ዐይናችን- ዐይን ፈልጓል!

Views: 189

መግቢያ፡-

የዘመኑ ሳይንስና ቴክኖሎጂ (ዕደ-ጥበብ) ካተረፈልን ብዙ ቁም ነገሮች ባሻገር፤ የተወሰኑት ዐይናችንን (ብርሃናችን)ን አድካሚ ሆኖ ቢገኝ ምን እናድርግ!?

ዘመኑ ካፈራው የ‹‹ቴክኖሎጂ›› ውጤት ውስጥ ጽሑፍን፣ ንባብን፣ ማህበራዊ ትሥሥርን፤ ወዘተ … እጅግ ፈጣን፣ ቀላል እንዲሆን ያረጉልን ኮምፒውተር እና አብረውት የበለፀጉ ተጓዳኝ ዕደ-ጥበቦች በርካታ ናቸው፡፡ እንደ ዋቢ ኮምፒውተር እና ተንቀሳቃሽ ስልክን ብንመለከት እንኳ፣ መሠረታዊ መገልገያ ሆነዋል፡፡ ያለ እነሱ ምንም መሥራት በማንችልበት ደረጃ ላይ እየደረስን ነው፡፡

ቀኑን ሙሉ በኮምፒውተር መስታወት ላይ ተጠምደን እንውላለን፡፡ ቴሌቪዥን እና የእጅ ስልኮችም እንዲሁ አዘውትረን የምናፈጥባቸው የዐይን ማዕከላችን ናቸው፡፡ ይህ መሆኑ ዐይናችንን እያዳከመ መሄዱ እሙን ነው፡፡  በእርግጥ ሌሎችም ብዙ ዐይን አድካሚ የሆኑ ምግቦች፣ መጠጦች፣ የኑሮ ዘይቤዎችም አሉ፡፡ ብዙ የዐይን ህመሞችም እንደ ካትራክት፣ ግላጎማ፣ የሚባሉ አሉ፡፡  ለዚህ ሁሉ ችግር ቀላል መፍትሔ እዚህ ይገኛል ቢባል ዘበት ነው፡፡ ዘመናዊ ሕክምና መነጽሮች በማበርከቱ በቂ ነው ቢባል እንኳ፣ ብቻውን፣ ብቸኛ መፍትሔ አለመሆኑ ግን እርግጥ ነው፡፡

የሆነው ሆኖ ዐይናችን ለማየት፣ ለማንበብ፣ በደከመ ጊዜ በሌሎች ተቋማት የሚሰጠው ሕክምና፣ መድኃኒት ወዘተ እንዳለ ሆኖ፤ እስኪ የሚከተሉትን እናስተውል፡፡

ሀ) ዘወትር ማለዳ በንፁህ ውሃ መታጠብ

ሁል ጊዜ ማለዳ በንፁህ ውሃ ደህና አድርጎ የዐይን ውስጡን ጭምር መታጠብ ጥሩ ነው፡፡

ለ) ብርትኳን፣ቀይ ሽንኩርት እና ዓሳ ዘይት

ብርትኳን ለሚስማማው ሰው ጥሩ የቫይታሚን መገኛ ነው፡፡ ቀይ ሽንኩርት የታረሰው እና ለገበያ የቀረበውን በሙሉ በጓዳ ድስት ውስጥ ማቁላላት በተባለ የባልትና ዘርፍ አበላሽተነዋል፡፡ እንጂማ ከምንገዛው ቀይ ሽንኩር ጥቂቱን በጥሬው ብንመገብ ለጤና ብዙ አበርክቶ በኖረው ነበር፡፡ በዚሁ ዓምድ ላይ “የቀይ ሽንኩርት ብክነት በማሳ እና በድስት” በሚል ርዕስ፣ በዚህ ሊንክ

