የቀበሪቾ እና የዘመዶቹ የሳይንስ ስሞች የመስጠት ሂደት

Views: 105

መስፍን ታደሰ (ፒ ኤች ዲ)
(የእጽዋት ተመራማሪ) 

መግቢያ – ይህንን ጽሁፍ ሳዘጋጅ ሁለት በተደጋጋሚ ለሚደርሱኝ ጥያቄዎች መልስ ይሆናል በሚል ግምት ነው። በብሔራዊ ቋንቋችን፣ ታዋቂ የሆነን ዕጽ እንደምሳሌ በመውሰድ፣ ቀለል ባለ መንገድ ለማብራራት እና አስረጅ ወይም አስተማሪ ይሆናል በሚል እሳቤም ነው። ጥያቄዎቹ፡ ፩ኛ፣ በሳይንስ የዕጸዋት ስም እንዴት ነው የሚወጣው ወይም አንድ ዕፅ እንዴት ነው ስም የሚያገኘው? ፪ኛ ስም የወጣለት ዕፅ ናሙና አለው ይባላል፡ ምን ማለት ነው? የት ይቀመጣል? ፫ኛ፡ ልክ በሙዚየም እንዳሉት እንደ እንስሳት ናሙና ማየት ወይም መጎብኘት ይቻላል? ወይ የሚሉ ናቸው። ይህ ጽሁፍ ለማስተማሪያነትም ሊያገለግል ይችላል።

ቀበሪቾ (በአማርኛ) ወይም ቀረቢቾ (በኦሮምኛ) በኢትዮጵያ የሐገረሰብ ወይም ባህላዊ ሕክምና ትልቅ ስፍራ ያለው ዕጽ ነው። ትልቁን የመርካቶን ገበያ ጨምሮ በብዙ የከተማና የገጠር ገበያዎች ውስጥ ይሸጣል።

ጥቅሙ – በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በተለይ ቀበሪቾ ወይም ቀረቢቾ ተወዳጅ የሆነ የመድሃኒት ዕፅ ነው፣ ሴቶች ራሳቸውን እና ቤታቸውን በቀበሪቾ ጭስ ያጥናሉ፣ በተለይም ከልጅ መውለድ በኋላ በሰፊው ይጠቀሙበታል። በደቡብ ኢትዮጵያ የቦረና ሴቶች እንዴት እንደሚጠቀሙበት ዶክተር ገመቹ ዳሌ በአንድ የሳይንስ ጽሁፍ ላይ እንዲህ ጽፎ አስነብቦናል። በቤት ውስጥ ወደ መሬት ገባ ብሎ ጉድጓድ ይቆፈርና ዙሪያውን በጨርቅ ይሸፈናል። ከዚያም መቀመጫው ክፍት የሆነ ባለአራት እግር ወንበር ከጉድጓዱ ውስጥ ከፍ ብሎ ይቀመጣል፣ ጉድጓዱ ውስጥ ከመሃል የከሰል ወይም የእንጨት እሳት ይነድና ፍም ሲሆን እዚያ ላይ ቀበሪቾ ተቆራርጦ ይቀመጣል፤ የወለደችዋ ሴት ከክፍቱ ወንበር ላይ ተቀምጣ ራሷን ታጥናለች። አስፈላጊ ከሆነ ይህ በተደጋጋሚ ወይም በሌላ ቀናት ሊሆንም ይችላል።

ባህላዊ ወይም ሐገረሰባዊ መድሃኒትነት – ቀበሪቾ ምንድነው? በውስጡስ ምን ይዟል? ሴቶችስ እንዴትና ለምንድነው የሚታጠኑት? ለሚሉት ጥያቄዎች እኔና የሥራ ባልደረቦቼ በመጀመሪያ ያገኘናቸው መልሶች ቀበሪቾ የዕጽ የስር ግንድ እንደሆነና ሴቶች ራሳቸውን ከቆዳ በሽታ ለመከላከል እንደሆነ ነው። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ሴቶች በሚወልዱ ጊዜ ለሚደርሱ የሴት ብልት የተሃዋስያን ጥቃት ለመከላከል ነው ሲሉ የሃገረሰብ ሕክምና የሚያውቁ ሰዎች ይናገራሉ፤ በጽሁፍ የምናገኘውም እነዚሁኑ ገላጭ ናቸው።

