ዜና

ከትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ መግለጫ

Views: 211

በግፍ በተገደሉ ንፁሃን ዜጎች ደም፣ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘች መሯሯጥ፣ በግፍ ላይ ግፍ መፈፀም ብቻ ሳይሆን፣ እንደተለመደው እውነታውን ለማድበስበስ የሚደረግ ኣደገኛ ፀረ-ህዝብ ሴራ ነው፡፡

ከሁሉ በማስቀደም፣ የትግራይ ህዝብና የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት፣ ጥቅምት 22/2013 ዓ/ም በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ቃንቃ ጋዋ ቀበሌ፣ በንፁሃን ኢትዮጵያውያን ወገኖች የደረሰው የግፍ ጭፍጨፋ የተሰማቸው ጥልቅ ሃዘን ይገልፃሉ፡፡ በየትኛውም ስፍራም ሆነ ጊዜ፣ ብሄር ተኮር ጥቃት የትግራይ ህዝብና ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በጥብቅ ያወግዛሉ፡፡

ስለሆነም በንፁሃን ወገኖቻችኝ ላይ በተፈፀመው ግፍ ልባቸው ለተሰበረው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም የግፍ ሰለባ ለሆኑ ቤተሰቦች የትግራይ ህዝብና ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት መፅናናት ይመኛሉ፡፡

የትግራይ ህዝብና ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል፣ በኣሃዳዊ ኣምባገነኑን ቡዱንና ጋሽ ኣሻግሬዎቹ የደረሰባቸው ስፍር ቁጥር የሌለው ብሄር ተኮር ጥቃት በማንኛውም የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰብና ህዝብ ላይ ሊፈፀም ቀርቶ ሊታሰብ እንደማይገባው፣ ዕድሜ ልካቸው ሲታገሉለት የኖሩት እውነታ ነው።

ነገር ግን ትናንት በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ በንፁሃን ወገኖቻችን የተፈፀመው እጅግ ዘግናኝና ኣሳዛኝ ጭፍጨፋ፣ በማን እንደተፈፀመ በትክክል ሳይጣራ፣ በሕገ ወጡ ኣሃዳዊ ኣምባገነናዊ ቡዱን እውነታውን ለማድበስበስ ሲባል እንደተለመደው ጉዳዩን ወደ ሦስተኛ ወገን ማለትም የፈረደባቸው ህወሓትና የትግራይ ህዝብ ወንጅሏል፡፡

ይኸው ህገ ወጡ ኣሃዳዊ ኣምባገነናዊ ቡዱን መሪዎች የጥቃቱ ድርጊት የፈፀመ ኣካል ኦነግ ሸኔ እንደሆነ፣ ህወሓትም ከጀርባው በመሆን እየደገፈው ነው በማለት እንዳሻቸው በሚያሽከራክራቸው ሚዲያዎች፣ ሓሰተኛ የያዙኝ ልቀቁኝ አዛኝ ቅቤ ኣንጓች ቧልት ያለ ምንም ይሉኝታ በማን ኣለብኝነት እየተቀባበሉ፣ በማስተጋባት ላይ ናቸው፡፡ ሆኖም ይህ የኣዞ እምባ ጭሆት፣ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ ላእላዊነት ኣስደፍሮ ሀገር የካደ ኣሃዳዊ ኣምባገነናዊ ቡዱን ከሻዕቢያ መሪ በመመሳጠር የትግራይ ህዝብና መንግስት በሐይል ለማንበርከክ እያደረጉት ያሉት ዝግጅት ለማቀላጠፍ እንደ እሳት ማቀጣጠያ ቤንዚን ሊጠቀሙበት የከጀሉት ስለመሆናቸው የሚያሳይ ኣደገኛ ፀረ-ህዝብ ሴራ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

በመጨረሻም፣ በግፍ ለተገደሉት ንፁሃን ደም የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት መሯሯጥ፣ በግፍ ላይ ግፍ መፈፀም ብቻ ሳይሆን፣ እንደተለመደው እውነታውን ለማድበስበስ የሚደረገው ኣደገኛ ፀረ-ህዝብ ሴራ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

ስለዚህ በዋናነት ትናንት በምዕራብ ወለጋ ዞን እንዲሁም ከዚህ በፊት በየቦታው በተለያዩ ኣከባቢዎች በንፁሃን ዜጎች ላይ የተፈፀመውና ብሄር ተኮር የጅምላና የግፍ ጭፍጨፋዎች በገለልተኛ ወገን ተጣርተው እውነታው የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች እንዲሁም የዓለም ኣቀፍ ማህበረሰብ እንዲያውቀው እንዲደረግ፣ የትግራይ ህዝብና ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጥሪያቸውን ያቀርባሉ፡፡

ስለዚህ ማንኛውም የሰብአዊ መብት ተማጓች ተቋም፣ እንዲሁም የአለም አቀፍ ማህበረሰብ፣ ጊዜው ሳያልፍ እና ነገሮች እንዳይደበቁ፣ በአስቸካይ የማጣራት ሥራቸውን በማከናወን ሀላፊነታቸው ሊወጡ ይገባል፡፡
የትግራይ ክልል ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ
ጥቅምት 23/2013 ዓ/ም
መቐለ

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com