ዜና

መምህር መስፍንን-ሥሰናበት!

Views: 669

(የመጨረሻው- መጨረሻ)

ጌታቸው ወርቁ

‹‹ሞት ማለት›› ይላል መምህር በግጥም-

ሞት ማለት፡-

አለመናገር ነው፤ ጭው ያለ ዝምታ፤

የመቃብር ሰላም፣ የሬሳ ጸጥታ፣

ደሀ በሰሌኑ፣ ሣጥን ገብቶ ጌታ፣

የውሸት ልዩነት ተጋድሞ በተርታ፣

አይመሽ ወይ አይነጋ፤ ጠዋት የለ ማታ፤

ሐዘን የለ ለቅሶ፤ ደስታ፣ ፈገግታ፣

ዘፈኑና ለቅሶው የምስጥ ሹክሹክታ፤

ሞት ማለት፡-

አይረገዝበት፤ አይወለድበት፤

የመቃብር ዓለም፣ ጭንጋፍ የጭንጋፍ ቤት!

የሰው ልጅ እንደእበት ትል የሚሆንበት!

ክርክር የለበት፤ ውድድር የለበት፤

ውሸትና እውነት በማይበርድ ፍትወት

የተሳሰሩበት፤

የድብቅብቅ ዓለም፣ ምሥጢር የበዛበት!

ሁሉም በየጉድጓድ የተሸሸገበት፡፡

(መስፍን ወልደ ማርያም፣ ዛሬም እንጉርጉሮ፣ አዲስ አበባ፣ 2006 ዓ.ም)

በቀለም-ቀንድነት ከማውቃቸው ኢትዮጵያዊ የአደባባይ ምሁራን ውስጥ፤ ዕይታውን፣ አመለካከቱን እና ትንተናውን ከራሱ ግለሰባዊ የዝንባሌ-ጫና አላቅቆ፣ ከቡድናዊነት ተነጥሎ፣ ከጎሰኝነት ጸድቶ፣ የእውነት ወእውቀት ፍለጋውን በምክንያት እና ውጤት (በአመክንዩ) አሠናስሎ፣ በሞራል ልቀት ከፍ ብሎ ሃሳቡን በነጻነት ከድምዳሜ በማድረስ በአደባባይ የሚገልጽ፣ የሚከራከር እና የሚጽፍ ጉምቱ ምሁር እንደ መምህር (ፕሮፌሰር) መስፍን ወልደ ማርያም ያክል አልተመለከትኩም፡፡

መምህር የትምህርትን ማኅበረሰባዊ ዓላማን ሲያስረግጥ እንዲህ ይላል፡-

‹‹ዱሮ በልጅነቴ የኢጣሊያ ወረራ ማብቂያው ላይ የሰው ሁሉ ወሬ ነጻነት እንደ ነበር አስታውሳለሁ፡፡ ዘፈኑ ስለነጻነትና ስለአርበኞች፣ ስለድል አድራጊው ንጉሰ ነገሥት ነበር፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚወራው የመረረ ቁጭት ነበር፤ በኢጣልያና በእኛ መሐከል የነበረውና አሁንም ያለው የእውቀት ልዩነት ለጥቃትና ለውርደት እንደዳረገን በደንብ መረዳታችን ክፉኛ ይቆረቁረን ነበር፤ ስለዚህም፣ ድንቁርናችንን አራግፈን በእውቀት እንድንታጠቅ ዓየሩ በሙሉ የሚያበረታታ ነበረ፤ ትምህርት፣ ትምህርት፣ ትምህርት፣ … እውቀት፣ እውቀት፣ እውቀት!›› (መስፍን ወልደ ማርያም፣ አዳፍኔ- ፍርሃትና መክሸፍ፣ ገጽ 19)