https://ethio-online.com/archives/7272  ላይ አንብቡ፡፡ ቀይ ሽንኩርት የብዙ በሽታ መድኃኒት ነው፡፡

በዚህ ዩቲዩብ የመረጃ ምንጭ ላይ  https://www.youtube.com/watch?v=4JiHpGocWrU

Drink FOR STRONGER VISION AND REMOVE CATARACT, GLAUCOMA      እንዲህ ይላል፤

 • ሁለት መካከለኛ ብርቱካን ለሁለት መክፈል እና ጭማቂ ማዘጋጀት፣
 • ከአንድ እራስ ቀይ ሽንኩርት ጋር በጁስ መምቻ ማሽን መፍጨት፤
 • ከተፈጨ በኋላ ደህና አድርጎ መጭመቅ ወይም ማጥለል፣ ሽንኩርቱ ወደ ላይ ይቀራል፤
 • በተገኘው ጭማቂ ላይ አንድ ኮድ ሊቨር ኦይል ካብሱል ጫፉን ቆርጦ ዘይቱን በላዩ መጨመቅ፤
 • ለተወሰነ ሰዓታት በፍሪጅ ማቆየት ይቻላል፡፡ ጠዋት ወይም ማታ አንድ ኩባያ መጠጣት ለዐይን ካትራክት እና ግላኮማ ድንቅ ነው፡፡  ለአንድ ወር መጠጣት ከዚያም ደግሞ ለወራት ዕረፍት ማድረግ፡፡ እንደአስፈላጊነቱ መቀጠል፡፡

ይህ የሶስቱ በአንድነት መጨመቅ እና መዘጋጀት ከፍተኛ በረከት አለው ማለት ነው፡፡ እስቲ ሞክሩት፡፡ ጉዳዩን ለማመን  ቢቸግራችሁ ይበልጥ አንብቡ፡፡

ሐ) ሰንሰል በሸክላ  የመረጃ ምንጭ  (ሕክምና በቤታችን)

ሰንሰል በጣም ብዙ የጤና ጠቀሜታ ያለው አገራዊ የቁጥቋጦ ዛፍ ነው፡፡              https://ethio-online.com/archives/7470 በዚህ ላይ የሰንሰል ጠቀሜታ በሰፊው ማንበብ ትችላላችሁ፡፡

 • የሚታጠነው ሰው ለመኝታ ከመዘጋጀቱ በፊት ሁሉንም አስቀድሞ ያመቻቻል፤
 • ለጋ የሰንሰል ቅጠል መቶ ግራም ያህል፣ ማጠብ እና ማዘጋጀት፤
 • አንድ ሊትር ንፁህ ውሃ ጨምሮ በሸክላ ድስት ወይም በሸክላ ማሰሮ መቀቀል፤
 • 1ዐ ደቂቃ ያህል ከፈላ በኋላ፣ ታካሚው ተሸፋፍኖ ይታጠኗል፡፡
 • የዕንፍሎቱን ሙቀት መቋቋም በቻለ መጠን ዐይኑን ከፍቶ፣ ከ1ዐ እስከ 2ዐ ደቂቃ እታጠነ ይቆያል፤
 • ወድያውም ተሸፋፍኖ ይተኛል፡፡
 • ቀጥሎም የተቀቀለበት ዕቃ ተከድኖ ያድራል፡፡
 • ማለዳ የተቀቀለበት ውሃ ተጠሎ የዐይን ማጠቢያ ይሆናል፤
 • ከዚያም ጥቂት ቆይቶ ወደ ፀሐይ ከመውጣቱ በፊት ገላውን ይታጠባል፡፡
 • ይህን ለአንድ ሳምንት ብቻ መጠቀም በቂ ነው፡፡
 • አስፈላጊ ቢሆን ከወራት በኋላ እንዲሁ መቀጠል ይቻላል፡፡

መ) የጠሐይ በድር ቅጠል በሸክላ የመረጃ ምንጭ  (ሕክምና በቤታችን)

