ቅምሻ ከእኛ- ለእኛው (ኢትዮጵያዬ) የመቀለ ዩኒቨርስቲ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት ፕሮፌሰር ፈቴን ማን ናቸው?

Views: 54

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ፕሮፌሰር ፈቴን አባይ የመቀለ ዩኒቨርስቲ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ሆነው መሾማቸው ተሰምቷል። ፕሮፌሰሯ ይህንን ኃላፊነት የተቀበሉት ፕሮፌሰር ክንደያ ገ/ሕይወት የኃላፊነት ጊዜያቸው አብቅቶ መነሳታቸውን ተከትሎ መሆኑ ተገልጿል። ፕሮፌሰር ፈቲን በዚህ ዩኒቨርስቲ ይህንን ኃላፊነት ሲያገኙ የመጀመሪያዋ ሴት ናቸው። ፕሮፌሰሯ አብረዋቸው በሚሰሩ እና በሚያውቋቸው ዘንድ በርካታ ምርምሮችን በመስራት በስፋት የሚታወቁ ምሁር መሆናቸው ይገለፃል።

ለመሆኑ ፕሮፌሰሯ ማን ናቸው? ሲል ቢቢሲ ይጠይቃል፤

ፕሮፌሰር ፈቴን የተወለዱት ከመቀለ 45 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ውቅሮ ከተማ ነው። የፕሮፌሰሯ ቤተሰቦች 12 ልጆች ያፈሩ ሲሆን፣ እርሳቸውም ለቤተሰቡ የመጨረሻ ልጅ ናቸው።

ፕሬፌሰር ፈቴን ገና የ12 ዓመት ልጅ ሳሉ ሦስት ጉልቻ እንዲመሰርቱ ታስቦ እንደነበር የሚያስታውሱት ፈቴን፤ ለትዳር የታጨላቸው ግለሰብ ደግሞ በእድሜ በሦስት እጥፍ የሚበልጣቸው እንደነበረ ይናገራሉ።

ፕሮፌሰር ፈቴንን ከእዚህ በርካታ ኢትዮጵያውያን ታዳጊ ሴቶች ከሚገጥማቸው ካለ እድሜ የመዳር አጋጣሚ ያዳኗቸው እናታቸው መሆናቸውን ይናገራሉ። ከዚህ በኋላ ነበር ወደ ትምህርት ቤት ገብተው የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአጥጋቢ ሁኔታ ተከታተሉ።

ከዚያም የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ወስደው ለኮሌጅ መግቢያ የሚያበቃ ውጤት በማግኘታቸው በሐዋሳ የግብርና ኮሌጅ የእጽዋት ሳይንስ አጥንተው በዲፕሎማ ተመርቀዋል።

ትምህርታቸውን ካተናቀቁ በኋላም ከአስር ዓመታት በላይ በገጠራማ የኦሮሚያ እና የአማራ ክልል አካባቢዎች በመሰመራት በሙያቸው ተሰርተው አገልግለዋል።

ፕሮፌሰር ፈቴን ተመርቀው ወደ ሥራ ከገቡበት ጊዜ አንስቶ ከአርሶ አደሮች ጋር ውጤታማ የሆኑ ሥራዎች በመስራት የሚታወቁ ሲሆን፤ ለዚህም ሥራቸው ከማኅበረሰቡም ሆነ ከተለያዩ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት እውቅናን አግኝተዋል።

በተለይ የምዕራብ ሐረርጌ አርሶ አደሮች ፕሮፌሰሯ በአካባቢው በሚሰሩበት ወቅት በጥረታቸው የውሃ ምንጭ እንዲያገኙ በማድረጋቸው ለክብራቸው ሲሉ በስማቸው እንደሰየሙት ይጠቀሳል።

ከዚህ ጎን ለጎን በሐረማያ ዩኒቨርስቲ የዲግሪ ፕሮግራም የመማር እድል አግኝተው ትምህርታቸውን በመቀጠል በ1991 ተመርቀዋል።

የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ካገኙ በኋላም፣ በእርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት ተመራማሪ በመሆን ሰርተዋል። ከሁለት ዓመት በኋላ በ1993 ዓ.ም በመቀለ ዩኒቨርስቲ የምርምር እና የማስተማር ሥራቸውን ቀጠሉ። ፕሮፌሰር ፈቴን በመቀጠልም ወደ እንግሊዝ በመጓዝ ትምህርታቸውን የቀጠሉ ሲሆን፤ እዚያም በገጠር የተፈጥሮ ሀብት አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።

ረዘም ላለ ጊዜ በመቀለ ዩኒቨርስቲ በመማርና ማስተማር እንዲሁም ጥናት በመስራት ቆይተው በ2007 የዶክትሬት ዲግሪ ለማግኘት የሚያስችላቸውን ትምህርት ለመከታተል ወደ ኖርዌይ አቅንተው በዘርና እጽዋት ሳይንስ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።