ለመምህር መስፍን ወልደ ማርያም የልቦና ውቅር (ሥሪት) አስተዋጽኦ ካደረጉ የሕይወት ዓላባዊያን አንድ አንኳር እዚህ ከላይ ያሰፈርኩት የመጽሐፉ አንድ አንቀጽ ውስጥ ይገኛል ብዬ አስባለሁ፡፡ ደራሲ አንድ ጊዜ ከጻፈ ሚስጥር የለውምና ድርሰቱን፣ የህይወት ታሪኩን እና የኖረበትን ጊዜ አሰናስሎ ውስጣዊ እሱነቱ ላይ ይደረሳል ባይ ነኝ፡፡ ይህን ሃሳብ በየመጽሐፍቱ በልዩ-ልዩ ገለፃ ሲደጋገም እንመለከታለን፡፡

መምህር፣ ከእውቀት ጋር በመጣበቅ፣ ነገሮችን/ኹነቶችን በነጻነትና በድፍረት ከመመርመር በቀር፤ እኔ ከዚህ ጎሳ ነኝ፣ አንተ ከዚያ ጎሳ ነህ ሲል ሰምቼው አላውቅም፤ ጽፎም አላነበብኩ፡፡ ወደዚህ መስመር ተጎትተው የገቡትን ወይም ሊገቡ የዳዳቸውን አንጋፋ ምሁር ግን በአደባባይ ክርክር ‹‹ተው፣ አንተ ከዚህም፣ ከዚያም ወገን አይደለህም፤ ይልቅኑ ከባህር ማዶ ነህ›› ብሎ ገና ‹‹ዝናረ-ብዙ›› መሆኑን ማመላከቱን አንብቤያለሁ፡፡

መምህር በመጀመሪያ ሰው ነው፤ ከዚያ ጥቁር አፍሪቃዊ ሰው ነው፤ ቀጥሎ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነው፡፡ ሀገሩን ከነሁለንተናዋ እና ጥቁር አፈሩ አብዝቶ ይወዳል፡፡ ምክንያቱም አፈሩ ውስጥ ለሀገራቸው፣ ለወገናቸው ሲሉ መስዋዕት የሆኑ አያት/ቅድም አያት/ ቅማያት …እናት/አባቶቻችን አርፈዋል ይላል፡፡ በዛሬው ሕይወቱ የትላንት የእነርሱን/ዐርበኞች መስዋዕትነት ይዘክራል፤ ሕይወታቸውን በነፃነት ይፈትሻል፤ በእውቀት እና በማስረጃ ላይ ተመርኩዙ ይበይናል፡፡

ዋው እዚህ ላይ ብዕሩ ኃያል ነው!

መምህር መስፍን፣ ሕይወቱን ሙሉ ስለነጻነት፣ ስለሰው ልጅ ክብር፣ ስለሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ ስለፍትሕ መስፈን ዋትቷል፤ ለፍቷል፤ ደክሟል፡፡

(በቀ.ኃ.ሥ ዘመነ መንግሥት፣ በደርግ ዘመነ መንግሥት፣ በህወሓት (ወያኔ) ዘመነ መንግሥት (ይህ፣ የኃይለማርያም ደሳለኝን-ም ጊዜ ይጨምራል) እና በድሕረ- ህወሓት (የጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ዘመነ መንግሥት) ወቅት ሁሉ፣ አንድም ጊዜ ሳይዛነፍ ቀጥ ብሎ ነፃነትን፣ ትምህርትን፣ እውቀትን፣ ዴሞክራሲን፣ ፍትሓዊነትን እንደሻተ እና እንደፈለገ ኖሮ፤ ጥሩ ሲሰራ አበረታትቶ፤ ስህተት ሲሰራ ነቅፎ ነው ያለፈው፡፡

በዚህ የእውቀትንና እውነትን ፍለጋ የሕይወት መንገዱ ውስጥ ጋሬጣ እየሆኑ የሚያስቸግሩትን ገዢዎችን፣ ባለሥልጣናትን፣ ጨቋኞችን፣ እና ሰብዓዊ መብትን የሚጥሱ ተቋማትን፣ ቡድኖችን እና ግለሰቦችን  በሀገሩ ላይ ተቀምጦ በብዕሩ በአደባባይ እየተፋለመ፣ እየሄሰ እና እየተቸ በማረቅ ‹‹አካፋን አካፋ›› ሲል በይኗል፡፡

