ለስኳር በሽታ ዓይነት-፪ ሞሞርዲካ ከወዴት አለሽ!? (Diabetes type 2)

Views: 314

መነሻ፡-

በዚህ ዘመን የስኳር በሽታ ሥር የሰደደ እየሆነ መጥቷል፡፡ በዘመናዊ የሕክምና ዘዴ በሳይንስ የተደገፈ ሕክምና ያለው ቢሆንም እንኳ፣ ከዓመታት ብዛት ብዙ ውስብስብ ችግር ማስከተሉ እሙን ነው፡፡ በአመጋገብ ዘዴ እና በተፈጥሮ መድኃኒት በሽታውን ማስታገስ ወይም ማስታመም ብዙዎች የሚስማሙበት ነው፡፡

ስለሆነም፣ በብዙ ጥናት ብዙ የመድኃኒት ዕፅዋት ተመራጭ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ በኤሽያ አገራት በተለይም በህንድ እና ቻይና ልዩ ትኩረት ከተሠጣቸው ውስጥ ‹‹ሞሞርዲካ›› አንዱ ነው፡፡ ሞሞርዲካ ብቸኛው ፈዋሽ የመድኃኒት ተክል ባይሆንም እንኳን፣ የተሻሉ ናቸው ከተባሉት ተርታ ግን ይሰለፋል፡፡

ከዚህ ጋር በተገናኘ የስኳር በሽታን ውስብስብ ችግር ተከላከሉ በሚል ርዕስ በዚሁ ዓምድ  https://ethio-online.com/archives/7065   ሊንክ ላይ ያለውን አንብቡ፡፡  እንዲሁም ለስኳር በሽታ ዓይነት አንድ የግመል ወተት እና የጤና በረከቱ  በዚህ ሊንክ https://ethio-online.com/archives/10075  ላይ ያለውን አንብቡ፡፡

ሀ/ መጠሪያ ስሞቹ

በሳይንሳዊ መጠሪያ (Momordica charantia  L፤ ሞሞርዲካ ቻራንቲያ)፤ በእንግሊዘኛ (Bitter melon ቢተር ሜሎን፣ Bitter Gourd ቢተር ጉርድ)፤ በፈረንሳይኛ ( Poire de balsam  ) በጀርመንኛ  (Wachskürbis, Bittergurke) ይባላል፡፡ ከዚህ ሁሉ ለአማርኛ መጠሪያ አመቺ የሚሆነው ሞሞርዲካ የሚለው ይመስለኛል፡፡ ይህ የሳይንሳዊ መጠሪያም ስለሆነ፡፡ በአፋን ኦሮሞ-ም እንዲሁ Momordika  ቢባል ያግባባል፡፡

ለ/ ሞሞርዲካ መገኛው የት ነበር፡-

ነቅ መገኛ አገሩ ህንድ ነው፡፡ በ14ኛው ክፍለ ዘመን ወደ ቻይና ደረሰ፡፡ በቻይና ከደረሰ በኋላ በነሱ የምግብ ጓዳ መደበኛ እና ባለብዙ ዝና ሆነ፡፡ በቻይና ባሕል ሞሞርዲካን መመገብ የደም ስኳር ይቀንሳል፣ ጉበት እንዲያገገም ይረዳል፣ ሰውነት ከመርዛማ ነገሮች ያፀዳል ተብሎ ይታመናል፡፡ በዚህ ዘመን በብዙ የአውሮፓ እና አሜሪካ አገራትም ይገኛል፡፡ በፋብሪካ ደረጃ ተቀናብሮ የተዘጋጀም በብዙ አማራጭ አለ፡፡

ሐ/ ሞሞርዲካ በእኛ አገር፡-

ይህ ተክል ለኢትዮጵያ አዲስ ነው፡፡ ገበያ ላይ የለም፡፡ በማንም በምንም መንገድ መጥቶ በጥቂቶች ጓሮ ግን ይገኛል፡፡ ይህን አፈላልጎ ማልማት ግን እጅግ ቀላል ነው፡፡ ከአንድ አመት በፊት ከገዛ ጓሮው ውስጥ ተክሉን አሳይቶኝ፣ ዘሩንም የሠጠኝ ሰው የተመሠገነ ይሁን!፣ አሁን ማፍራት ጀመረ፡፡ ያው ከላይ መነሻው ላይ ያለው ምስል ማለት ነው፡፡ የህንድ ዓይነቱ ክርችፍችፉ አካል ዓይነት መሆኑ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ውስጥ፣ ወይም በአገሪቱ በየትኛውም አካባቢ አልፎ አልፎ በጓሮ ይገኛል፡፡

