ዜና

‹‹ኮሮና ቫይረስ በአንዳንድ ቁሶች ላይ እስከ 28 ቀናት ሊቆይ ይችላል››

Views: 249

ኮቪድ-19 በሽታን የሚያስከትለው ኮሮና ቫይረስ የገንዘብ ኖቶች ላይ፣ የስልክ ስክሪኖች ላይ እና በማይዝጉ ብረቶች ላይ ለ28 ቀናት ሳይሞት ቆይቶ በሽታ ሊያስተላለፍ እንደሚችል ተመራማሪዎች ይፋ አደረጉ።

የአውስትራሊያ ብሔራዊ ሳይንስ ኤጀንሲ ይፋ ያደረገው ጥናት ሳርስ-ኮቭ-2 የሚል ሳይሳዊ መጠሪያ ያለው ኮሮናቫይረስ ከተገመተው በላይ ለረዥም ጊዜ በቁሶች ላይ እንደሚኖር ያረጋገጠ ነው።

ኮሮና ቫይረስ በብዛት የሚተላለፈው ሰዎች ሲያስሉ፣ ሲያስነጥሱ ወይም ሲነጋገሩ እንደሆነ ይታወቃል። ይሁን እንጂ ይህ አዲሱ የተመራማሪዎች ግኝት ቫይረሱ ከቁሶች ወደ ሰዎች የሚተላለፍበት መጠንም ከተገመተው በላይ ሊሆን ይችላል ተብሏል።

ከዚህ ቀደም ተማራማሪዎች አልትራ ቫዮሌት (ዩቪ) ብርሃን ቫይረሱን ሊገድለው እንደሚችልም ማሳየታቸው ይታወሳል። ከዚህ ቀደም የተካሄዱ ምርምሮች ኮሮናቫይረስ በገንዘብ ኖቶች እና ጠርሙሶች ላይ ከሁለት እስከ ሶስት ቀናት እንዲሁም በፕላስቲክ እና በማይዝጉ ብረቶች ላይ ደግሞ እስከ ስድስት ቀናት ሊቆይ እንደሚችል ነበር።

አውስትራሊያውያኑ ባካሄዱት ምርምር ግን በጭለማ እና 20 ዲግሪ ሴሊሺየስ ሙቀት ባለው ክፍል ውስጥ ቫይረሱ በጠርሙሶች እና በስልክ ስክሪኖች ላይ እስከ 28 ቀናት ሊኖር እንደሚችል አመልክተዋል።

በጥናቱ እንደተመለከተው፤ ኮሮናቫይረስ ሞቃታማ በሆነ ክፍል ውስጥ ለረዥም ጊዜ እንደማይቆይ አረጋግጧል። 40 ዲግሪ ሴሊሺየስ ሙቀት መጠን ባለበት ክፍል ውስጥ የተቀመጠው ቫይረስ ከ24 ሰዓታት በኋላ ሰዎችን ሊበክል አይችልም።

በተነጻጻሪ ጉንፋን የሚያስከትሉ ቫይረሶች በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ከተቀመጡ እስከ 17 ቀናት ድረስ ሊቆዩ ይችላሉ። ቫይረሱ በጨርቅ ላይ ከ14 ቀናት በላይ እንደማይኖርም በጥናት ውጤቱ ላይ ተጠቁሟል።

የተመራማሪዎቹ ጥናት ሰዎች እጆቻቸውን እና የስልክ ስክሪኖቻቸውን በተደጋጋሚ ማጽዳት እንዳለባቸው የሚያስታውስ ነው ተብሏል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የአውስትራሊያ ብሔራዊ ሳይንስ ኤጀንሲ ይፋ ያደረገውን ጥናት አጥብቀው የተቃወሙ ባለሙያዎች አልጠፉም።

በካርዲፍ ዩኒቨርሲቲ ጉንፋን የሚያስከትሉ ቫይረሶች ላይ ምርምር ያደርጉ የነበሩት ፕሮፌሰር ሮን ኢካልስ፤ ቫይረሱ ለ28 ቀናት በቁሶች ላይ ይኖራል ብሎ ማወጁ በሰዎች ዘንድ አላስፈላጊ መደናገጠን የሚፈጥር ነው ይላሉ።

ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት ከሆነ ሰዎች ሲያስነጥሱ ወይም ሲስሉ ቫይረሱ ከሰውነታቸው የሚወጣው እርጥበት ውስጥ ሆኖ ነው። “ቫይረሱም ከአንዱ ወደ ሌላ የሚተላለፈው ከሰዎች ሲወጣ የያዘውን እርምጥበት እንደ መጓጓዣ በመጠቀም ነው” ይላሉ።

የማይክሮባይሎጂ ፕሮፌሰሩ ኢማኑኤል ጎልድማን ደግሞ ላንሴት ላይ ባሳተሙት ጽሑፍ፤ ቫይረሱ በቁሶች አማካኝነት ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ እድሉ በጣም አስተኛ ነው ብለዋል።

ፕሮፌሰሩ የአውስትራሊያ ብሔራዊ ሳይንስ ኤጀንሲ ያካሄደው ጥናት በጭለማ እና የሙቀጥ መጠኑ በማይቀያየር ክፍል ውስጥ መሆኑን በማስታወስ፤ “ጥናቱ እኛ የምንሮርበትን ዓለም ከግምት ውስጥ አስገብቶ የተካሄደ ጥናት አይደለም” ይላሉ።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com