ምርምር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ – ይህንን የቀበሪቾን የባህላዊ የመድሃኒትነት ጥቅም ያጤኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኬምስትሪ ክፍል አባላት በ፲ ፱ ፻ ፸ ፯ (1977) ጥናት ማድረግ ጀመሩ፤ ቀበሪቾን ከመርካቶ በመግዛት ውስጡ የያዘውን ንጥረ ነገር ለማወቅ ሞከሩ፣ ሙከራቸው እየተሳካ ሲሄድ እና ምናልባትም ለሳይንስ አዲስ የሆነ ንጥረ ነገር እንዳለው ሲረዱ ለመሆኑ የቀበሪቾ የሳይንስ ስም ማነው? እያሉ መጠየቅ ጀመሩ፣ መጽሃፎች አገላበጡ፣ ነገር ግን ስም ሊያገኙለት አልቻሉም፤ በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሃገራት ያሉን ጽሁፎች እና መጽሃፎች ተመለከቱ፣ ምንም አላገኙም። ከዚያም ወደ ብሔራዊው የእጸዋት ቤተመዘክር ሄደው መጠየቅ ያዙ፣ እዚያም የሳይንስ ስሙ አልተገኘም። የዚህን ጊዜ ነው ያ የኬምስትሪው ባልደረባ የዚህን ጽሁፍ ደራሲ እባክህን ላስቸግርህና የቀበሪቾን የሳይንስ ስም ፈልግልኝ ያለው እና እኔም በቤተመዘክሩ የነበሩትን የእጸዋት ናሙናዎች በጥሞና መመልከት የጀመርኩት። ጥናቱ ቢደረግና ያለሳይንስ ስም የጥናቱን ውጤት ለአንባቢና ለተጠቃሚ ማድረስ ቢቻልም፣ የተሟላ አያደርገውም። ሌሎች አጥኚዎች ተመሳሳይ ጥናት በማድርግ ውጤቶቹን ለማወዳደር ቢፈልጉ እንኳን ናሙናው በማያሻማና በግልጽ የሚታወቅ መሆን አለበት። በሳይንስ ይህ ናሙና ቫውቸር (Voucher) ይባላል። ጥናት የሚያደርጉ ሁሉ በተቻለ መጠን የናሙናቸውን መለያ ሁኔታ፣ ማለትም ስም፣ ተራ ቁጥር፣ የተቀመጠበት ቦታ፣ ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል።

የቀበሪቾን የሳይንስ ስም ፍለጋ– የቀበሪቾ የወል የላቲን ስም “Echinops” መሆኑን ካረጋገጥኩ በኋላ በዚህ የወል ስም ተመዝግበው የሚገኙትን የእጸዋት ናሙናዎች ሁሉ አንድ በአንድ ማጥናት ጀመርኩ። ጥናቱም ቅጠሎቻቸውን፣ አበባዎቻቸውን፣ እና ፍሬዎቻቸውን በማጉያ መነጽርና በማይክሮስኮፕ በመመልከት ነበር። ሳይንስ ለፍጡራን ሁሉ ስም ይሰጣል ወይም ያወጣል። የእነዚህ ስሞች መሰረት የላቲን ፊደል ነው። የላቲን ቋንቋ የተመረጠው ቀድሞ በነበሩ የሳይንስ ሊቀ ጠቢባን ነው። ሁለት ምክንያቶች ነበሯቸው፤ አንደኛው ታሪካዊ ነው፣ ቀድሞ የነበሩ ጠቢባን የመግባቢያ ቋንቋ ላቲን ስለነበር በላቲን እየጻፉ ጽሁፎቻቸውን ይላላኩ፣ ይለዋወጡና ይቀያየሩ ስለነበርና ያ ታሪክ እንዲቀጥል ስለተስማሙ አንደኛው ምክንያት ሆኖ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ላቲንን የእኔ ቋንቋ ነው ብሎ የወረሰ ሃገር ስለሌለ ነው። በእነዚህ ሁለት ታላላቅ ምክንያቶች እጸዋት፣ እንስሳት፣ ባክቴርያ፣ ወዘተ የላቲን ስሞች እንዲኖሪቸው ተደረገ።

