ቅምሻ ከወዲያ ማዶ፡- ኪም ካርዳሺያንና ሊዮናርዶ ዲካፕሪዮ የፌስቡክ ተቃውሞን ተቀላቀሉ

Views: 42

ፌስቡክ በመላው ዓለም ሰላም አፍራሽ የጥላቻ ንግግሮችን በጊዜ ባለማስወገዱ ከፍተኛ ጥፋት እያደረሰ ይገኛል፡፡ይህንን በመቃወም ከፍተኛ ተቃውሞ እየተካሄደ ነው፡፡ ይህንን ተቃውሞ እውቅ የዓለማችን ሰዎች እየተቀላቀሉት ነው፡፡

በአሜሪካ ‹‹የካርዳሺያን እውናዊ ትእይንት (ሪያሊቲ ሾው)›› ላይ ገናና የሆነችው ኪም፣ በፌስቡክ ሐሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር ላይ የተጀመረውን ተቃውሞ መቀላቀሏን ይፋ አድርጋለች፡፡

የሙዚቃ አቀንቃኙ የካኒዮ ዌስት ባለቤት ኪም ይህን ተቃውሞ ስትቀላቀል የመጀመርያዋ ሥመ ጥር አይደለችም፡፡

በርካታ የሆሊውድ ዝነኞችም ተቃውሞው ላይ በይፋ ገብተውበታል፡፡ ፕሮፓጋንዳ፣ የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትና የጥላቻ ንግግር ይቁም የሚለው ተቃውሞ እየተደረገ ያለው በተለያየ መንገድ ሲሆን፣ አንዱ ዘዴ የፌስቡክና የኢኒስታግራም አድራሻን ለአጭር ጊዜ በመዝጋት ነው፡፡

የተቃውሞው መፈክር #በጥላቻ ንግግር ማትረፍ ይቁም! (#StopHate for Profit) የሚል ነው፡፡

በዚህ ተቃውሞ እንቅስቃሴ የሚሳተፉ የዓለም ዜጎች ዛሬ ረቡዕ ለ24 ሰዓታት የፌስቡክ ገጻቸውን ይዘጋሉ፡፡ ከነዚህም አንዷ ኪም ካርዳሺያን ዌስት ናት፡፡

ኪም እንደተናገረችው ‹‹ፌስቡክ በጥላቻ ንግግር ሲነግድ ቁጭ ብዬ ልመለከት አልችልም›› ብላለች፡፡

ከኪም ሌላ ዝነኛው ተዋናይ ሊዮናርዶ ዲካፕሪዮ፣ ኦርላንዶ ብሉም፣ ቦራት በሚል የተሳልቆ ሥራው ዋና ገጸባሕሪ ስም በይበልጥ የሚታወቀው ሳሻ ባረን ኮን እና ጄኔፈር ሎውረን ይገኙበታል፡፡

አቀንቃኟ ኬቲ ፔሪም ይህንኑ ተቃውሞ መቀላቀሏን አስታውቃለች፡፡

ፔሪ በኢኒስታግራም አልበሟ ሰሌዳ ላይ እንደጻፈችው ‹‹ፌስቡክ በጥላቻ ሲነዛ እንዳላየ ሆኜ ማለፍ አልችልም›› ብላለች፡፡

ተወዳጁ መልከመልካም ተዋናይ አሽተን ኩቸር ሚሊዮን ተከታዮች አሉት፤ በፌስቡክ፡፡ ‹‹እነዚህ ማኅበራዊ ሚዲያዎች የተፈጠሩት ጥላቻን ለመንዛት አይደለም፤ እብደቱ ይቁም›› ብሏል፡፡

ይህ ፌስቡክ በጥላቻ ንግግር ማትረፍ ይቁም የሚለው ዘመቻ የተጀመረው ባለፈው ሰኔ ወር ላይ ነበር፡፡

ፌስቡክ ድርጅት ኢኒስታግራምና ዋትስ አፕን ጭምር በባለቤትነት ያስተዳድራል፡፡

ፌስቡክ ባለፈው ዓመት ብቻ ከማስታወቂያ 70 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ አጋብሷል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com