በዚህ ቀጥተኛ የሕይወት መርሁ፣ ጥናት ባላደርግበትም ቅሉ፣ ከወዳጆቹ ይልቅ አክባሪዎቹ እና ነቃፊዎቹ ተደምረው የሚልቁ ይመስለኛል፡፡

መምህር መስፍን፣ በቀን-ተቀን የእውቀትና እውነት ፍለጋው ሳቢያ፣ በገዢዎች ከግዞት እስከ እሥራት ዋጋ እየከፈለ (አንዳንዴም ‹‹የደህንነት ሰዎች›› እርግጫን ቀምሶ፣ ታሞ- ታክሞ- አገግሞ ኖሮ ያለፈ፣ አንጋፋ ብሔራዊ ጀግና- አርአያችን ነው፡፡

መምህር መስፍን ወልደ ማርያም፣ በመሐል ፒያሳ በሚኖርበት ከሔንርኮ ኬክ ቤት ወረድ ብሎ ባለው ‹‹አፓርታማ›› ቤት (ስቱዲዮ/ቤተ-መጽሐፍት/ቢሮ) ውስጥ በስልክ ቀጠሮ አስይዞ- ጎራ ከሚል ማንኛውም እንግዳ ጋር ጤናው ካልታወከ እና የራሱ አጣዳፊ መርሃ-ግብር ካልያዘው በቀር ለመነጋገር፣ ለመወያየትና ለመከራከር ብዙ ጊዜ ፈቃደኛ መሆኑን ተመልክቻለሁ፡፡

በንግግር፣ በውይይት እና በክርክር ጊዜ ከይሉኝታ፣ ከከንቱ ወዳጃዊ ግቡቡነት፣ ከጭፍን ጥላቻና ድምዳሜ (ፕሪጂዱዩስ) ውጪ ነው፡፡ ሳይዘጋጅ (መጽሐፍቱን ሳያነብ) እርሱ ጋር ቀርቦ በግልጽ በጽሑፍ ባሰፈረው ሃሳብ ላይ ሳያነብ ጥያቄ የሚያቀርብ በተለይ ጋዜጠኛ ያናድደዋል፤ እናም፣ ግለሰቡን አስደንግጦ ይመልሰዋል፡፡

ሆኖም፣ ከሁለት ዓመት በፊት አሜሪካን አገር ሕክምና አድርጎ ከመጣ በኋላ ግን ይህን ባህርይውን አለሳልሶ እንደያዘው ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ነገሮችን በአንክሮ ስለሚከታተል ሂስ-ጣል ሳያደርግ እና ሳይተች አያልፍም፡፡ ያኔ ሕክምናውን አሜሪካን አገር አድርጎ ሲመጣ፣ ከጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እና ፍቃዱ ማኅተመወርቅ ጋር ልንቀበለው ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሄደን ነበር፡፡

ስንመለስ ከብዙ ወዳጆቹ ጋር (ዶ/ር ያቆብ ኃይለ ማርያም፣ አርቲስት ደበበ እሸቱ፣ አንዷለም አራጌ፣ ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ፣ ይድነቃቸው ከበደ፣ ኤልሳ … እና ሌሎች ወዳጆቹ)ም ከተቀበሉት በኋላ፣ ፒያሳ ካለው አፓርታማ ቤቱ አረፍ አልን፡፡

የአተነፋፈሱ ሂደት በኦክስጅን መሳቢያ መሳሪያ ድጋፍ እየተረዳ በዊልቸር ተቀምጦ በመምጣቱ፣ ስለጤንነቱ እና ስለሕክምናው ሁኔታ ጠየቅኩት፡፡