የቀበሪቾ የሳይንስ ስም ጥናት በአዲስ አበባ – የተሟላ የሳይንስ ስም የነበራቸውን ናሙናዎች ከሌላቸው በመለየት ጥናቴ ቀጠለ። ቀስ በቀስ ሙሉ የላቲን ስም ያላቸውን አንዱን ከሌላው የሚለይበትን ጠቋሚ ጠባዮች ማወቅ ቻልኩ። ቀለል ያሉትና አስቸጋሪ ያልሆኑትን በመተው ለመለየት አስቸጋሪ በሆኑት ላይ ትኩረት ማድረግ ጀመርኩ። በቤተመዘክሩ የነበሩት ናሙናዎች በቂ ስላልነበሩና የመስክ እይታና ጥናት አስፈላጊ በመሆኑ በተደጋጋሚ ወደ ልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በመሄድ የቀበሪቾን ዘመዶች በሙሉ ናሙናዎች መሰብሰብ ጀመርኩ። አንድ ሁለት ጊዜም ከኬምስትሪው ባልደረባዬ ጋር ለመስክ ጥናት አብረን ተሰማራን። ብዙ ናሙናዎች ሰብስበን።

ቀበሪቾና ዝርያዎቹ እሾሃማ ቅጠሎች ስላሉት በእጸዋት ጥናት ተግባር የተሰማሩ ሰዎች ብዙ አልሰበሰቡትም ነበር። ለዚህም ነበር በቤተመዘክሩ ተከማችቶ ያልተገኘው። ይህ የብዙዎቹ እሾሃማ እፀዋት እጣ ፈንታ ነው፣ ሰዎች ግድ ካልሆነባቸው በስተቀር አይሰበስቧቸውም፤ በእነርሱ ላይ ያተኮረ ጥናት ሲደረግ ብቻ ነው በበቂ ሁኔታ ተሰብስበውና ተከማችተው ሃገር ውስጥም ይሁን በውጭ ሃገር በሚገኙ ቤተመዘክሮች የሚገኙት።

የቀበሪቾ የሳይንስ ስም ጥናት በእንግሊዝ ሃገር – እኔ የሰበሰብኳቸውን ናሙናዎች በዓይነት በዓይነታቸውና በውጫዊ ይዘታቸው ወይም ጠባያቸው (በእንግሊዝኛ ሞርፎሎጂካል ጠባይ ማለት ነው፡ ማለትም የአበባ፣ የፍሬ፣ የቅጠል ይዘት ወይም ሁኔታ) ከለየዃቸው በኋላ ከእያንዳንዱ ዓይነት ወኪል የሚሆኑትን ይዤ ወደ እንግሊዝ ሃገር፣ ለንደን፣ ወደሚገኘው ኪው (Kew) ወደሚባለው የእጸዋት ቤተመዘክር ተጓዝኩ። ይህ ተቋም ወደ ዘጠኝ ሚሊዮን ያህል ከመላው አለም የተሰበሰቡ የእጸዋት ናሙናዎች ተከማችተው የሚገኙበት ቦታ ነው። እዚያ ያሉ ናሙናዎች ብዙዎቹ የሳይንስ ስሞች አሏቸው። የሌላቸውም በባለሞያዎች በየጊዜው እየተጠኑ ስም ይወጣላቸዋል።

እዚያ ለስድስት ሳምንታት በቆየሁባቸው ጊዜያት በቤተመዘክሩ የሚገኙትንና በመጀመሪያ ከኢትዮጵያ በልዩ ልዩ ሰዎች ተሰብስበው የተከማቹትን አጠናሁ። ከዚያም በምሥራቅ አፍሪካ፣ ቀጥሎም በምዕራብ እና በሰሜን አፍሪካ ያሉትን ሁሉ በአጥጋቢ ሁኔታ ካጠናሁ በኋላ ከአፍሪካ ውጭ ያሉትን አንዳንድ ዝርያዎች በተለይም እንደአረም ሆነው ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች የአፍሪካ ሃገሮች ውስጥ የገቡትና በየመንገዱ የሚገኙትን ከሜዲተራንያን አካባቢ ሃገሮች የመጡ እጸዋትን ማጥናት ቀጠልኩ።