መ/ ዓይነቱ ስንት ነው፡-

ሞሞርዲካ አበቃቀሉ እንደዘርማዘሩ ሐረግ ተክል ነው፡፡ በዛፍ ላይ፣ በአጥር ላይ ተንጠላጥሎ ማደግ ይወዳል፡፡ ወይናደጋ ወዳድ ነው፡፡ በዋናነት ሁለት ዓይነት ነው፡፡ የህንድ ዓይነት የተባለው ክርችፍ አካል ያለው (Indian bumpy skin). እና የቻይና ዓይነት ልስልስ  (Chinese smooth skin) አካል ያለው ነው፡፡ በቀለሙ ብርቱካናማ፣ ጥቁር አረንጓዴ፣ ሲሆን፣ ፍሬው እየበሰለ ሲሄድ ደማቅ ቢጫ ይሆናል፡፡ በታይዋን ደግሞ ነጭ ዓይነት ሞሞርዲካ አለ፡፡

ሞሞርዲካ ክርችፍችፉ የህንድ ዓይነቱ፣ ማጣቀሻ አንድ

መቼም የመድኃኒትነት በረከቱ እጅግ የበዛ ስለሆነ እንጂ፣ ለውበቱ ብሎ ማንም ዞር ብሎ ባላየው ነበር፡፡ መልከ ጥፉ ነው፣ መራር ነው፡፡ ግን ደግሞ ባለብዙ የጤና በረከት ነው፡፡

ሞሞርዲካ ልስልሱ የቻይና ዓይነቱ፣ ማጣቀሻ አንድ

ሠ/ ሞሞርዲካ መራር ጣዕሙ፤

ከሁሉም ተክሎች ወይም ፍራፍሬዎች ይበልጥ በመራርነቱ ይታወቃል፡፡ በተለይም ዝም ብለው ቢሠሩት እና ከውስጥ ፍራቻ ያለበት ሰው ምሬቱን መቋቋም ይቸግረው ይሆናል፡፡ ነገር ግን ፍራፍሬውን  በአበሳሰል ሂደት እና ከሌሎች ጋር ተስማሚ አድርጎ ቀምሞ መሥራት ይቻላል፡፡  ከአረጓ ዓይነቱ ደግሞ ነጩ በጣም ይመራል፡፡

በጊቢ ካለማሁት ቅጠሉን እንደሻይ አፍልተን ባየነው ጊዜ፣ የሻይው ቀለም እጅግ ይማርካል፣ ጣዕሙ ግን ከአቆራራጭ ይበልጥ ይመራል፡፡ የሚገርመው ምሬቱ እስከ ጆሮ ግንድ ድረስ ይሰማል፡፡ እንዲህ ዓይነት ምሬት ቀምሼ አላውቅም፡፡ እሬት በዚህ ዓይነት ማር ማለት ነው፡፡ ግራዋ ደግሞ ስኳር ማለት ነው፡፡   ምን ይደረግ እንግዲህ! በብዙ ጥናት የተወደሰው የመድኃኒትነት ብቃቱ እዚህ ምሬቱ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ያነበበ፣ የተረዳ ምሬቱን ተቋቁሞ መጠጣት ይችላል፡፡ ምሬትም ቢሆን ጥዑም ነው- ለጤና!!!