‹‹ሕክምናቸው እጅግ ዘመናዊና በእያንዳንዱ መስክ ሁሉ ጠቢባን (ስፔሻሊስት) ባለሙያ አላቸው፡፡ እንደ ዋዛ የሚመለከቱት ነገር የላቸውም›› አለ መምህር፡፡ ቀጠል አድርጎም ትንፋሽ ከወሰደ በኋላ፣ ‹‹ሁሉ ነገርህን በአንክሮና ወደ-ፊት ሊያስከትል ከሚችለው የጤና እክል ሁሉ ሊጠብቁህ በሙያቸው ይታትራሉ›› ብሎ ፈገግ አለ፡፡

‹‹እኔማ በስተመጨረሻ በቃ ተሸሎኛል፤ ድኛለው፤ … የነበረብኝን በሽታ ሁሉ አክማችሁ ጨርሳችኋል፤ አሁን ሰውነቴ ላይ የግድ በሽታ ካላገኘን ብላችሁ እየደከማችሁ ነው፤ ጤንነት ነው የሚሰማኝ፤ በቃኝ ብዬ ወጣሁ›› ብሎ አስቆናል፡፡

መምህር፣ ሁልጊዜ እውቀትን፣ እውነትን በመፈለግ በመመርመር ውስጥ ነው ራሱን የሚያሰማራው፡፡

አንድ ጊዜ ደግሞ ከሙያ ጓዶቼ (ተመስገን ደሳለኝ፣ አለማየሁ ገላጋይ፣ በእውቀቱ ስዩም) ጋር ሆነን ቤቱ ልንጠይቀው ሄደን (ከኮቪድ 19 ተኅዋስ ወረርሽኝ በፊት-በፊት ነው!) ስንወያይ፤ በመሐል፡-

‹‹ሠራተኛዬ የለችም፤ እኔም ምንም አላዘጋጀሁም፤ ሆኖም፣ ፈቃዳችሁ ከሆነ እዛ ጋ ውስኪ አለ፤ ልትጋበዙና ራሳችሁን ልታስተናግዱ ትችላላችሁ፡፡›› አለንና

‹‹ቢራ እንኳ እኔ ቤት አይገባም›› ብሎን ሳቅ አለ፡፡

ከዛም ‹‹የመ-ሕጎች›› ሲል የሰየመውን የግሉን የአልኮል መጠጥ-ክልከላ ሕጎቹን ነገረን፡፡

ሀ. አልኮል መጠጥ ለመጠጣት ብዬ- አልጠጣም፤

ለ. ርቦኝ ወይም በአግባቡ ሳልመገብ- አልጠጣም፤

ሐ. ተናድጄ፣ ንዴቴን በአልኮል መጠጥ ለማብረድ ስል- አልጠጣም፤

መ. ተደሰትኩ ብዬም ለጭፈራ- አልኮል መጠጥ አልጠጣም፤

ነገር ግን፣ ልክ እንደ እናንተ ወዳጆቼ መጥተው ወይም ወደ ወዳጆቼ ሄጄ ከጠቀስኳቸው ምክንያቶች ውጪ በሆነ መንገድ፣ ለመጨዋወት፣ ለመወያየት ስል በአጋጣሚ እቀማምሳለሁ እንጂ አለን፡፡

ከመምህር ሌላው የሚደንቀኝ፣ በአያት/ቅድመ-አያት የእድሜ እርከን ላይ ሳለ እንኳ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ በየጊዜው የሚፈጥሩትን ልውጥውጥ አዎንታዊ የተግባቦት ትሩፋቶችን፣ እግር-በእግር እየተከተለ፣ ራሱን በማሳወቅ በአግባቡ መጠቀሙ ሲታከልበት ደግሞ፣ ሰውዬው (መምህር) ሁልጊዜ ተምሮ-አስተማሪ ጊዜውን የዋጀ ሰው መሆኑ ጎልቶ ይታያል፡፡