የሳይንስ ስም የማውጣት ሂደት – እያንዳንዱን ዘር በበቂና በተሟላ ሁኔታ ካጠናሁ በኋላ አንዱን ከሌላው ለመለያ የሚያስችል ጽሁፍ ጻፍኩ፣ ጽሁፉ ቁልፍ (Key to species) ይባላል። ይህንንም ቁልፍ በመጠቀም ከኢትዮጵያ የመጡትን ለይቶ ለማወቅ ሞከርኩ። እንግዲህ በዚህን ጊዜ ነው ቀበሪቾ የሳይንስ ስም እንደሌለው ያወቅሁት። እስከዚያ ጊዜ ድረስ አላውቅም ነበር። የእያንዳንዱን ዝርያ ገላጭ የሆኑ ውጫዊ ባህርያት እንደገና፣ በተደጋጋሚ መፈተሽ ነበረብኝ። ስለዚህ የተለያዩ ባህርያት ጥምረትን እየለዋወጥኩ በመጻፍ ቁልፉን እየቀየርኩ ለሰበሰብኳቸው እጸዋት ስም ማግኘት መቻሌን ወይም አለመቻሌን ማረጋገጥ ነበረብኝ።

ስዕል ፩የቀበሪቾ የላይኛው ክፍል በክብ ወይም ኳስ መልክ ችምችም ብለው ከተፈጠሩት አበቦች ጋር። አዋሳ አካባቢ፣ ከጥቁር እንጭኒ ወደ ሸነን በሚወስደው ሜዳ ላይ በየካቲት ፲ ፫ ቀን፡ ፲ ፱ ፻ ፹ (February 21, 1988) ዓም የተነሳ ፎቶግራፍ።

በስዕል ፪ የሚታየው ፎቶግራፍ በስዕል ፩ ከሚታየው ዕጽ አንድ ቅርንጫፍ ከነአበቦቹ ተወስዶ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሚገኘው የእጸዋት ቤተ መዘክር ውስጥ ተቀምጦ የሚገኘውን የቀበሪቾ ልዩ ወይም መሠረታዊ የሆነ ናሙና ነው። በእንግሊዝኛ (Type Specimen) ይባላል። የቀበሪቾ የሳይንስ ስም ሲሰጥ ወይም ሲወጣ የስሙ መለያ የሆኑን እና የዕጹን ውጫዊ ጸባዩን ገላጭ የሆኑ ቅጠሎች፣ ቅርንጫፍ፣ አበቦች፣ ወዘተ፣ የያዘ ናሙና ማለት ነው። እንደ ኳስ ክብ የሆኑት አበቦች ሲደርቁ ስለሚለያዩና ስለሚበታተኑ በትንሽ ፖስታ ወይም ከረጢት ውስጥ ተቀምጠዋል። እነዚህ እና የመሳሰሉት ናሙናዎች በቤተመዘክር ውስጥ ከተቻለ ተለይተው በልዩ ቁምሳጥን ይቀመጣሉ። ካልተቻለ ደግሞ ልዩ ቀለም ባለው ማቀፊያ ውስጥ ይቀመጣሉ። የእጸዋት ናሙናዎች ሙዚየም እንደሚቀመጡ የእንስሳት ናሙናዎች አይጎበኙም። በእጸዋት ጥናት ወይም ምርምር ስራ ላይ ላሉ ብቻ ነው የሚፈቀደው። ሆኖም ምን ይመስላል ብሎ ለማየት የእጸዋት ቤተመዘክሩን ሃላፊ ማነጋገር ወይም የተወከለውን ሰው መጠየቅ ያስፈልጋል።

ስዕል ፪ – የቀበሪቾ ናሙና (በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የእጸዋት ቤተ መዘክር ተቀምጦ ያለ)

የሁሉንም ዝርያ ጠባዮች በአጥጋቢ ሁኔታ ካጠናሁ በኋላ ነው ወደ አዲስ ስም መፈለግ እና ስም ወደ መስጠቱ ሂደት የገባሁት ወይም የደረስኩት። በዚህም ሂደት መሰረት ቀበሪቾና የሚከተሉት የቀበሪቾ ዝርያዎች ለሳይንስ አዲስ መሆናቸውን አረጋገጥሁና ሁሉም ስሞች አገኙ ወይም ተሰጣቸው። እነርሱን እና ሌሎቹን የቀበሪቾ ዝርያዎች ያካተተ ጽሁፍ አዘጋጀሁ።

