ዜና

የሰሜን እዝ ሠራዊት ላይ በድንገት ጥቃትና ወረራ የፈጸመው የህወሓት ጽንፈኛ ቡድን የድረሱልኝ ጥሪ በማቅረብ ላይ ነው

Views: 250

ከአለፉት ሁለት አሥር ዓመታት በላይ ትግራይ ላይ ሆኖ ሕዝብንና ኢትዮጵያን ሲጠብቅ የነበረውን የሰሜን እዝ ላይ ጥቃትና ወረራ የፈጸመው ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን፣ ከደቂቃዎች በፊት የድረሱልኝ ጥሪውን በይፋዊ ድረ-ገጹ ላይ አቀረበ፡፡

የድርጅቱ ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል በተጣደፈ መልዕክታቸው፣ ‹‹የኢትዮጵያ ብሔር- ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች፣ ሠራዊቱን ተው አቁም በሉት፤ ትግራይን ከውጭ ኃይል ጋር ሆኖ እየወረረና እየወጋ ነው›› ሲሉ ይደመጣሉ፡፡

የህወሓትን የጥድፊያ ድረሱልኝ መግለጫ ከሥር እንደሚከተለው (እንደ ወረደ) አቅርበነዋልና ይመልከቱ፡-

“አገር በኢሳያስ በተደፈረችበት ጊዜ በትግራይ ደቡባዊ ዞን፣ በራያ በኩል የመከላከያ ሰራዊቱና መሬት አስመላሹ ሰራዊት በጋራ ጦርነት ከፍተዋል። በበርካታ የትግራይ ድንብር አከባቢዎች የሻዕቢያ ሰራዊት ሲወጋን በራያ በኩል ደግሞ የመከላከያ ሰራዊት እየወጋን ይገኛል። በሌሎች ግምባሮችም የኤርትራና የኢትዮጵያ ሰራዊት ሁለቱም በጣምራ እየወጉን በታሪክ እጅግ አሳፋሪ ክህደት እየፈፀሙ ይገኛሉ።” የድርጅታችን ህወሓት ሊቀ መንበር ጓድ ዶ/ር ደብረፅዮን

የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች!

የአብይ አሕመድ ሃይል ትግራይን እንደወረረ ገልጬ ነበር። አሁን ደግሞ የኤርትራ ሰራዊት ከአብይ አህመድ ቡድን በመተባበር ከ16 ክፍለ ጦሮች በላይ አሰልፎ በሁሉም ግንባሮች ወረራ እያካሄደ ይገኛል። ስለሆነም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ህዝብንና ህገ መንግስቱን ለመጠበቅ የተሰጠውን ሃላፊነት ከውጭ የማዳን ተልእኮ የት ገባ? ማለት አለብን። የኢትዮጵያ ህዝብ ካሁን በኋላ “የመከላከያ ሰራዊት አለኝ” እንዳትል። ከእንግዲህ በኋላ ሰራዊቱ ከውጭ ወራሪ ሃይል ማዳን እንደማይችል በተጨባጭ መገንዘብ ይኖርበሃል። ሰራዊቱ ከውጭ ወራሪ ግንባር ገጥሞ ትግራይን የሚወር ከሃዲ ሰራዊት ሆኗል።

እኛ ለዓላማችን እንሰዋለን! ይህ ከሃዲ ሰራዊት ግን ዓላማ ቢስ ሆኗል። ህዝብን መጠበቅንና ማገልገልን ትቶ የአምባገነን መሪ አገልጋይና ዘበኛ ሆኗል። የትግራይ ህዝብ ይህ ሰራዊት ፀረ- ህዝብ መሆኑን ስላወቀም እየሸሸ ነው ያለው። ይህ ሰራዊት ወደ ደርግ ሰራዊትነት በመቀየሩ ያሳዝናል! ያሳፍራል! የነበረው አኩሪ ታሪክ አክትሟል! ካሁን በኋላ ሁሉም የሰራዊት አመራርና አባሉ ተጠያቂ ነው። የሀገር ማፈሪያዎች ሆናችኋል።

የመከላከያ ሰራዊቱ አገርን ማዳን ህዝብን መጠበቅ ሲገባው ከውጭ ወራሪ ሃይል ተዳብሎ የትግራይን ህዝብ መውጋት የክህደት ክህደት ነው! ለመሆኑ በሰራዊቱ ውስጥ የነበረው የትግራይ ተወላጆች በመሆናቸው ብቻ ከሰራዊቱ ተለቅመው ሲወጡ ምን አላችሁ? አንድ ብሄር አግልሎ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መሆን ይችላል ወይ? ለኛ ይህ ሰራዊት ባዕድና ወራሪ ሃይል ነው! ስለሆነም ከሻዕቢያ ወራሪ ሃይል ደርበን እንፋለመዋለን! መሬት አስመላሽ ነኝ ባዩ ደግሞ መሬት ሳይሆን የሚያገኘው የመቀበሪያው አፈር ብቻ ነው!

