ቅምሻ ከእኛ- ለእኛው (ኢትዮጵያዬ) ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ሙዲስ ጠቆመ

Views: 35

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫውን ማራዘሟን ተከትሎ የተፈጠረው አለመግባባት በአገሪቱ የሚከናወኑ የኢንቨስትመንት ውሳኔዎች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ‹‹ሙዲስ›› የተሰኘው የአሜሪካ የቢዝነስና ፋይናንስ ተቋም ጠቆመ።

አገራዊው ምርጫ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ቢራዘምም፣ ባለፈው ሳምንት በትግራይ ክልላዊ ምርጫ ተካሂዷል። ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ምርጫውን “ሕገ ወጥ” ማለታቸው እንዲሁም የፌደሬሽን ምክር ቤት “ምርጫው እንዳልተካሄደ ይቆጠራል” እንደተባለ ይታወሳል።

ሙዲስ እንዳለው፤ ባለፉት ዓመታት ፖለቲካዊ ውጥረቶች ያስከተሏቸው ግጭቶች የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ስጋት ከፍተኛ አድርጎታል።

ሙዲስ ግንቦት ላይ የኢትዮጵያን ነጥብ ከቢ1 ወደ ቢ2 ዝቅ አድርጎታል። ለዚህም በምክንያትነት የተቀመጠው ከውጪ ምንዛሪ ገቢ ይልቅ እዳ ማመዘኑ ነው። ነሐሴ ላይ በኮቪድ-19 ምክንያት ኢትዮጵያ አሉታዊ ግምት ተሰጥቷታል። ወረርሽኙ በግብርና እና በመስተንግዶ ዘርፍ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ እንዲሁም መንግሥት ገቢው ቢቀንስም ወጪው መናሩ እንደ ምክንያት ተጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ከግብጽና ከሱዳን ጋር ስምምነት ላይ ሳትደርስ ታላቁ ህዳሴ ግድብን መሙላት መጀሯም ተጠቅሷል። በተያያዥም አስፈላጊ የጥንቃቄ እርምጃዎች ሳይወሰዱ ሙሌቱ መጀመሩ የውጪ አገራት ኢንቨስትመንቶች እንዲቀንሱ ሊያደርግ እንደሚችል ተገልጿል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቀደም ሲል አሜሪካ ለኢትዮጵያ ለመስጠት መድባ የነበረው እርዳታ ላይ እገዳ መጣሏን ይፋ አድርጋለች።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን በጥሩ ሁኔታ ማስቀጠል መቻሏ ወደ አገሪቱ ኢንቨስትመንት እየሳበ መሆኑን ሙዲስ ገልጿል።

ለዓመታት በመሠረተ ልማት ዝርጋታው ዘርፍ የውጪ ኢንቨስትመንት ከሳበች በኋላ፤ አይኤምኤፍ በፍጥነት ምጣኔ ሀብታቸው እያደገ ያሉ ካላቸው የአፍሪካ አገሮች ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያ ትገኝበታለች።

ሙዲስ የተባለው ተቋም ዓለም አቀፋዊ በሆኑ በተለያዩ የፋይናንስና ምጣኔ ሃብት እንዲሁም የብድር ጉዳዮች ላይ ምርምሮችን በማድረግ የሚታወቅ ሲሆን፣ ከዚህ በመነሳትም የአገራትን የብድር አዋጭነት ደረጃ ያወጣል።

ሙዲስ በዓለም ላይ ካሉ ከሦስቱ ተሰሚነት ካላቸው ተመሳሳይ ተቋማት አንዱ ሲሆን፣ አገራትና መዋዕለ ነዋይ አፍሳሾች ሙዲስን የመሳሰሉ የምጣኔ ሀብትና የፋይናንስ ተቋማት በሚያወጧቸው ትንተናዎችና ደረጃዎች ላይ በመመርኮዝ ቁልፍ ውሳኔዎችን ያሳልፋሉ።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com