የሳይንስ ስሙን ለዓለም የማሳወቅ ሂደት – በሙያው እና በእጸዋት ጥናት መስክ ላሉ ሌሎች ተመራማሪዎች እና ለተጠቃሚዎችም ይህንኑ ማሳወቅ ስለሚገባ ጽሁፉ መታተም ነበረበት። የትኛው የህትመት መጽሄት (ጆርናል) ውስጥ እና በምን ሁኔታ እና መቼ ለሚሉት ጥያቄዎች መልሶች ስፈልግ ነበር በየጊዜው እየተሰበሰቡ ጥናቶቻቸውን በአንድነት የሚያቀርቡትን እና የሚያትሙትን የአፍሪካ የእጸዋት ጥናት ማህበርን ከእሳቤ ውስጥ ያስገባሁት። ከዚያም በአንድ ጀርመን ሃገር በተካሄደ የአፍሪካ እጸዋት ጥናት ስብሰባ ላይ በንባብ አቀረብኩት። የስብሰባው አዘጋጆች ይህን ጽሁፍ እና ሌሎቹንም የቀረቡ ጽሁፎችን በአንድነት በአንድ ጥራዝ አሳትመው ለዓለም ሁሉ አሰራጩት። ጽሁፉ በተራ ቁጥር ፩ (1) የተመለከተው ነው። ይህ የተለመደ አሰራር ሲሆን ከሕትመት በፊት እያንዳንዱ ጽሁፍ ለትምህርቱ ቅርብ በሆኑ ቢያንስ በሁለት ሰዎች ይገመገማል። ግምገማውን ያለፈ ወይም ግምገማውን ተቀብሎ ማስተካከያ የተደረገበት ጽሁፍ ለህትመት ይበቃል። ይህ በእንግሊዝኛ ፒር ሪቪው (peer review) ወይም የእኩያሞች ግምገማ ይባላል።

አዳዲሶቹ እጸዋት የሚከተሉት ናቸው፣

፩ኛ፣ ቀበሪቾ፡ የሳይንስ ስሙ Echinops kebericho ተባለ፣

፪ኛ፣ በጎንደር ቡሃኢት ተራራ ጫፍ ላይ የሚገኝ ዝርያ፣ የሳይንስ ስሙ Echinops buhaitensis
ተባለ፣ ስሙ የተገኘበትን ቦታ ገላጭ ወይም አመልካች ነው።

፫ኛ ፣ ታንዛኒያ ውስጥ የሚገኘው Echinops lanatus ተባለ፣ “ላናተስ” የሚለው ቃል የእጹ ቅጠሎች እና ግንዶች ችምችም ባሉ ነጭ ጸጉር መሸፈኑን ለማመልከት እና ለመለያነት እንዲሆንም ነው።

የሳይንስ ስም ማውጣት ያስገኘው ውጤት – ስለ ቀበሪቾ የተጻፉትን ለማወቅ በድህረገጽ በዛሬው ቀን (ሚያዝያ ፴ ፳ ፻ ፲ ፪ ዓም)፣ የሳይንስ ስሙን አስገብቼ ስፈልግ ስድስት ሺህ ሁለት መቶ ስልሳ ውጤቶች (6,260 results) እንዳሉ አመለከተኝ። በእጹ ላይ ብዙ ስራዎች እንደተሰሩ አመልካች ነው።

የቀበሪቾ ተሃዋስያንን የማጥፋት ብቃት – እንግዲህ የኬምስትሪው ክፍል ባልደረባ ጓደኛዬ አዲሱን የቀበሪቾ የሳይንስ ስም ካገኘ በኋላ ነበር ስለቀበሪቾ ውስጣዊ ጠባይ፣ ማለትም ስለንጥረ ነገሮቹ፣ አንድ ጽሁፍ ጽፎ ለሕትመት ማብቃት የቻለው። ጽሁፉ በተራ ቁጥር ፪ (2) የተገለጸው ነው። ሌላው የኬምስትሪው ክፍል ባልደረባ ጓደኛዬ (ፕሮፌሰር ኤርምያስ ዳኜ) ከጊዜ በኋላ እንደነገረኝ የቀበሪቾ ፈዋሽ ባህርይ ከውስጡ በፈሳሽነት መልክ የሚወጣው ንጥረ ነገር ሳይሆን ሲጨስ እንደጥቀርሻ የሚወጣው ጥቁሩ ጭስ ወይም ጥላሸት ነው። ይህ ደግሞ ካርቦን (Carbon) የሚባለው ንጥረ ነገር ነው። ጥቁሩ ጭስ ወይም ካርቦን ነው የመድሃኒትነት ጠባይ ያለው። ይህንን ጥላሸት በልዩ ልዩ እንስሳት ላይ በቤተሙከራ በመፈተሽ እንዳረጋገጠ ነገረኝ።

