋጀት (ከሁለት አንዱ ይበቃል)

አኩሪ አተር ማዘጋጀት (Soybean)

አኩሪ አተር ተበጥሮ ይዘጋጃል፡፡  በሸክላ ምጣድ እስኪበስል ይቆላል፡፡  እስከ 1ዐ ከመቶ ይመጠናል፡፡ አኩሪ አተር በላቀ መጠን ፖታስየም፣ ብረት፣ ፎስፈረስ፣ ካልስየም፣ አሠር፣ ቅባት፣ ኘሮቲን እና የምግብ ኃይል አለው፡፡

ባቄላ ማዘጋጀት፣

ባቄላ ተበጥሮ፣ መጠኑ ተለይቶ ይፀዳል፡፡ ይህ በሸክላ ምጣድ ላይ ታምሶ ይበስላል፡፡ 1ዐ ከመቶ ይቀየጣል፡፡ ባቄላ የሥነ ምግብ ይዘቱ ከሽምብራ ጋር ተቀራራቢ ቢሆንም፤ የገብስ በሶ ብቻውን ሲሆን የልብ ቃር እንዳያስከትል ይረዳል፡፡ ሙሉ ባቄላ ሳይከካ ስለሆነ፣ የአሠር መጠኑ ጥሩ ይሆናል፡፡

4ኛ/ ቅመማት ለረዥም ጊዜ ሳይበላሽ ለማቆያ (preservative for long shelf life)  እና ጣዕሙ ጥሩ እንዲሆን ተመጥነው ይጨማራሉ፡፡

4.1 ጦስኝ (Thymus)   ጦስኝ ቆሻሻው ተለቅሞ በፀሐይ ሙቀት ላይ

ይሰጣል፣ በሸክላ ምጣድ ይታመሳል፣ 1 ከመቶ ይደባለቃል፡፡

4.2 ኮሰረት (Ethiopian coseret )  የደረቀ የኮሰረት ቅጠል በቀዝቃዛ ውሃ

ይታጠባል፣ በፀሐይ ሙቀት ላይ ይሰጣል፣ ይደርቃል፣ ዐ.5 ከመቶ

ተመጥኖ ለበሶ እህል ይቀየጣል፡፡

 4.3 ኮረሪማ (cardamom )   ኮረሪማ ተፈልፎሎ፤ ይታመሣል፤ ገለባው

ይበጠራል፤ 1 ከመቶ  ተመጥኖ ለበሶ ይቀየጣል፡፡

4.4 ቀረፋ (Cinnamon)   ቀረፋ ይታጠባል፣ በፀሐይ ሙቀት ላይ ይሰጣል፣

ይታመሣል፡፡ የተስተካከል መጠን እንደኖረው ተሸክሽኮ  2 ከመቶ ተመጥኖ

ለበሶ ይቀየጣል፡፡

 • ጨው. ጣዕሙን ያስተካክላል፣ ለብዙ ጊዜ እንዲቆይም ይረዳል፡፡

ታምሶ 2 ከመቶ የሚሆን ይቀየጣል፡፡

5ኛ/ አመጣጥኖ ማደባለቅ፤ ከላይ የተነገረውን ሁሉ መዝኖ መጥኖ ማደባለቅ፡፡

6ኛ/ ማስፈጨት፣ የተዘጋጀውን ምጥን እህል በሶ በሚፈጭ ወፍጮ በአግባቡ ማስፈጨት፡፡

7ኛ/ በወንፊት ነፍቶ ማሸግ

የበሶ ዱቄቱ በወንፊት በአግባቡ ይነፋል፡፡ ቀጥሎም  ለምግብ ተብሎ የተዘጋጀ የምግብ ማሸጊያ ከረጢት ውስጥ፣ (ቢቻል ቀድሞ በአልኮል ይፀዳል፤ አልኮሉ ከደረቀ በኋላ) ዱቄቱ እየተለካ ይጨመራል፤ ይታሸጋል፡፡

ሠ. የበሶው ቆይታ ጊዜ

በዚህ አሠራር የተዘጋጀው በሶ በሞቃት አካባቢ ከ 2 እስከ 3 ወራት ይቆያል፡፡ በጣም ቀዝቃዛ በሆነ ደጋማ አካባቢ ከ 6ወራት በላይ ሊቆይ ይችላል፡፡