ፕሮፌሰሯ በትግራይ ከተለያዩ አርሶ አደሮች ጋር በጋራ በመስራት የተለያዩ ሰብሎችን ዘር የማሻሻል ሥራዎችን አከናውነዋል።

በተጨማሪም የእርሻ ልማትን በማሳደግ ላይ ያተኮሩ ከ45 በላይ የምርምር ጽሁፎች በማዘጋጀት በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ አሳትመዋል።

በ2015 ደግሞ በኢትዮጵያ በዘር ማዳቀል ምርምር ላይ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሮፌሰር ለመሆን ችለዋል። እንዲሁም በአትክልትና እጽዋት ላይ ለሚደረጉ ምርምሮች በአገር አፍ ደረጃ ሦስተኛዋ ፕሮፌሰር ናቸው።

ፕሮፌሰር ፈቴን በኢትዮጵያ ውሃና የአፈር ጥበቃ እንዲሁም የዘር አያያዝን በሚመለከት ከአርሶ አደሮች ጋር አብሮ ሲሰሩ የአርሶ አደሮቹን ነባር እውቀት በመጠቀም ከሳይንስ ጋር በማስተሳሰር ሲሰሩ እንደቆዩ ይናገራሉ።

በዚህም መስክ ለአምስት ዓመታት ያህል ሲሰሩ እና ግንዛቤ የማስጨበት ሥራ ሲያከናውኑ ቆይተው ወደ ዘር ማዳቀል ምርምር ተሸጋግረዋል።

እንደ ፕሮፌሰር ፈቴን ከሆነ ይህንን የምርምር ሥራ የሚሰሩት በአርሶ አደሮች በራሳቸው ምርጫና ውሳኔ መሰረት ነው።

ከዚህ በመነሳት ከ19997 እስከ 2001 ዓ.ም በኔዘርላንድ መንግሥት ድጋፍ የተደረገለትን የውሃና የአፈር ጥበቃ ጥናት ፕሮጀክትን አስተባብረዋል።

ይህ የዓለም አቀፍ ፕሮግራም በሰባት የአፍሪካ አገሮች የሚሰራ ሲሆን፣ ፕሮፌሰሯ የዚህን ፕሮጀክት በትግራይ ሲያስተባብሩ ቆይተዋል።

ፕሮፌሰሯ በዚህ ፕሮጀክት ሴቶች በእርሻና በተፈጥሮ ሀብት አስተዳደር ያላቸው ሚና እንዲጎላ ማድረጋቸውን ይናገራሉ።

ይህ ፕሮጀክት በአሁኑ ጊዜ በአገር አቀፍ ደረጃ አድጎ እየተሰራበት ሲሆን፤ በ18 የአፍሪካ አገሮች፣ በእስያና በላቲን አሜሪካ አገራት የሚገኙ መንግሥታዊ ከሆኑና ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር እየተሰራ ነው።

ፕሮፌሰር ፈቴን ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የሥነ ምህዳር ሥርዓተ ጾታ ልማት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ሆነው የ’ድራይ ላንድ አግሪካልቸር’ መጽሔትም ተባባሪ ኤዲተር ነች።

ፈጠራና ሽልማት፡-

ፕሮፌሰር ፈቴን የገብስ ዝርያ በማዳቀል በሰሯቸው ምርምሮች ሽልማት አግኝተዋል።

የአየር ለውጥ እና ድርቅን የሚቋቋም፣ ከፍተኛ ጣዕም ያለው ሦስት አይነት የገብስ ዝርያ ማዳቀላቸውን ይታወቃል።

እነዚህ የገብስ ዝርያዎች በአንድ ሄክታር ከ4.5 እስከ 5.2 ቶን ምርት ሊሰጡ የሚችሉ ሆነው፣ ከሌሎች ዝርያዎች በበለጠ ከስልሳ በመቶ በላይ የምርታማነት ጭማሬ አላቸው ተብሏል።

በዚህ የምርምር ሥራም ከ30 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሲደረግ፣ ከ500 ሄክታር በላይ የሸፈነ ዝርያ ነበር።

እነዚህ የገብስ ዝርያዎች ፈላሚት፣ ህሪት፣ ፈቴን የሚል ስያሜ በዩኒቨርስቲው ተሰይሞላቸዋል፟።

ፕሮፌሰር ፈቴን በ2009 ዓ.ም የሴት ባለሙያ ከአምስት የአፍሪካ ተመራማሪ ሴቶች አንዷ ሆነው በአዝርዕት ምርምር ተሸልመዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥትም በ2010 ሳይንስን ከአርሶ አደሮች ጋር ለማስተሳሰር ባደረጉት ጥረት ሸልሟቸዋል።

በተጨማሪ የአፍሪካ ሕብረት በሳይንስ ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋፍኦ የኩዋሜ ንክሩማህ ሽልማት የምሥራቅ አፍሪካ ሎሬት በመባል አሸናፊ ሆነዋል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com