ዜና

ቅምሻ ከእኛ-ለእኛው (ኢትዮጵያዬ) በአፋር ወጣቶችና ፖሊስ ተጋጭተው ሦስት ወጣቶች ተገደሉ

Views: 57

በአፋር ክልል አብዓላ ከተማ ወጣቶች ከፖሊስ ጋር ተጋጭተው ሦስት ወጣቶች ከጸጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት ሲገደሉ፣ ዘጠኝ መቁሰላቸውን የዓይን እማኞችና የሆስፒታል ምንጮች ለቢቢሲ ገለጹ።

ግጭቱ የተከሰተው በክልሉ ልዩ ኃይል አባላትና በወጣቶች መካከል አብዓላ (ሽከት) ተብላ በምትታወቀው ከተማ ውስጥ ሲሆን፣ በክስተቱ የሰው ህይወት ሲጠፋ በርካቶች ቆስለዋል ሲሉ በስፍራው የነበሩ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የዓይን እማኞቹ ዘጠኝ ያህል ሰዎች የመቁስል ጉዳት እንደደረሰባቸው ሲናገሩ፤ ቢቢሲ ከሆስፒታል ምንጮች እንዳረጋገጠው ደግሞ ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ስድስት ሰዎች ቆስለው ትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኘው የአይደር ሪፈራል ሆስፒታል በድንገተኛ ክፍል የህክምና እርዳታ እያገኙ መሆኑ ተነግሯል፡፡

በወጣቶቹና በጸጥታ ኃይል አባላቱ መካከል ለተከሰተው ግጭት ምክንያቱ ምን እንደሆነ ያነጋገራቸው የዓይን እማኞች ሲመልሱ፣ “ወጣቶቹ የመስቀል በዓልን ለማክበር ለደመራ የሚሆን እንጨት ቆርጠው ሲያዘጋጁ የነበረ ሲሆን፣ የልዩ ኃይል አባላት ጥይት ተኩሰውባቸዋል” ብለዋል።

የአፋር ክልል ከትግራይ ክልል ጋር በሚዋሰንበት ድንበር አቅራቢያ የምትገኘው የአብዓላ (ሽከት) ከተማ ከንቲባ የሆኑት አቶ ጣሂር ሃሰን ለቢቢሲ እንደተናገሩት ችግሩ የተፈጠረው “በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የታወጀውን አዋጅ የጣሱ ወጣቶች ከፖሊስ ጋር በመጋጨታቸው ነው።”

በተጨማሪም “የትግራይናን የአፋር ሕዝብን ለማጋጨት ከሌላ አከባቢ የመጡ ሰዎች ያስነሱት ግጭት ነው” የሚል ግምት እንዳለ አቶ ጣሂር ቢገልፁም፣ ግምታቸውን በዝርዝር ከመናገር ግን ተቆጥበዋል።

የሟቾቹ አስከሬን በአሁኑ ሰአት በአብዓላ ከተማ በሚገኘው ሆስፒታል እንደሚገኝ ነዋሪዎች ገልፀው በግጭቱ በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ጨምረው አረጋግጠዋል።

አብዓላ (ሽከት) ከተማ በአሁኑ ሰዓት በአንጻራዊ መረጋጋት ላይ እንደምትገኝም ተናግረዋል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com