ሌላ በዛሬው ቀን አገር በተደፈረችበት ጊዜ በትግራይ ደቡባዊ ዞን በራያ በኩል የመከላከያ ሰራዊቱና መሬት አስመላሹ ሰራዊት በጋራ ጦርነት ከፍተዋል። በበርካታ የድንብር አከባቢ የሻዕቢያ ሰራዊት ሲወጋን በራያ በኩል ደግሞ የመከላከያ ሰራዊት እየወጋን ይገኛል። በማኸል ያሉ ቦታዎች ደግሞ የኤርትራና የኢትዮጵያ ሰራዊት ሁለቱም በጣምራ እየወጉን በታሪክ እጅግ አሳፋሪ ክህደት እየፈፀሙ ይገኛሉ። ይህም ይህ አገር አገር መሆኑን እንዳበቃለት ያሳያል። ካሁን በኋላ” ከውጭ ወራሪ ሃይል ሆኖ አገርን አስጠብቃለሁ!” የሚለው ነገር ዘበት ነው! ምክንያቱም በዚህ አሳፋሪ ተግባር ውጤትም አገርን የመበተን እንጂ አንድነት የሚባል ነገር የለም።

ወራሪው የኢትዮጵያ አየር ሃይልም ድብደባውን እየቀጠለ ይገኛል። ከትግራይ ምዕራባዊ ዞን እስከ ደቡባዊ ዞን ከተሞችና ገጠር በቦንብ እየደበደቡ ይገኛሉ። በዚህ ድብደባ ገፈት ቀማሽ የሆነው አንዱ ወልቃይት የስኳር ፋብሪካ ነው። ፋብሪካው እንደ ጠላት ሃብት በቦንብ ተደብድቧል። ባለፈውም የተከዜ ኤሌክሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ መደብደቡ ይታወቃል።

ስለዚህ ይህ ወራሪ ሃይል በአያሌ የኢትዮጵያ ህዝብ አንጡራ ሃብት የተገነባውን በቦንብ ደብድቦታል። ይህ ድብደባም ትግራይን ብቻ ሳይሆን አገሪቷን በሙሉ ወደ ኋላ የሚመልስ ከመሆኑም በላይ እንደ ሃገርና ክልል ከድህነት ለመውጣት የምናደርገውን ትግል ወደ ኋላ የሚመልስ ነው። ይህንን አሳፋሪ መንግስት ሁላችንም በጋራ ካልታገልነው በቀር አገሪቷ በሙሉ የሚያወድም ሃይል ነው፤ በመሆኑም ይህንን ተገንዝበን መታገል ይገባናል።

የተከዜ ግድብ ከተደበደበ በኋላ በስንት ትግልና ጥረት አገልግሎት መስጠት ችሏል። ይህ አገልግሎት ለመላው ሃገር ህዝብ እንጂ ለትግራይ ብቻ የሚሰጥ አልነበረም ግን ተደብድቧል። ካሁን በኋላ ይህ ግድብ ዳግም የሚደበደብ ከሆነ እኛም ተመጣጣኝ አፀፋዊ እርምጃ ለመውሰድ እንገደዳለን።

ሌላው በትግራይ ምዕራባዊ ዞን የአማራ ብሄር በመሆናቸው አሰቃቂ ግፍ፣ አሳዛኝና አስደንጋጭ በሆነ መልኩ የተገደሉ መሆናቸውን ሰምተናል። ይህ አሳዛኝና አሳፋሪ ተግባር ነው! ይህ ግፍ አሁንም “በህወሓት ልዩ ሃይል ተፈፀመ” የሚል ክስ ቀርቧል። ይህ ሴራ ልክ በወለጋ እንዳጋጠመውና “በወያኔና በኦንግ ሸኔ” እንደተላከከው ሁሉ አሁንም “በትግራይ ውስጥ በህወሓት እንደዚህ ዓይነት ድርጊት ተፈፀመ” ተብሎ የቀረበው ነጭ ውሸት ነው። ምክንያቱም በትግራይ ህዝብና መሬት እንደዚህ ዓይነት ተግባር ሊፈፀም ቀርቶ ሊታሰብ አይችልም። እንደዚህ ዓይነት እኩይ ድርጊት በከፍተኛ ደረጃ የምናወግዘውና፣ አምርረን የምንጠላውና የምንቃወመው ነው።