መምህር የሚጠቀምበት ኮምፒውተር ላይ የሚፈልገውን ‹‹ሶፍትዌር›› በዲጂታል ተግባቦት ተጠቅሞ በማውረድ ይጭናል፣ የራሱን ጽሑፍ ራሱ ኮምፒውተር ላይ ይጽፋል፣ ‹‹ዲዛይንና ሌይ አውት›› ይሰራል፤ የመጽሐፉን የፊት ገጽ ያዘጋጃል፡፡ እናም ያለቀለት ‹‹ብሉ-ፕሪንት›› አዘጋጅቶ ወደ ማተሚያ ቤት ይልካል፡፡

በሌላም በኩል፣ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በመሳተፍ ሃሳቡን ያጋራል፣ የሌሎችን ሃሳብ ያነባል፣ በጋራ የዲጂታል ውይይቶችና ክርክሮች ላይ ጎራ ብሎ ይወያያል፣ ይከራከራል፡፡ በሂደቱም እውቀትንና እውነትን ይፈነጥቃል፡፡ ይደንቃል የ90 ዓመቱ አረጋዊ ይህን ሲከውን መመልከት!!!

ወዳጄ፣ ይህን የተግባቦት-ሂደት እንደ ቀላል እንዳትመለከተው፡፡ ብዙ ጊዜያቸውን በምዕራቡ ዓለም ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች ያስተማሩ የቀድሞ ተማሪዎቹ (ወዳጆቹ) በዚህ ሲቸገሩ ተመልክቻለሁና እርሱ ራሱን ከጊዜው ዲጂታል የግልጋሎት መሳሪያዎች ጋር አስማምቶ መጠቀሙን መመስከር ተገቢ ነው፡፡

(ፕሮፍ) በዋናነት እውነትንና እውቀትን ማንጠርና መተቀም ይችልበታል፡፡ በሕይወት ቆይታው፣ የእውቀትን መንገድ ተግቶ ይዞ- አውቋል፤ አሳውቋል፡፡ ተምሯል፤ አስተምሯል፡፡ ለዚህም፣ መምህር የሚለውን የክብር ካባ በጊዜ ደርቧል፡፡ ውሎ እና አዳሩ ልክ እንደ ብትህውና ሕይወት እውቀትን (ዊዝደም) እና እውነትን ፍለጋ ስለሆነ፣ በሂደቱም እርሱ ራሱ እውቀትን ወደ መሆን ተጠግቷል፤ ተሸጋግሯል፡፡

እናም፣ ዛሬ  ማክሰኞ መስከረም 26 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ አራት ኪሎ ቅድሥት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ግብዓተ- መሬቱን የምንፈጽመው ለሀገራችን ቁም-ቤተመዛግብታችንና ቤተ-መጻሕፍታችን  ነው፡፡ ነፍሰሄር መምህር መስፍን!!!

የመምህር መስፍን የሕይወት-ዳራ፡-

አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በ1922 ዓ.ም የተወለደው ብላቴናው መስፍን ወልደማርያም፣ ወደ ዘመናዊው ትምህርት ከመግባቱ በፊት በልጅነቱ በቤተክርስትያን የሚሰጠውን ሐይማኖታዊ ትምህርት በመከታተል ድቁናን እንዳገኘ የህይወት ታሪኩን የከተበው ቢቢሲ ያመላክታል።

ከዚያም በኋላ በአሁኑ የእንጦጦ አጠቃላይ፣ በቀድሞው የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ገብቶ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በመከታተል ጥሩ ውጤት ከሚያስመዘግቡ ተማሪዎች መካከል ለመሆን ችሏል።

በዚህም በወቅቱ ኮከብ ከሚባሉት የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች መካከል ልቆ የተገኘው መስፍን ወልደማሪያም፣ በወቅቱ ለጎበዝ ተማሪዎች ይሰጥ የነበረው የውጪ አገር የትምህርት እድል አግኝቷል።

