ቅምሻ ከእኛ- ለእኛ (ኢትዮጵያዬ) የብር ወረቀት መቀየር የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ አመኔታ እንዲጨምር ያደርጋል ሲሉ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ገለጹ

Views: 39

የኢትዮጵያ ብር ‹‹ኖቶች›› መቀየር፣ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የሚያካሂዱትን ኢንቨስትመንት በማስፋፋት ኢኮኖሚያዊ አመኔታን እንደሚያሳድግ ተገልጿል፡፡ አዲሱን የብር ‹‹ኖት›› በተመለከተ ከምጣኔ ሃብት ባለሙያውና የኦሮሚያ ፕላንና ኢኮኖሚ ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ተሾመ አዱኛ ጋር ኢዜአ ቆይታ አድርጓል፡፡
ዶክተር ተሾመ እንዳሉት ገንዘብ የአንድ አገር ኢኮኖሚ ደም ስር ነው፤ ሰዎች የሚፈልጉትን ማግኘት እንዲችሉ የጋራ መለኪያ ሆኖ ያገለግላል፡፡
ኢኮኖሚን በመለካት፤ በማጠራቀም እና ልውውጥ እንዲካሄድ በማስቻል ገንዘብ የአንድን አገር ኢኮኖሚያዊ ህልውና አስጠብቆ እንዲሄድ ያደርጋልም ነው ያሉት፡፡
አሁን የተደረገው የብር ኖቶች ለውጥም እነዚህን ነገሮች በማጠናከር ከዚህ በፊት በህገወጥ መንገድ ተይዞና ተደብቆ የነበረን ብር በመቆጣጠር ህጋዊ እንዲሆን ያስችላል ብለዋል፡፡
አሁን አገልግሎት ላይ ያለው የብር ‹‹ኖት›› በግለሰብ እጅ በብዛት በመኖሩ የተከሰተውን ህገ-ወጥ ንግድ ለመቆጣጠር እና ህገ ወጥ የገንዘብ ምንዛሬን ለማስቆም ትልቅ አቅም ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡
እንደ ባለሙያው ማብራሪያ የብር ኖቶቹ መቀየር ኢኮኖሚ በማረጋጋት ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የሚያካሂዱትን ኢንቨስትመንት በማስፋፋት የምጣኔ ሃብት አመኔታን ያሳድጋል፡፡
“ሰዎች የአሜሪካን ዶላር በብዛት የሚጠቀሙት ዋጋው ባለበት ስለሚቆይና ባለመዋዠቅ ኢኮኖሚያዊ አመኔታን ስላተረፈ ነው” የሚሉት ዶክተር ተሾመ፤ አሁን ላይ መንግስት የፋይናንሱን ሴክተር ደህንነት ባጠናከረ ቁጥር ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ብር መዋዕለ ንዋይ ያፈሳሉ በማለት ይገልጻሉ፡፡
ንብረቶችን በመግዛትም የኢትዮጵያን ብር የግብይትና የሽያጭ መጠቀሚያቸው እንዲሆን ያደርጋሉም ብለዋል፡፡
ይህም በተለያዩ ዘርፎች የሚካሄዱ የስራ እድል ፈጠራዎችን ለማሳካት እድል የሚሰጥ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል የብር ‹‹ኖቶቹ›› በህጋዊ መስመር ስር ስለሚሆኑ የመንግስትን የገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማ ለማድረግና በገንዘብ ዝውውር ላይ የሚወሰኑ ጉዳዮችን ለማስፈጸም ያስችላል ብለዋል፡፡
በቀጣይ አዲሱን የብር ‹‹ኖት›› በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንዲዳረስ ባንኮችን፤ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማትንና ህብረት ስራ ማህበራትን በሰፊው መጠቀም አንደሚያስፈልግም ባለሙያው አብራርተዋል፡፡
ከፍተኛ የገንዘብ ዝውውር የሚፈጸምባቸውን አካባቢዎች በመለየት ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚያስፈልግም ነው ዶክተር ተሾመ የገለጹት፡፡
የኢኮኖሚ ባለሙያዎችም በጥናት ላይ የተመሰረተ ውጤታማ ሃሳብ በማምጣት ከመንግስት ጋር ሊሰሩ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com