ሞሞርዲካ ቅጠሉ እና የሻይው ምስል

ረ/ ሞሞርዲካ አሠራር

ፍራፍሬውን መቀቀል ወይም መጥበስ፡-

 • ፍራፍሬውን ማጠብ፣ ጫፉን መቁረጥ፣ ለአንድ ሰው አንድ ትልቁ በቂ ነው፡፡
 • ለሁለት መሰንጠቅ፣ የውስጡን ፍሬ ጠርጎ ማስወገድ፤
 • በክብ በቀጫጭኑ መክተፍ፣
 • በጨው ውሃ ውስጥ መዘፍዘፍ፣ ውሃውን ቀይሮ ማፍሰስ፣
 • ከዚያም መቀቀል፣ ወይም በመጥበስ መልክ መሥራት ነው፡፡
 • በቀይና ነጭ ሽንኩርት፣ ዘይት፣ ጨው፣ ቃርያ፣ ሶያ ሶስ ወዘተ ማብሰል ነው፡፡ ከ 5 እስከ 1ዐ ደቂቃ ውስጥ ይበስላል፡፡ ከሌላ ተስማሚ አትክልት ጋር ለምሳሌ ብሮኮሊ፣ አበባ ጎመን፣ ካሮት ጋር ማብሰል ይቻላል፡፡
 • ለምሳሌ ቻዮቴ ለስኳር ታማሚዎች የተወደሰ ነው፣ ደግሞ በጣም ጥፍጥና አለው፡፡ ቻዮቴን በስስ መፈቅፈቅና አብሮ ማብሰል ይቻላል፡፡ እንደዚህ ሠርተነው በጣም ጥሞን በላነው፡፡

ፍራፍሬውን ጁስ መስራት፡-

 • አንዱን ፍራፍሬውን ማጠብ፣ ጫፉን መቁረጥ፣
 • መሰንጠቅ ፍሬውን ማውጣት እና ለዘር የሚሆን ከሆነ ማስቀመጥ፣ እንጭጭ ከሆነ ግን ልጆች ከማይደርሱበት መጣል፣
 •  ለ1ዐ ደቂቃ ያህል መቀቀል፣
 • ከነ ውሃው በጁስ መፍጫ መፍጨት፣ ከዚያም እንደ ጁስ ማዘጋጀት፡፡

ቅጠሉን ሻይ ማፍላት፡-

ቅጠሉን እርጥቡን ወይም ደረቁን እንደ ሻይ ማፍላት እና በማር ወይም እንዲሁ ምሬቱን ተቋቁሞ መጠጣት፡፡

የደረቀውን መዘፍዘፍ፡-

የደረቀውን የሞሞርዲካ ደረቅ (እንደ ቋንጣ ያለ) ፍራፍሬ ለብ ባለውሃ መዘፍዘፍ እና ለግማሽ ሰዓት ማቆየት፣ ከዚያም ማጠብ እና እንደሚፈለጉት መሥራት ነው፡፡

ሰ/ ሞሞርዲካ ማቆያ ዘዴው፡-

ፍራፍሬውን ማጠብ፣ መሰንጠቅ እና ፍሬውን ማውጣት፣ በስስ መክተፍ፣ በፀሐይ ላይ ማስጣት እና ማድረቅ፣ የደረቀው ለብዙ ጊዜ ይቆያል፡፡ ቅጠሉንም አድርቆ ማቆየት ይቻላል፡፡

ሸ/ ሞሞርዲካ መድኃኒትነቱ   (የመረጃ ምንጭ ማጣቀሻ ሁለት)

 • የሞሞርዲካ ፍራፍሬን መብላት ወይም ጁሱን መጠጣት ደም ያጠራል፡፡
 • ሞሞርዲካ ለስኳር በሽተኞች (ዓይነት 2) ሐይፓግላሴሚክ ውሑድ (hypoglycemic compound ) ስለያዘ፣ ይህ ማለት የዕፀዋት ኢንሱሊን ማለት ነው፤ የደም ስኳርን ዝቅ ለማድረግ ጠቃሚ ነው፡፡
 • ሁለት የሾርባ ማንኪያ ጂስ፣ ከሁለት የሾርባ ማንኪያ ቀይ ሽንኩርት እና ሁለት የሾርባ ማንኪያ የሎሚ ውሃ ጋር በማደባለቅ ገና ለጀመረው ኮሌራ በሽታ ማከሚያ ይሆናል፡፡
 • ቤታ ካሮቲን በበቂ መጠን የያዘ ስለሆነ፣ የዓይን የማየት አቅም (improving one’s eyesight.)  ለማሻሻል ይረዳል፣
 • ይህ መራር ጣዕሙ ከሰውን በሽታ የመከላከል አቅም ሥርዓት (boost the immune system) ከፍ ያደርጋል፤
 • ሁለት የሾርባ ማንኪያ ጁስ ከአንድ ብርጭቆ እርጎ ወተት ጋር በቀን 3 ጊዜ መጠጣት፣ የፊንጢጣ ኪንታሮት (Piles or hemorrhoids) ለማስታመም ይጠቅማል፣
 • በመደበኛነት እንደ ዕለታዊ ምግብ መመገብ የቆዳ ችግሮችን እንደ ፓሶሪያሲስ (psoriasis)፣ እና የቆዳ ላይ ፈንገስ በሽታ እንደ አጓጉት እና የእግር ጮቅ (ringworm and athletes foot) ለማስወገድ ይረዳል፡፡
 • ጁሱን መጠጣት ሰውነትን ከመርዛማ ነገር ለማጽዳት (detox the body) ይረዳል፤

