ቅምሻ ከእኛ- ለእኛው (ኢትዮጵያዬ) በጣና ሃይቅ ውሃ መሙላት ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ እየቀረበ ነው

Views: 42

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የጣና ሃይቅ ሞልቶ ባስከተለው የጎርፍ መጥለቅለቅ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ከ5 ሺ በላይ አባወራና ቤተሰቦቻቸውን የመደገፍ ስራ እየተካሄደ መሆኑን የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

ሃይቁ ባስከተለው መጥለቅለቅ አካባቢያቸውን የለቀቁ የምስራቅ ደንቢያ ወረዳ አርሶ አደሮች በበኩላቸው በሰብልና በንብረታቸው ላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ እንደተናገሩት ጉዳቱ የደረሰው በሃይቁ አዋሳኝ በሆነው ምስራቅ ደንቢያ ወረዳ በሚገኙ አራት ቀበሌዎች ውስጥ ነው።

ተጎጂዎችን ፈጥኖ ለመደገፍ በተደረገው ጥረት 16 የሸራ ድንኳኖችን በማዘጋጀትና ለመኝታ የሚውሉ 500 ፕላስቲክ ንጣፍ የማሰራጨትና ነዋሪዎቹን ወደ ደረቃማ ቦታዎች የማስፈር ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ሃይቁ እያስከተለ ያለውን መጥለቅለቅ ለመቆጠጣርም ከ3 ሺህ በላይ ጆንያዎችን በአፈር በመሙላት በህብረተሰቡ ተሳትፎ ጊዜያዊ የጎርፍ መከላከያ ግድብ ቢሰራም የመጥለቅለቅ መጠኑ ከፍ ያለ በመሆኑ በሚፈለገው ልክ ውጤታማ ማድረግ እንዳልተቻለ ተናግረዋል።

ለተፈናቃዮቹ ለእለት ምግብ የሚያውሉት አንድ ሺህ ካርቶን ብስኩት መሰራጨቱን ጠቁመው፤ አንድ ሺህ 113 ኩንታል የምግብ እህልም ወደ አካባቢው እንዲጓጓዝ መደረጉንና ከነገ ጀምሮ እርዳታውን ማሰራጨት እንደሚጀመር ገልፅዋል።

በተጨማሪም 3 ሺህ ሊትር የምግብ ዘይት አንድ ሺህ 312 ብርድ ልብስና አንድ ሺህ 312 የውሃ መቅጃ ጄሪካን ወደ ቀበሌዎቹ እየተጓጓዘ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡

በውሃ ብክለት ሳቢያ በተፈናቃዮች ላይ የጤና ችግር እንዳይከሰትም የውሃ ማከሚያ ኬሚካሎች እየተሰራጩ መሆኑን ጠቁመው፤ ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ኮሚቴም መቋቋሙን አመልክተዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com