ቀበሪቾ ፀረ ፈንገስ (anti-fungus) እና ፀረ ቫይረስ (anti virus) በተለይም ችፍ ብለው በልዩ ልዩ የሰውነት ክፍሎች፣ ለምሳሌ በከንፈር ላይ፣ በብልት ላይ ወይም ከባቢ ቆዳ ላይ የሚወጡትን ቁስሎች ለማጥፋት እንደሚረዳ ታውቋል። በሃገረሰብ መድሃኒትነት የታወቀው ቀበሪቾ በሳይንም ድጋፍ አለው።

አዲስ ክስተት – ይህንን ጽሁፍ አዘጋጅቼ ከጨረስኩ በኋላ ከዶክተር ይጋርዱ መንገሻ፣ የኢትዮጵያ የአካባቢና የደን ምርምር ተቋም አባል፣ አንድ ጥያቄ ከእፅ ምስሎች ጋር በኢሜይል እንደ ኤአ በ (May 27, 2020) ደረሰኝ። ጥያቄው እነዚህን ምስሎች እይና የቀበረቾ ምስሎች መሆን ወይም አለመሆናቸውን ግለጽልኝ ወይም አረጋግጥልኝ የሚል ነበር። የተላኩልኝ ምስሎች የፍሬዎች ብቻ ስለነበሩ ከተቻለ የእፁን መላ አካል እንዲላክልኝ ጠይቄ የተያያዙት ሁለት ፎቶዎች ተላኩ። በስእሉ የሚታዩት እጸዋት በአካባቢው ሕብረተሰብ ቀበሪቾ ነው የሚባሉት። ሥሮቻቸውም በአካባቢው ባሉ ገበያዎች በዚህ ስም እንደሚሸጡ ነበር ዶክተር ይጋርዱልሽ የጠቀሰችው። የተላኩልኝ ፎቶግራፎች ሌላ የ(Echinops) ዝርያ እንደሆነ ገልጬ ስሙ ( Echinops hispidus ) እንደሆነ ጠቀስኩ። እዚህ ላይ ስለቀበሪቾ አንድ ጥያቄ አነሳሁ፣ ሃሳብም ገባኝ። ቀበሪቾ የወል ስም ነወይ? ከሆነስ በሌሎቹ ዝርያዎች ውስጥ ተመሳሳይ ንጥረ ነገር ነወይ ያለው ወይስ ይለያያሉ? የሌሎቹንም ዝርያዎች ውስጣዊ ባሕርይ ማጥናት ይጠይቃል ማለት ነው። ይህንን ለዶክተር ይጋርዱ እና ለቀጣዩ ትውልድ አስረክባለሁ።

ስዕል ፫ Echinops hispidus – የፎቶግራፎቹ ባለቤት፡ ይጋርዱ መንገሻ
____________________________________

1. Mesfin Tadesse and Berhanu Abegaz, 1990. A revision of the genus Echinops
(Compositae – Cardueae) in Ethiopia with notes on phytogeography and chemistry. In: Ihlenfeldt, H.-D. (ed.), Mitt. Inst. Allg. Bot. Hamburg, Band 23b S. 605 – 629.

2. Mesfin Tadesse. 1990. A New Species of Echinops (Compositae, Cardueae) from East Africa. Kew Bull. 45(2): 351-352.

3. Berhanu M. Abegaz, Mesfin Tadesse and Runner Majinda, 1991. Distribution of sesquiterpene lactones and polyacetylenic thiophenes in Echinops (Compositae). Biochemical Systematics and Ecology, 19(4): 323 – 328.

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com