ዜና

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና ትምህርት በኢትዮጵያ

Views: 794

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና ትምህርት በኢትዮጵያ

መስፍን ታደሰ

ተፃፈ ነሐሴ ፲፱፻፺፮ዓም (August, 2004)

ከመደበኛ ሙያው ውጪ፤ የኢትዮጵያን ታሪክ እና ስለ ኢትዮጵያ የሚወሱትን ሁሉ አጥብቆ የሚከታተለው የእጽዋት ተመራማሪው መስፍን ታደሰ (ፒኤችዲ)፣ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና ትምህርት በኢትዮጵያ›› ሲል ያወጋናል፡-

በኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹ ተማሪዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ያስተማረቻቸው እንደነበሩ ከታሪክ እንረዳለን። ትምህርቱም የቤተክህነትን ታሪክ እና ቋንቋ እንደ ነበር ጸሐፍት ይገልጻሉ።

ተምሮ ማስተማር” የሚለውን ጽንሰ ሃሳብን ያፈለቀችው ይህችው ጥንታዊት ቤተክርስቲያን ነበረች። ዘመናዊው ትምህርት በዳግማዊ አፄ ሚኒልክ በ፲፱፻፩ ዓ.ም (October 1908 GC) እስከሚጀመር ድረስ በኢትዮጵያ የነበረው ትምህርት ይኸው በቤተክህነት ሰዎች በግዕዝ ቋንቋ የሚሰጠው ነበር።

በ፲፱፻፷፮ ዓ.ም የተደረገ ጥናት ከአስራ አምስት ሺህ (15,000) በላይ ቤተክርስቲያናት በሃገሪቱ እንደነበሩና የቀሳውስቱ ቁጥር ወደ ሁለት መቶ ሺህ (200,000) እንደነበር ገልጿል።

ከእነዚህ ውስጥ ምን ያህሉ በአስተማሪነት እንደተሰማሩ ባይታወቅም፤ ቁጥሩ ቀላል እንዳልነበርና ካስተማሯቸው መሐል ብዙዎቹ ለዘመናዊው ትምህርት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ እንደሆኑ ብዙ ተጽፏል።

በዚህ ሂደት ውስጥ ያለፉ ተማሪዎች ስንት እንደሆኑ ወይም እንደነበሩ ባይታወቅም ቅሉ፣ በዚህ በ፲፱፻፷፮ ዓ.ም በተደረገ ጥናት፤ የተማሪዎች ብዛት ወደ ሶስት መቶ ሺህ (300,000) የሚደርስ ነው ሲል ተዘግቧል፡፡ ስሌቱም በአንድ ቤተክርስቲያን ስር በአማካኝ ሃያ (20) ተማሪዎች ቢማሩ የሚል ነበር።

የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ትምህርት ቤት መስራቾች የኦርቶዶክስ ሃይማኖት አማኝና ተከታይ ወጣት ግብጻውያን እንደ ነበሩ ከታሪክ ፀሐፊው እና ከተመራማሪው ከፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ጽሑፎች እንረዳለን።

ለተማሪዎች ይሰጡ የነበሩ ትምህርቶች ፈረንሳይኛእንግሊዝኛጣልያንኛአማርኛሂሳብ እና ሳይንስ ነበሩ፤ የሰውነት እንቅስቃሴና ስፖርትም አብረው ይካሄዱ ነበር።

እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ልናነሳ እንችላለን። ለምን ግዕዝ፣ እንደ ቋንቋ፣ በትምህርቱ ውስጥ አልተካተተም!? አስተማሪዎቹ ወጣት ግብጻውያን ስለነበሩ? የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ስላልተካፈለች? ወይስ በሌላ ምክንያት? መልስ የለኝም፡፡

ነገር ግን፣ ግዕዝን እኔ በተማርኩበት በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ባለማግኘቴ ቅር ይለኝ ነበር። ተስፋ አለኝ የመቀሌው ዩኒቨርሲቲ እንደሚያስፋፋው እና ለታሪካችን ቅርብ እንድንሆን እንደሚረዳ።

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com