            በሳይንስ ስሙ (Dicliptera taxataይባላል፡፡ ይህ ቅጠል ብዙ አገራዊ የሕክምና ጥቅሞች አሉት፡፡ ዋና መገኛው በጉራጌ፣ በከፋ፣ በዳውሮ እና በእነዚህ አቅራቢያ አካባቢ ነው፡፡ ብዙ አገልግሎት የሚሰጠውም በዚሁ በብዛት በሚገኝበት አካባቢ ነው፡፡  ነገር ግን አሁን በብዙ ከተሞች በየጓሮ ተተክሎ ይገኛል፡፡ በየቦታው መጠሪያውም የተለያየ ነው፡፡

የጠሐይ በድር ለዐይን ሕክምና አጠቃቀም፤

 • ማታ የሚታጠነው ሰው ለመኝታ ይዘጋጃል፤
 • ለጋ የጠሃይ በድር ዘንጎች ከቅጠል ጋር አንድ ጭብጥ ያህል፣ ማጠብ እና ማዘጋጀት፤
 • ግማሽ ሊትር ንፁህ ውሃ ጨምሮ በሸክላ ድስት ወይም በሸክላ ማሰሮ መቀቀል፤
 • ሁለት ደቂቃ ያህል ከፈላ በኋላ፣ ታካሚው ተሸፋፍኖ ይታጠኗል፡፡
 • የዕንፍሎቱን ሙቀት መቋቋም በቻለ መጠን ዐይኑን ከፍቶ፣ እየታጠነ ይቆያል፤
 • ወድያውም ተሸፋፍኖ ይተኛል፡፡
 • ይህን አምስት ቀናት ብቻ መጠቀም በቂ ነው፡፡
 • አስፈላጊ ቢሆን ከወራት በኋላ እንዲሁ መቀጠል ይቻላል፡፡

 

ምስል 1፣ የጣይ በድር ቅጠል

የሰንሰል ቅጠል እና የጠሐይ በድር ቅጠል ለታመመ ዐይን፣ ባሕላዊ ተፈጥሮአዊ የማከሚያ ዘዴዎች ናቸው፡፡ ሆኖም በተለያየ ምክንያት ለተዳከመ ዐይንም ጭምር ይረዳሉ፡፡

ሠ) ሌሎች ጠቃሚ ምክሮች

 • ተስማሚ ፍራፍሬ ጠቀም አድርጎ መመገብ፣ እንደ ወይን፣ እንጆሪ፣ ብርቱካን፣ ወዘተ
 • ተስማሚ የሆኑ አትክልት ለምሳሌ ካሮት፣ ዱባ፣ ቢጫ ስኳር ድንች፣ ብሮኮሊ፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ቀይ ሽንኩርት፣ ቃሪያ፣ ወዘተ
 • ኦሜጋ 3 ፋቲ አሲድ የሚገኙባቸው ምግቦችን ማዘውተር፡፡ ከነዚህም በእኛ አገር በስፋት የሚገኘው ተልባ ነው፡፡ ተልባ በሙቀት ከተጎዳ የተባለውን ጥቅም አይኖረውም፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ከተልባ የሚዘጋጀው ዘይት ሳይቀር በሙቀት የተጎዳ ነው፡፡ በምድረ አውሮፓ የዘይት ጨመቃው በቅዝቃዜው ነው፡፡ ኮልድ ፕረስ የተልባ ዘይት ተብሎ በውድ ዋጋ ይሸጣል፡፡

ማጠቃለያ፡-

ለዐይን ጤና የሚረዱ በመላው አገሪቱ ብዙ ተፈጥሮአዊ ዘዴዎች አሉ፡፡ በይበልጥ ማድመጥ ብዙ ዕውቀት ያስገኛል፡፡ መቸም ቢሆን ዐይን ከሚያደክሙ ነገሮች እራሳችንን መከላከል አለብን፣ የዐይንን የማየት አቅም የሚደግፉ ነገሮችን ደግሞ መከታተል ይበጀናል፡፡ ዐይናችን- ዐይን ፈልጓልና ልብ እንበል!!!

የአይን ፎቶ የተወሰደው ከ https://wexnermedical.osu.edu/blog/poked-in-the-eye ነው።

መልካም ጤና፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com