ለመሆኑ ከ2008 ዓ/ም ጀምሮ ስንትና ስንት የትግራይ ተወላጆች በአማራ ክልል ውስጥ ሲገደል፣ ሲገረፍ፣ ሲፈናቀል ንብረቱ ሲቃጠል፣ ሲዘረፍና ሲባረር፣ በኛ በኩል በወቅቱ “ግድ የለም ይህ እኩይ ድርጊት የጥቂት አመራሮች ችግርና ያልገባቸው ልጆች ድርጊት ነው” ተብሎ በትዕግስት ታልፏል። በአንፃሩም በትግራይ በኩል አንድም የአማራ ተወላጅ ጉዳት እንዳይደርስበት ተደርጓል። ይህ ድርጊት እንደ ህብረተሰብ፣ መንግስትና ፓርቲ ተቀባይነት የለውምና ነው። ምክንያቱም ሰው በትውልዱ ሳይሆን ሰው በመሆኑ ብቻ የሚከበርበት ክልል ነው። ይህ ተግባር የቆየ፣ አሁንም ያለና ለወዲፊቱም የሚቀጥል ነው።

ስለዚህ ይህ አሳዛኝ ድርጊት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የፈፀመው ወራሪ መንግስት መሆን አለበት። ይህ የተፈለገው በትግራይ ህዝብ ላይ ሌላው ህዝብ ለማነሳሳት ነው። በትግራይ ህዝብ ላይ እየተወሰደ ያለው ግድያ፣ እስርና እንግልት ለማስቀጠል የታሰበ መሆኑ ግልፅ ነው። ህዝብ ከህዝብ ጋር ለማጨራረስ ነው። እኛ በህዝብ ዘንድ የሚደርሰውን ግፍ እንታገላለን እንጂ በኛ ዘንድ ፈፅሞ አይደረግም!

ስለሆነም ይህ አሳዛኝና አሰቃቂ ድርጊት በነፃና ገለልተኛ ወገን ይጣራ እንላለን። ወንጀለኞችም ተለይተው ለፍርድ ይቅረቡ። እኛም በዚህ ረገድ ለሚደረገው ማጣራት ሂደት ተባባሪ መሆናችንን መግለፅ እንፈልጋለን።

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አሁን በትግራይ ላይ በሁሉም ግንባር እየተካሄደ ያለው ወረራ ተጠናክሮ እየቀጠለ ነው ያለው። የኢትዮጵያና የኤርትራ ሰራዊት ባለ በሌለ ሃይሉ ገብቶ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰብን ይገኛል። የትግራይ ህዝብም የሰራዊቱ ባህሪ ተገንዝቦ በመቃወም እየተፈናቀለና ይገኛል። ልክ የውጭ ጠላት ሲመጣ እንደሚያደርገው እየገጠመም ሰላም ወደአለበት አከባቢ እየተፈናቀለም ይገኛል። ህዝቡ በአውሮፕላንም እየተደበደበ ነው ያለው። ስለሆነም ይህ አሳፋሪ የክህደት ታሪክ በከፋ ደረጃ ከመቀጠሉ በፊት እንዲቆም የራሳችሁን ትግል እንድታካሂዱ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

ትግራይን የወረረ ሃይል አሁንም ቢሆን የፈለገውን መስዋእትነት ከፍለን መብታችንንና ህልውናችንን ደግመን እናረጋግጣለን!

ድሉ ለመብቱ፣ለታሪኩና ለህልውናው በፅናት የሚታገለው የትግራይ ህዝብ ነው!

አመሰግናለሁ!

ድል ለትግራይ ህዝብ!

የድርጅታችን ህወሓት ሊቀ መንበርና የትግራይ ፕረዚዳንት ጓድ ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ፋሽስት ወራሪዎች የትግራይ ህዝብ ማንነቱን ለማጥፋት የከፈቱት ጦርነትና በትግራይ በኩል እየተወሰደ ያለው የአፀፋ ምላሽ በማስመልከት የሰጠው መግለጫ

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com