ረ. የበሶው አጠቃቀም

ይህ በሶ ንጥረ ምግቡ የተሻሻለ ስለሆነ በትንሹ ሲመገቡት ያጠግባል፡፡

በቀላሉ ለመጠቀም፡-

 • በትኩስ ውሃ እና በዘይት ወይም በቅቤ ሠረቶ መብላት ይቻላል፡፡ ወይም በንፁህ ውሃ በጥብጦ መጠጣት ይቻላል፡፡ አስፈላጊ ከሆነ ስኳር መጨመር ነው፡፡
 • ለአንድ ሰው ለአንድ ጊዜ ከ 5ዐ እስከ 1ዐዐ ግራም በቂ ነው፡፡
 • አንድ ሰው ከ 3 እስከ 6 ቀናት  አንድ ኪሎ ሊጠቀም ይችላል፡፡
 • በአስቸጋሪ ቦታ ላይ ለሚገኙት በኪሎ የታሸገውን ለማከፋፈል አመቺ ነው፡፡
 • 1 ኪሎ በሶ በአንድ ጊዜ ሠርቶ ለማቅረብ ቢያስፈልግ  ከ1ዐ እስከ 2ዐ ለሚሆኑት በቂ ነው፤
 • በዚህ ስሌት አንድ መቶ ኪሎ በአማካይ ለአንድ ጊዜ ለ15ዐዐ ሰዎች ይበቃል፡፡

ሰ. ጭኮ

ይህ የተሻሻለው በሶ ዱቄት ጭኮ ለማዘጋጀትም ይውላል፡፡ ጭኮ የሚሠራው የተነጠረ አንድ ኪሎ ቅቤን አቅልጦ፣ በአንድ ኪሎ የበሶ ዱቄት ደህና አድርጎ ማሸት እና ማዋሃድ ነው፡፡ ከላይ ትንሽ ቅቤ ፈሰስ ማድረግም ይቻላል፡፡ ይህ ጭኮ እንደዚህ ተሠርቶ  በሞቃት ቦታ እስከ 3 ወር፣ በቀዝቃዛ ቦታ እስከ 6 ወራት እና በማቀዝቀዣ (ፍሪጅ) ውስጥ እስከ አንድ አመት ሳይበላሽ ጣዕሙን ሳይቀይር ሊቆይ ይችላል፡፡ ሁለት ኪሎ ጭኮ ከ 3ዐ እስከ 4ዐ ለሚደርሱ ሰዎች ቁርስ ሊበቃ ይችላል፡፡

ተሠርቶ የቀረበ ጭኮ

ማጠቃለያ፡-

 የእንጀራ ድርቆሽ እና የሥጋ ቋንጣ በአግባቡ አዘጋጅቶ ማድረቅ እና ለስንቅ ማዋል ጥሩ ጉዳይ ነው፡፡

ይህ ለምሳሌ ያህል የቀረበው የበሶ ዱቄትም ጥሩ ስንቅ ይሆናል፡፡ በቤት ውስጥ በትንሽ መጠን ሊዘጋጅ ይችላል፡፡ በባልትና ደረጃ በሰፊው ለብዙ ጥቅም ወይም ለሰፊ ገበያ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ቢታሰብበት፣ በጥናት ጭምር ተደግፎ በፋብሪካ ደረጃ እንደዚህ ቢሠራ ብዙ ሰዎችን በአስቸጋሪ ቦታ እና ጊዜ ሊታደግ ይችላል፡፡

ተጨማሪ ምክር፣

በአገራችን በጥናት እና ምርምር የተደገፈ የበሶ ዱቄት አሠራር የለም፡፡ ነገር ግን ይህንን ከዚህ በተሻለ ሁኔታ ማዘጋጀት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ተጨማሪ ምክር የምትነግሩን ካላችሁ እባካችሁ ችላ አትበሉ፡፡ ጻፉልን፡፡

                                               

ማጣቀሻ አንድ፤ ከ 6 ዓመት በፊት “ስነምግቡ የተሻሻለ የምግብ ዱቄት እና የአዘገጃጀት ዘዴ” በሚል፣ በኢትዮጵያ የአዕምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት ለዩቲሊቲ ሞዴል ምዝገባ አቅርቤ ካስመዘገብኩት ውስጥ ይህኛው በሶ አንዱ ሲሆን፤ ለዚህ ጽሑፍ በሚመች ሁኔታ አሻሽዬው የቀረበ ነው፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com