መስፍን በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ውስጥ ባሳየው ብቃት ከፍ ያለ ትምህርት እንዲከታተል ወደ ህንድ አገር በማቅናት የመጀመሪያ ዲግሪውን ከፑንጃብ ዩኒቨርሲቲ ከተቀበለ በኋላ፣ በማስከተል ደግሞ አሜሪካን አገር ከሚገኘው ክላርክ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪውን አግኝቷል።

መስፍን ወልደ ማርያም ትምህርቱን አጠናቆ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ፣ አብዛኛውን የሥራ እድሜውን ወዳሳለፉበት የመምህርነት ሥራ በመሰማራት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ አገልግሏል።

መስፍን ወልደ ማርያም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በቆየባቸው ዓመታት ውስጥ፣ በጂኦግራፊ የትምህርት ክፍል ውስጥ በመምህርነት እንዲሁም በትምህርት ክፍሉ ኃላፊነት ያገለገለ ሲሆን፣ ለክፍሉ ማስተማሪያ የሚሆኑ መጽሐፍትን በማዘጋጀትም ታላቅ ባለውለታ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም፣ መስፍን ወልደ ማርያም (ፕሮፌሰር) በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በመምህርነት ካገለገለበት ጊዜ ጀምሮ፣ በርካታ የጥናታዊ ጽሑፎችንና ሌሎች መጽሐፍትን በማዘጋጀት አሳትሟል። በተጓዳኝም፣ የተለያዩ ይዘት ያላቸውን ጽሑፎች በማዘጋጀት በጋዜጦች፣ በመጽሔቶችና ፌስቡክን በመሰሉ የማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ጭምር ሲያካፍል ቆይቷል።

በተለይ በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ እየተከሰተ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፈተና ሆኖ የቆየውን መምህር መስፍን “ጠኔ” የሚለውን ረሃብ በተመለከተ፣ ተጠቃሽ መጽሐፍትን አዘጋጅቶ አሁን ድረስ ጉዳዩን በተመለከተ እንደማጣቀሻ ከሚቀርቡ ሥራዎች መካከል በቀዳሚነት የሚነሳ ነው።

መምህር መስፍን፣ የአገሪቱ ተደጋጋሚ ፈተና የሆነውን ረሃብን በምሁር ዓይን በማየት ትኩረት እንዲያገኝ ምርምርና ጽሑፍ ከማዘጋጀት ባሻገር፣ በተለይም በንጉሡ ጊዜ የተከሰተውን ረሃብ ወደተለያዩ ቦታዎች በመሄድ በቅርበት ለመመልከት ከመቻሉ ባሻገር የተቸገሩትን ለመርዳት ከባልደረቦቹ ጋር ጥረት ማድረጉን ብዙዎች ይመሰክሩለታል።

‹‹ፕሮፌሰር›› መስፍን ከትምህርታዊ የምርምር ሥራዎቹ በተጨማሪም፣ ፖለቲካውን ጨምሮ በአጠቃላዩ የዕለት ከዕለት ሕይወቱ ያስተዋለውን ጉዳዮች በማንሳትም ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ትችትን እንዲሁም ምክሮችንም በጽሑፎቹ ያለፍርሃትና ይሉኝታ የሚያንጸባርቅ ምሁር ነበር።

ሃሳቡን በመጽሐፍ፣ በመጣጥፎች፣ በመጽሔትና በጋዜጣ እንዲሁም በጣፈጠና በአጭሩ ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚያቀርበው መምህር መስፍን፣ በግጥምም ጠንካራ ሃሳቦቹን የሚገልጽ ምሁር ነበር።

ለዚህም እንደ ማሳያ አሁን ድረስ መነጋገሪያ እንደሆነች ያለችው የፕሮፌሰሩ የሥነ ግጥም ስብስብ መድብል የሆነችው “እንጉርጉሮ” ማሳያ ናት። ‘እንጉርጉሮ’ የተለያዩ ጉዳዮችን በማንሳት በተመረጡ ቃላት ጥልቅ መልዕክትን የያዘች የግጥም መጽሐፍ እንደሆነች በርካታ አንባቢያን ይመሰክራሉ።