ቀ/ ሞሞርዲካ እንዳይበሉ የሚመከሩቱ፡-

 • የደም ስኳርን ዝቅ በማድረግ ያለተጠበቀ ችግር ላይ ሊጥላችሁ ይችላልና፣ ሌላ የስኳር በሽታ መድኃኒት የምትወስዱ ከሆነ ሞሞርዲካ ይቅርባችሁ፡፡
 • የሞሞርዲካ የውስጡ ዘር ፍሬ ምሬቱም ከባድ ነው፣ ወደ ሰው ሆድ ከገባ ቀይ የደም ሴሎችን ይመርዛል፤ ራስ ምታት፣ ትኩሳት፣ የሆድ ሕመም እና እራስን ማሳት ያደርሳል፣ ስለዚህ ፍሬው ፈጽሞ አይበላም፡፡
 • ለህፃናት፣ ለእርጉዝ እና ለሚያጠቡት እናቶች አይሰጥም፡፡

ማጠቃለያ፡-

ይህን ተክል ባለበት ስታገኙ ተንከባከቡት፣ ወይም ሰዎች እንዲንከባከቡት ምክር ስጡ፡፡ ፍራፍሬው ለምግብነት እና ለመድኃኒትነት ከላይ እንደተነገረው ይውላል፡፡ ለዘር ሲሆን በሐረጉ ላይ እንዲቆይ ተውት፤ ሙሉ ቢጫ ሲሆን ግን ከመበስበሱ በፊት አውርዶ ፍሬውን ማውጣት ነው፡፡ ፍሬው ጠቆር ይላል፡፡ በፀሐይ ከደረቀ በኋላ ጥቂት ሳምንታት አቆይቶ መልሶ መትከል ነው፡፡ ለሶስት ወራት እድገቱ በጣም አዝጋሚ ነው፡፡ እንዲንጠላጠል ማድረግ ነው፡፡ ከተመቸው ከ 6 ወራት በኋላ ብዙ ያፈራል፡፡ ከሥር በቂ ውሃ በየጊዜው ማጠጣት እና የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ሞሞርዲካ፣ የሱን መሰሉ በኢትዮጵያ ዱር በቀል የሆነው የቁራ ሐረግ (Momordica foetida ሞሞርዲካ ፎቲዳ) ይባላል፡፡ ነገር ግን የቁራ ሐረግ የሚባሉ ብዙ ዓይነታት አሉ፡፡ እነዚህ የቁራ ሐረግ የተባሉት ምን ያህል የተጠኑ ቢኖሩ፣ ለምን ጥቅም እንደሚውሉ ያነበበ ወይም ከማህበረሰብ ዕውቀት የተረዳ ቢኖር ይፃፍልን፡፡ ሌላም ተጨማሪ ነገረ ሐሳብ ቢኖራችሁ ፃፉልን፡፡

                                                                                                                                               

ማጣቀሻ አንድ https://timesofindia.indiatimes.com/life-style/health-fitness/diet/ ምስሎቹ ከዚህ ሊንክ የተገኙ ናቸው፡፡

ማጣቀሻ ሁለት   https://food.ndtv.com/food-drinks/bitter-gourd-tea-how-to-make-this-herbal-tea-to-manage-diabetes-and-fight-chol

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com