በአማራ ክልል ከ800 በላይ የነዳጅ ማደያዎች ሊገነቡ መሆኑ ተገለጸ

Views: 56

በአማራ ክልል የነዳጅ አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ ተጨማሪ ከ800 በላይ የነዳጅ ማደያዎችን ለመገንባት መታቀዱን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታውቋል። በዚህም በአማራ ክልል የነዳጅ አቅርቦት ችግሩን ለመፍታት አዲስ የነዳጅ ማደያ እና የቦታ አሰጣጥና አጠቃቀም መመሪያ መውጣቱ ተገልጿል።

አዲስ የወጣውን መመሪያ አስመልክቶ የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ እና የከተማ ልማት እና ቤቶች ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊዎች ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ተዋቸው ወርቁ በሰጡት መግለጫ፣ በክልሉ 202 የነዳጅ ማደያዎች መኖራቸውን አስታውቀዋል።
እነዚህ የነዳጅ ማደያዎች በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ለተመዘገቡ 100 ሺህ ተሽከርካሪዎች እንኳን አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ካለማድረጋቸውም ባለፈ ደረጃቸው ዝቅተኛ መሆንም ሌላኛው ችግር ሆኖ መቆየቱን ምክትል ቢሮ ኃላፊው በመግለጫቸው አብራርተዋል።

ከዚያም ባለፈ የነዳጅ ዋጋ በመንግስት ተመን የሚመራ መሆን እና ባለሃብቶች በጨረታ እንዲወዳደሩ መደረጉ፣ በቂ የነዳጅ ማከፋፈያ መሰረተ ልማት አለመኖር፣ ለተለያዩ አገልግሎቶች ነዳጅ የሚጠቀመው የኅብረተሰብ ቁጥር እና የነዳጅ አቅርቦት አለመመጣጠንም ሌላኛው ችግር መሆኑንም ነው ያነሱት። ይህም በክልሉ ኢኮኖሚ ላይ ጫና መፍጠሩን አቶ ተዋቸው ወርቁ አመላክተዋል።

ችግሩን ለመፍታትም ጥናት ሲካሄድ መቆየቱንና በጥናቱ መሰረት በክልሉ በተጨማሪ ከ800 በላይ ማደያዎች እንደሚገነቡ አቶ ተዋቸው አስታውቀዋል።

የሚገነቡት የነዳጅ ማደያዎች እስከ ስድስት ታንከሮችን መቅበር የሚያስችሉ እና ሱቆችን፣ ካፍቴሪያዎችን፣ ቢሮዎችን እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ያካተቱ ይሆናሉ ነው የተባለው።

የአማራ ክልል የከተማ ልማትና ቤቶች ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወንድምነው ክንዱ በበኩላቸው፣ ግንባታዎቹ በ2013 ዓ.ም ተጠናቅቀው በ2014 ዓ.ም አገልግሎት እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
ማደያዎቹ ተገንብተው ሲጠናቀቁ የክልሉ የነዳጅ ማደያዎች ቁጥር ከ1 ሺህ በላይ ይሆናሉ ማለታቸውን አብመድ ዘግቧል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com