መምህር መስፍን፣ በእንግሊዝኛ ከዘጋጃቸው መጽሐፍት ባሻገር፣ በአማርኛ ቋንቋ ኢትዮጵያ ከየት ወዴት፣ አደጋ ያንዣበበበት የአፍሪካ ቀንድ፣ ሥልጣን ባሕልና አገዛዝ፣ ፖለቲካና ምርጫ፣ የክህደት ቁልቁለት፣ አገቱኒ (ተምረን ወጣን)፣ መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ፣ አድማጭ ያጣ ጩኸት፣ እንዘጭ! እምቦጭ! የኢትዮጵያ ጉዞ፣ አዳፍኔ፣ ፍርሃትና መክሸፍ፣ ዛሬም እንደ ትናንት እና ሌሎችም መጽሐፍትን አሳትሟል።

የመምህር መስፍን የፖለቲካ ሕይወት ዳራ፡-

መምህር መስፍን በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ ማድረግ የጀመረው ከንጉሡ ጊዜ ጀምሮ ነበር። የሕዝቡ የመብትና የኑሮ ጥያቄዎች እንዲሁም በየዘመኑ ይነሱ የነበሩ የለውጥ ፍላጎቶችን በመደገፍ በተለያየ መንገድ ተሳትፏል።

በዩኒቨርስቲው ውስጥ ይነሱ የነበሩ የተማሪዎችን የለውጥ ጥያቄዎች ይደግፍ በነበረው መምህር መስፍን፣ በንጉሡ ባለስልጣናት በኩል በጎ አመለካከት አልነበረም። ስለዚህም በሹመት ስም ከአዲስ አበባ እንዲወጡ ለማድረግ ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ ጊምቢ አስተዳዳሪ ሆኖ መሾሙ ሲነገረው ሹመቱን ተቃውሞ ነበር።

ከዚያም በወቅቱ በወሎ ክፍለ አገር በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ ለችግር ተጋልጠው የነበሩት ሰዎች ቀያቸውን እየተው ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት በሚሞክሩበት ወቅት ባለስልጣናት ረሃቡ እንዳይታወቅ ጥረት ማድረጋቸውን የተመለከተው መምህር መስፍን፣ ችግሩን ለሕዝቡ ለማሳወቅ የቻለውን አድርጓል።

በዚህም ረሃቡ ያስከተለውን ጉዳትና ለችግር የተዳረጉትን ሰዎች የሚያሳይ የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን በዩኒቨርስቲው ውስጥ ላለው የመምህራን ማኅበር አቀረበ። ከተለያዩ ሰዎችም እርዳታን በማሰባሰብ በረሃብ ለተጎሳቆሉት ሰዎች ለማድረስ ጥረት ማድረጉ በቅርብ የሚያውቁት ሰዎች ይመሰክራሉ።

መምህር መስፍን ድርቁንና የተከተለውን ረሃብ በተመለከተ ሌሎች እንዲያውቁት በማድረግ በኩል ቀዳሚ ከመሆኑ ባሻገር፤ የንጉሡ አስተዳደርን ኋላ ላይ ለውድቀት የዳረገው የተማሪዎች ጥያቄና እንቅስቃሴ ተጨማሪ ምክንያት ለመሆን በቅቷል።

ወታደራዊው ደርግ የንጉሡን አስተዳደር አስወግዶ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ፣ ለበርካታ ሰዎች ዕልቂት ምክንያት የሆነውን የወሎ ክፍለ አገር ረሃብን በተመለከተ የሚያጣራው መርማሪ ኮሚሽን ውስጥም አባል ሆኖ ሰርቷል።

በደርግ ዘመን አብዛኘውን ጊዜውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በማስተማር ያሳለፈ ሲሆን፤ በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የነበረው የእርስ በርስ ጦርነት እየበረታ በሄደበት ጊዜ የነበረው መንግሥት ችግሮች ከቁጥጥር ውጪ ከመሆናቸው በፊት ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈለግ ከሌሎች ሰዎች ጋር በመሆን ጥሪ ሲያቀርብ ነበር።

ከዚያም ወታደራዊው መንግሥት በአማጺያኑ ኃይሎች ተሸንፎ ከስልጣን ሲወገድና ኢህአዴግ አገሪቱን በተቆጣጠረ በአጭር ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) የተባለ ድርጅት በማቋቋም፣ በአገሪቱ ስለሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ክትትል ማድረግና ሪፖርቶችን ማውጣት ሀገርን ሲያገለግል ነበር።

መምህር መስፍን ወልደማርያም ለረጅም ዓመታት ኢሰመጉን በሊቀመንበርነት በመራበት ጊዜያት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተለይ የመንግሥት ኃይሎችና ባለስልጣናት የሚፈጸሙ ሪፖርቶችን ሲያወጣ ቆይቷል።

ብዙ የተባለለትና ከባድ ቀውስን አስከትሎ የነበረው የ1997ቱ ምርጫ ሊካሄድ በተቃረበበት ጊዜም የቀስተ ዳመና ንቅናቄ ለማኅበራዊ ፍትህ (ቀስተ ዳመና) የተባለ የፖለቲካ ፓርቲ ከእነ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና ከሌሎችም ጋር እንዲመሰረት አድርጓል።

ይህም ፓርቲ በኋላ ላይ በምርጫው ላይ አውራ ፓርቲ ነኝ ይል የነበረውን ኢህአዴግን በመገዳደር በኩል ትልቅ ሚና የነበረውን ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ (ቅንጅት) የተባለውን ጥምረት ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ለመመስረት ችሏል። በዚህ ሂደት ውስጥም መምህር መስፍን የጎላ ሚና እንደነበረው ይነገራል።

ምንም እንኳን መምህር መስፍን በምርጫው ላይ ተወዳዳሪ ሆኖ ባይቀርብም በሚደረጉ የምርጫ ክርክሮች ላይ ቀርቦ የፓርቲውን ዓላማ በማብራራት ተሳታፊ ነበር።

በኋላም ከምርጫው ውጤት ጋር በተያያዘ በተፈጠረው ውዝግብና ሳቢያ መንግሥት የቅንጅት አመራሮችን ሲያስር ፕሮፈሰር መስፍንም ለእስር ተዳርጎ ነበር። ይህ እስር ግን የመጀመሪያው አልነበረም፤ ቀደም ሲልም በተለያዩ ጊዜያት ለእሥር ተዳርጎ ነበር።

ተጠቃሽነቱ፡- ሳይማር ላስተማረኝ ሰማዕታት ወገኔ …

‹‹ሞታችሁ ለኛ ሕይወት-

ሰቃያችሁ ለኛ ልማት፣

ውርደታችሁ ለኛ ክብር …

ዕዳችሁን ለመክፈል ባልችልም፤

እንዳለብኝ (ግን) አምናለሁ፡፡ …

(ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም፣ መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ)

ታዋቂው ምሁር፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋችና ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም መስከረም 19 ቀን 2013 ዓም ለረቡዕ አጥቢያ በ90 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው እንደተሰማ ነበር ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ፡-“የሐሳብ ልዕልና ምልክት፤ የሰላማዊ ትግል አርአያ፣ ላመኑበት ነገር እስከ መጨረሻቸው ሞጋች፣ ላመኑበት እውነት ብቻ የሚቆሙት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም በማረፋቸው ጥልቅ ሐዘን ተሰምቶኛል።” ሲሉ ነበር  የሃዘን መግለጫቸውን ያሰፈሩት፡፡

ቻዎ-ቻዎ ፕሮፍ!

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *